አዲስ አበባ፡- ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚሹ ችግሮችን ለመፍታት አገራዊ ምክክሩ እንደ አንድ ትልቅ መሠረታዊ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ አስታወቁ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአገራዊ ምክክሩ አማካኝነት ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚሹ ችግሮችን ለመፍታት እንደ አንድ ትልቅ መሠረታዊ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። አገራዊ ምክክሩ ችግሮች ለመቅረፍ ተስፋ አለው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስብስብ የሆነ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ቀውስ አለ ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ችግሩ የፖለቲካ ቀውስና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ብቻ ሳይሆን የጤና፣ የኢኮኖሚ፣ የትምህርትና መሰል ችግር መሆኑን ገልጸዋል። የተጀመረው የአገራዊ ምክክር መድረክ ካሉብን ችግሮች ውስጥ ለዋነኛ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ትክክለኛው እርምጃ ነው፡፡
አገራዊ ምክክር ለማካሄድ የሚያስችል ተቋም ለመመሥረት በመንግሥት በኩል ቁርጠኝነት ታይቷል፤ ኮሚሽኑ በተገቢው ሥራውን እንዲሠራ በቀጣይም እገዛና ድጋፍ ማድረግ ከሁሉም አካል ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ዘርፍ ብዙ ለውጥ በመሆኑ በፖለቲካና በዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በባህልና በሌሎች ዘርፎች ጭምር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ፤ አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆንም የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ከኛ ማንነት ጋር አዛምዶ መፍትሔ መስጠትን ይጠይቃል። ኮሚሽነሮች ሥራቸውን መሥራት እንዲጀምሩ እድልና ድጋፍ መስጠት እንጂ ከተመሠረተ ወራቶችን ያላሳለፈ ኮሚሽንን መተቸት አስፈላጊ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በብዙ ዘርፎች ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር የሥራ ግንኙነት ይኖረዋል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በፖለቲካ ቀውስ ሳቢያ በአገራችን ካሉ ችግሮች ውስጥ አንዱ የሰብዓዊ መብት ቀውስ በመሆኑ አገራዊ ምክክሩ የሰብዓዊ መብቶች መርሕ ላይ ተመሥርቶ እንዲካሄድ የምናደርገው ክትትል ይኖራል። እንዲሁም በዘላቂነት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል የምንላቸውን ጭብጦች የኮሚሽኑ ትኩረት እንዲሆኑ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ዳንኤል ገለጻ፤ ኮሚሽኖች ከሚያከናውኑት ተግባር ውስጥ ለአገራዊ ምክክሩ አስፈላጊ የሆኑ ጭብጦችን መርጦ ማውጣት በመሆኑ በዚህ ሂደት ውስጥም ኢሰመኮ ሚና ይኖረዋል፡፡ የሚመረጡት ጭብጦች ወይም ርዕሰ ጉዳዮች ላሉብን ችግሮች መፍትሔ የሚሰጡ እንዲሆኑ ጭብጦችን በመለየት፣ ውይይቱ ሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ እንዲከናወን ለማድረግና ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች የሚወጡ ምክረ ሀሳቦችን የሰብዓዊ መብት መርሆችንና ግዴታዎችን ያከበሩ መሆናቸውን እናረጋግጣለን፡፡ ምክክር በመስጠትና የሙያ ድጋፍ በማድረግ ከኮሚሽኑ ጋር ተቀራርበን እንሠራለን ብለዋል፡፡
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም