አዲስ አበባ፡- ሰብዓዊ ድጋፍ ጭነው ወደ ትግራይ ከተጓዙት ሦስት ሺህ 297 ተሽከርካሪዎች ውስጥ አንድ ሺህ 128ቱ እንዳልተመለሱ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታ አስመልክተው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ለትግራይ ክልል እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ አሁንም ቀጥሏል። በክልሉ አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ወገኖች ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። እስካሁን ድረስ ሦስት ሺህ 297 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ ጭነው ቢሄዱም አንድ ሺህ 128ቱ አልተመለሱም።
እስካሁን ለሰብዓዊ እርዳታ የተሰማሩ የጭነት ተሽከርካሪዎች ሦስት ሺህ 297 መሆናቸውን አቶ ደበበ ጠቁመው፤ እስካሁን የተመለሱት ተሽከርካሪዎች ሁለት ሺህ 169 ሲሆኑ፤ ያልተመለሱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር አንድ ሺህ 128 ናቸው። ባልተመለሱ ተሽከርካሪዎች የሚመለከተው አካል ክትትል የሚያደርግ ይሆናል።
ለሰብዓዊ አገልግሎት ከአዲስ አበባ መቀሌ 236 በረራ መደረጉን አመልክተው፤ይህም በአጋር አካላት አማካኝነት ለሰውና ሰብዓዊ እርዳታ ጭነት ምልልስ የተደረገ ጉዞ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሰብዓዊ ድጋፉ እየተደረገላቸው ያለው በ95 አጋር ድርጅቶች አማካኝነት መሆኑን ጠቁመው፤ድጋፉ ነዳጅን ጨምሮ ጥሬ ገንዘብ፣ መድኃኒትና የተመጣጠነ ምግብ እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑትን ጭምር ያካተተ እንደሆነ ነው አቶ ደበበ ያሳወቁት።በተጨማሪም ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በለጋሽ አካላት አማካኝነት ሁለት ሺ 502 ተሽከርካሪዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ጭነው መቀሌ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ደበበ ገለጻ፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ በጥሬ ገንዘብ ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ፣216ሺህ 91ኪሎ ግራም መድኃኒት እና 421ሺህ977 ኪሎ ግራም የተመጣጠነ ምግብ በአጋር ድርጅቶች አማካኝነት በአየር ትራንስፖርት ወደ መቀሌ መጓጓዙንም ጠቅሰዋል።
130ሺ 200ኪሎ ግራም ምግብ ነክ ያልሆኑ እንደ ውሃ፣ ንጽህና መጠበቂያ መጠለያና ቁሳቁስ እንዲሁም የእርሻ ግብአቶች በአየር ትራንስፖርት መጓጓዙን ተናግረዋል። ለህጻናት፣ ለነፍሰ ጡሮች፣ ለአጥቢ እናቶች እንዲሁም ለአቅመ ደካማዎች የሚውል112ሺህ 492 ሜትሪክ ቶን የተመጣጠነ ምግብን ጨምሮ በየብስ ትራንስፖርት ከሐምሌ ወር 2013ዓ.ም ጀምሮ እንደተጓጓዘም ገልጸዋል።
ውሃ መጠለያ ቁሳቁስና የንጽህና መጠበቂያ እቃዎችን ጨምሮ 15ሺህ 554ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች በየብስ ትራንስፖርት እየተጓጓዘ እንዳለም አመላክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም 782ሺህ 396 ሊትር ነዳጅ ከሚያዝያ ወር 2014ዓ.ም ጀምሮ በየብስ ትራንስፖርት እየተጓጓዘ እንዳለ አስታውቀዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም