አዲስ አበባ፡- ሌላው ሰው አካሉንና ህይወቱን ለአገሩና ለወገኑ በሚገብርበት ሰዓት ሰላም እንዲወርድ ለማስቻል የራስን አስተዋጽኦ ማድረግ ክብር መሆኑን የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ሌላው ሰው አካሉንና ህይወቱን ለአገሩና ለወገኑ በሚገብርበት ጊዜ እንደኔ አይነቱ ሰላም እንዲወርድ፤ የእርስ በእርስ መተሳሰብ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስና አገር እንድትቀጥል ለማስቻል የራስን አስተዋጽኦ ማድረግ የክብርም ክብር ነው ብለዋል፡፡
“ኮሚሽነር ሆኜ መሾሜ ድብልቅ ስሜት ፈጥሮብኛል” ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ በአንድ በኩል ህዝብ መርጦ ለዚህ ሲያበቃ አልሰራም የማለት የሞራል ብቃቱ እንደማይኖር ገልጸዋል፡፡
የበለጠ ድብልቅ የሚያደርገው ክብደቱ ነው፤ ምንም እንኳን ወሳኙ የሚወያየውና ወደ መግባባቱ የሚመጣው ህዝብ ቢሆንም ያንን በማመቻቸቱ ሂደት ኃላፊነቱ ከባድ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ መግባት ስለሚያስፈልግ የሁሉንም ከሚሸነሮች ቡድን በሚገባ መስርቶ፣ ተዋውቆና የእነርሱን አቅምና የራሳቸውንም ጭምር በመገንዘብ የሥራ ድርሻ ነድፎና ተከፋፍሎ መሄዱና የመሳሰለው ተግባርም ቀላል እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡
ሆኖም በህዝብ ተመርጦ ወደ መግባባቱ ለመድረስ ሁኔታዎችን አመቻችልን መባል ትልቅ ክብር ነው ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ዋና ኮሚሽነሩ፤ ለሥራቸው ያላቸውን ተነሳሽነት በተመለከተ ሲገልጹ፤ አንድ ሰው ወታደርነት ሲቀጠር ምን እንደሚያደርግና የአገሬን ዳር ድንበር እጠብቃለሁ ካለ ለአገሩ ጠበቃ ወታደር ሆኛለሁ ብሎ እንደሚያስበው፤ እንዲህ አይነት ሁኔታ በሚታይበት ጊዜም ለአገር ለማገልገል ተነሳሽነቱ አጠያያቂ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት አገልግሎት ላይ ብዙ ዓመት መቆየታቸውን የጠቀሱት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ይህ ደግሞ ጫፍ ላይ የደረሰ ኃላፊነት በመሆኑ ተነሳሽነቱ እንዳላቸው ይሄም ለአገር የሚደረግ አስተዋጽኦ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
ከእርሳቸው ጋር የተሾሙት ኮሚሽነሮችም ልምድ ያላቸው ስለሆኑ ከእነርሱ በመማር የእርሳቸውንም ልምድ በማካፈል ለተሻለ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
በማመቻቸት ሂደቱ፤ መርሐ ግብር በመንደፍ መተዳደሪያ ደንባቸውን፣ መመሪያቸውን፣ ሥርዓታቸውን በማየት፣ ቢሯቸውን ማዘጋጀት እንዲሁም ለዚህ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን፣ በፊት የተጠኑ ጥናቶችን፣ የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን፣ የጥናት ግኝቶችንና ውጤቶችን የማሰባሰብ፣ ኮሚሽኑ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ችሎታና እውቀት እንደ ግብዓት በመጠቀም፣ ሁሉም ኮሚሽነሮች በአንድ መስመር እንዲጓዙ ማስቻልና መሰል ጉዳዮች ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላለመግባባት መንስኤ የሆኑ ነገሮች ምንድናቸው? የሚለውን ነቅሶ ማውጣት ቀጣይ ተግባራቸው እንደሆነ የገለጹት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ይሄንን ነቅሰው የሚያወጡት ደግሞ ከህዝቡ እንደሆነ ጠቁመዋል፡ ፡
“ለምንድነው እየተጋጨን ያለነው? በማንነት፣ በውሃ ወይስ በወሰን፣ በባንዲራ፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በአመጋገብ ወይስ በጾታ፣ በሃይማኖት? የሚሉትን እያንዳንዱን ነገር ነቅሶ ማውጣት ይኖርብናል፡፡ በአንድ ጊዜ ነቅሰን ካወጣን በኋላ ቅድሚያ መስጠት ይኖራል” ብለዋል፡፡
“አንድ ሚሊዮን ሀሳቦች ቢኖሩ አንድ ሚሊዮኑን ጠረጴዛ ላይ ለማምጣት እንኳን በተሰጠን ሦስት ዓመት ጊዜ ቀርቶ በ30 ዓመትም ላንጨርሰው እንችላለን” በማለት፤ ነገር ግን ያሉትን አጀንዳዎችን በሚገባ ነቅሶ በማውጣት የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት ውጤታማ ሥራ እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡
ለዚህም፤ “አገራችን ለሁላችንም እኩል እንድትሆንና ወደፊት በሚገባ በአስተማማኝ ሁኔታ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንድትሻገርና እንድትቀጥል ከተፈለገ ሁሉም ተባባሪ ሊሆን ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ አክለውም፤ “እኛ በኢትዮጵያ ህዝብ የወደ ፊት እጣ ፈንታ ላይ የምንወስን ሳይሆን ህዝብ እንዲወስን የምናመቻች አባላት መሆናችንን ህዝቡ ተረድቶን በእውቀትም፣ በጉልበትም በጸሎትም እንዲያግዘን ነው የምንጠይቀው” ብለዋል፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን የካቲት 18 /2014