በኢግል ሂልስ ግዙፍ ፕሮጀክት ምዕራፍ አንድ እየተገነባ የሚገኘው የለገሐር አንድ ህንጻ በሲሚንቶ እጥረትና በወሰን ማስከበር ችግር የተነሳ በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ አለመሆኑ ተገለጸ።
ላጋር ኢግል ሂልስ በአዲስ አበባ ለገሐር የድሮው ባቡር ጣቢያ አካባቢ በ360 ሺህ ካሬ ሜትር ስኩዌር ቦታ ላይ የሚያርፍ 4000 መኖሪያ ቤቶችን የሚይዝ ግዙፍ ግንባታዎች አንዱ ነው። ህንፃው ከለገሐር በስተሰሜን-ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና የማህበረሰቡን የዕለት ተዕለት የጋራ ገልግሎቶችን በቀላሉ ለማግኘት በሚያስችል ቦታ ላይ እየተገነባ የሚገኝ ነው።
በራማ ኮንስትራከሽን ሥር የኢግል ሂልስ ፕሮጀክት የለገሐር አንድ ህንጻ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ዮሐንስ ጌታቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት የሲሚንቶ አቅርቦትና የወሰን ማስከበር ችግሮች በአሰሪ ድርጅቱ በኩል የሚፈቱ ናቸው። እንደ ኮንትራክተር ሲሚንቶ ከውጭ በግዢ በማስመጣት ጭምር ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት በገጠመው የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር እና የቦታ ማጽዳት ሥራዎች መዘግየት ምክንያት ፕሮጀክቱ በሚፈለገው ፍጥነት እየተሰራ አለመሆኑንም ገልጸዋል።
ራማ ኮንስትራክሽን የላጋር አንድ ህንጻ ግንባታን ለማጠናቀቅ 12 ሚሊዮን ዶላር ኮንትራት የተፈራረመ መሆኑን የገለጹት ኮንትራቱ ከፊኒሺንግ ጋር የተያያዙ ጊዜያትን ሳይጨምር 670 ቀናትን የያዘ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ የገጠመው የሲሚንቶ እጥረት ከምንጊዜውም በላይ ችግር ሆኗል ያሉት የስትራክቸር እና ብሎኬት ሥራ በዋነኛነት ሲሚንቶ የሚያስፈልገው በመሆኑ የሲሚንቶ ድጋፍ ያስፈልገናል ብለዋል።
ለገሐር ስካይ ጋርደን አንድ የመጀመሪያው በለገሐር የሚገነባው ህንጻ ሲሆን ባለ1 ፣ ባለ2፣ ባለ 3 እና ባለ 4 መኝታ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን ያካተተ ነው ። 4000 ሜትር ስኩየር ላይ እየተሰራ ያለው ለገሐር አንድ የሕንጻ ፕሮጀክት በጠቅላላው 92 አፓርትመንቶችን፣ ከ260 በላይ ፓርኪንጎችን የሚያካትት መሆኑን ገልጸዋል።
የግንባታ ሂደት 10ኛ ፎቅ የደረሰ ሲሆን፣ የብሎኬት እና የልስን ሥራ እስከ 8ኛ ፎቅ፣ የውስጥ ልስን 5ኛ ፎቅ መድረሱን ለማየት ተችሏል።
የላጋር አንድ ህንጻ ሥራ የማማከር እና ቁጥጥር ሥራ የሚሰራው የዚያስ ዲዛይን ኢንተርናሽናል ምክትል ማናጀር አቶ ምስክር ዘበነ በበኩላቸው መሰረታዊ ችግር ያሉት የሲሚንቶ እጥረት ከተስተካከለ የግንባታ ሂደቱን በሚፈለገው ፍጥነት ለማስኬድ ያስችላል ብለዋል።
በየጊዜው የተለያየ ቢሆንም አሁን ላይ በህንጻ ግንባታው ምክንያት ከ700 በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች የሥራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል።
የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ፅሕፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አዲስ አረጋይ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የላጋር ኤግል ሂልስ በአጋርነት እና በሽርክና ከሚሰሩት ሶስት ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው።
የላጋር ኢግል ሂልስ፣ አዲስ ቱሞሮ፣ አዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን እና ኤግዚቪሽን ማዕከል ፕሮጀክቶች የከተማ አስተዳደሩ በሜጋ ፕሮጀክቶች አማካይነት በአጋርነትና በሽርክና የሚሰራቸው ናቸው።
ከእነዚህም መካከል ኢግል ሂልስ ፕሮጀክት ቀድሞ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን ግንባታውም በ36 ሄክታር ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኢግል ሂልስ በሽርክና የሚለማ ሪል ስቴት ነው።
የከተማዋን ገጽታ በአዎንታዊ መልኩ መቀየር የሚችል፣ ዜጎችን የቤት ባለቤት በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ፤ የከተማዋን ቱሪዝም በማስፋት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ፕሮጀክት እንደሆነም ጠቁመዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከሰሞኑ ባደረጋቸው የከተማዋ ሜጋ ፕሮጀክቶች ጉብኝት አጠቃላይ በትላልቅ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ እና ሌሎች ችግሮችን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ባለ አቅም ለመደገፍ ዝግጁነቱን የገለጸ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የከተማ አስተዳደሩ መሬት ከማቅረብ ባለፈ በሽርክና ከሚሰራባቸው አንዱ ሥራም ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን መቅረፍ በመሆኑ የግንባታ ቦታዎችን ነጻ አድርጎ ዝግጁ ማድረግ፣ እንዲሁም በሚፈለገው ጥራት እየተካሄዱ መሆኑን መከታተል እና ድጋፍ ማድረግ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።ለፕሮጀክቱ መጓተት እንቅፋት በሆኑት የሲሚንቶ እጥረትና የወሰን ማስከበር ችግሮች እንደሚቀረፉ ተናግረዋል ።
በኃይሉ አበራ