አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል በፊትም ሆነ በአሁን ወቅት በሸኔ ቁጥጥር ሥር የዋለ ወረዳም ሆነ ቀበሌ የለም ሲል የክልሉ የጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡ መንግሥት በአሸባሪ ቡድኑ ላይ የተሳካ ዘመቻ እያካሄደ ነው፡፡
የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና የጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ አሸባሪው የሸኔ ቡድን በኦሮሚያ ክልል የተቆጣጠራቸው ቦታዎች እንዳሉ ቢነገርም ቡድኑ ከበፊትም ጀምሮ እስካሁን ድረስ የተቆጣጠረው ወረዳ፣ ቀበሌ አሊያም ምንም መንደር የለም፡፡ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለው ዘመቻም የተሳካ ሆኗል፡፡
የሽብር ቡድኑ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሯል ተብሎ ትክክለኛ ያልሆነ ወሬ ቢወራም አሸባሪው ሸኔ ሾልኮ ገብቶ ንጹሐንን ከመግደል ውጭ በፊትም ሆነ በአሁን ወቅት የተቆጣጠረው ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌ ወይም መንደር እንደሌለ ኮሎኔል አበበ ገልጸዋል፡፡ በአጥፊው የሸኔ ቡድን ሳቢያ ሕዝቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ተስኖት እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁን ወቅት በብዙ ቦታዎች ላይ ሥርዓት እንዲከበር መደረጉንም ነው ያስታወቁት፡፡
እንደ ኮሎኔል አበበ ገለጻ፤ አሸባሪው የሸኔ ቡድን የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ፣ ትምህርት ቤቶችንና የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ያወደመ ፤ ከግድያ ባለፈ ሰዎችን ከነነፍሳቸው ያቃጠለና ወደ ገደል የከተተ ቡድን ነው፡፡ ሴቶችን በባሎቻቸው ፊት የደፈረ፤ ሕጻናትን ጨምሮ እድሜያቸው 80 ዓመት የሆናቸውን አዛውንቶችን የደፈረ፤ ሰዎችን በማፈን ገንዘብ የሚጠይቅ፤ እናትን ከነልጇ እንዲሁም ልጅን እናት ፊት የገደለ፤ ቤተሰብን በአንድ ቤት ውስጥ በእሳት ያቃጠለ አጥፊ ቡድን ነው።
ከዚህ ቀደም ቡድኑ ላይ እርምጃ ሲወሰድ የነበረ ቢሆንም፤ የጁንታው ቡድን ወረራ በፈጸመ ጊዜ ሁሉም አቅሙን አገርን ከጥቃት የመከላከል ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ ሸኔ ማንሰራራቱን፤ በአገር ሽማግሌ ጭምር ወደ ሠላማዊ የትግል እንቅስቃሴ እንዲመለስ ቢጠየቅም አሻፈረኝ በማለት አንዱ አዲስ አበባ በመሆን ሌላው ጫካ በመሆን የእኩይ ተግባሩን መቀጠሉን፤ በዚህ ምክንያት መንግሥት ባደረገው ሰላም የማስጠበቅና ሕግ የማስከበር ኦፕሬሽን በቡድኑ ላይ እርምጃ መውሰዱንና በዚህም ለበርካታ ጊዜ እጅ የሰጡና የመደምሰስ እርምጃ የተወሰደባቸው የሽብር ቡድኑ አባላት መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ተታለው ወደ ሽብር ቡድኑ የተቀላቀሉ በተለያየ ጊዜ እጃቸውን ለመንግሥት በመስጠት ከጥፋታቸው መታረም እንደቻሉም አስታውቀዋል።
በክልሉ በአሁን ወቅት የሸኔ ቡድን የተቆጣጠረው አንድም ቦታ እንደሌለ በመጥቀስ፤ ቡድኑን በማጥፋት ረገድ የሕዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበርና በአሁን ወቅት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እንዳለ አመልክተዋል። ሕዝቡም ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ብለዋል። ኦፕሬሽኑ ንጹሐንን በማይጎዳ መልኩ መካሄዱንም ተናግረዋል። የሽብር ቡድኑን እስከ መጨረሻው ለማጥፋት ሁሉም ባለ ድርሻ አካል ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም