አዲስ አበባ፡- በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት 72 የሚደርሱ መስሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዥ ሲስተምን መጠቀም መጀመራቸውን በመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዥ ሲስተም ፕሮጀክት ማናጀር አስታወቁ፡፡
የባለሥልጣኑ የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዥ ሲስተም ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ታደሰ ከበደ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት 72 የሚደርሱ መስሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዥ ሲስተምን መጠቀም ጀምረዋል፡፡
እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ፤ የመጀመሪያው የበጀት ዓመት ጊዜ የእቅድ ማቀጃ ጊዜ በመሆኑ ተቋማቱ የግዥ እቅዳቸውን አዘጋጅተዋል። በሥርዓቱ ተጠቅመው ግዢያቸውን ፈጽመዋል። ይህ አዲስ ሥርዓት በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ችግር ያለበትን የግዥ ሥርዓቱን ያስተካክለዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሥርዓቱ ለመንግሥትና ለተጫራቾች ጠቀሜታ አለው ያሉት ማናጀሩ፤ ለመስሪያ ቤቶች ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ደረጃውን የጠበቀ እቃዎችን ለመግዛት ያስችላቸዋል ብለዋል። የግዥ ጨረታዎች በሥርዓቱ ሲሆኑ የተወዳዳሪ ቁጥር የሚጨምር በመሆኑ ጥራት ያለውን እቃን በተመጣጣኝ ዋጋ በማግኘቱ ረገድ ጠቀሜታ አለው ሲሉም ተናግረዋል።
ይህ ሥርዓት ከምንም በላይ ጊዜንና ገንዘብን ይቆጥባል የሚሉት ማናጀሩ፤ ከተጫራቾች አኳያ ጊዜና ቦታ ሳይገድባቸው በማንኛውም ሰአት የመጫረቻ ሰነዶችን ከፖርታል ላይ ማግኘትና መጫረት ይችላሉ።
ጋዜጣ ለማየት ጊዜ አያባክኑም፤ በኦንላይንም መጠቀም ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚያውጡትን የትራስፖርት ወጪ ይቀንስላቸዋል ብለዋል።
እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ፤ በማንዋል ሥርዓቱ ተጫራቾች ጨረታው ወደ አለበት መሄድ ይጠበቅባቸዋል፤ ሰነዶችን መግዛት የሚችሉት በመንግሥት የስራ ሰአት ብቻ በመሆኑ ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጋሉ። ከዚህ አንጻር አዲሱ አሰራር ለአገር ኢኮኖሚ እድገትም ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
እንደ ፕሮጀክት ማናጀሩ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ አንድ ጨረታ እስኪጠናቀቅ በአማካኝ ሁለት መቶ አስራ ሰባት ቀናት ይፈጃል። አዲሱ ሥርዓት ተግባራዊ ሲሆን ይህንን ጊዜ በግማሽ ማውረድ ይችላል። የተወዳዳሪን ቁጥር በእጥፍ በመጨመር ጥራት ያለው እቃ ማግኘት ያስችላል።
መንግሥት ለጨረታ ማስታወቂያና ለህትመት የሚያወጣውን ዋጋ በመቀነስ ከፍተኛ ብርን ማትረፍ ያስችላል። እንዲሁም የወረቀት ሕትመትን በማስቀረት ለግሪን ኢኮኖሚም ጠቀሜታ አለው ብለዋል። ጥናቶች እንዳረጋገጡት የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዥ ሥርዓትን የሚጠቀም ማንኛውም አገር ለግዥ ከሚያወጣው የትራንዛክሽን /የገንዘብ ልውውጥ/ ወጪ ከአምስት እስከ ሃያ አምስት በመቶ መቀነስ ይችላል። ኢትዮጵያ በቀላሉ አንድ በመቶ ወጪ ብትቀንስ ከአመታዊ በጀት ስልሳ አምስት በመቶው ለግዥ የሚወጣ በመሆኑ ከፍተኛ ገንዘብ ማትረፍ እንደምትችል ገልጸዋል።
የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዥ እንደ ዓለም ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቷል ያሉት ማናጀሩ፤ እ.ኤ.አ በ1991 ካናዳ ለመጀመሪያ ጊዜ መጠቀም መጀመሯን አስታውሰዋል። ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ በ2002 እና ናይጀሪያ በ2006 ይህንን ሥርዓት መጠቀም የጀመሩ ሲሆን ከፍተኛ ጥቅም እንዳገኙበትም ማናጀሩ ጠቁመዋል። ሥርዓቱን መጠቀም ከጀመሩ በኋላ በአንድ ጨረታ ይወዳደሩ የነበሩ የተጫራቾችን ቁጥር ከፍ ማድረግ ችለዋል።
ደቡብ ኮሪያ በአመት እስከ ስምንት ቢሊዮን ዶላር፣ ባንግላዲሽ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ይባክን የነበረ ብርን ማዳን ችለዋል። ሰላሳ ሰአት ይወስደባቸው የነበረውን የግዥ ሥርዓት ወደ ሰላሳ ደቂቃ ማውረድ ችለዋል። ሕንድ ከዘጠና አምስት ቀን እስከ አንድ መቶ አስር ቀን ይወስድባት የነበረውን ወደ ሰላሳ ቀን መቀነስ መቻሏን ገልጸዋል። እንዲሁም ችሊ ይህን ሲስተም ተጠቅማ ግዥ መፈጸም ከጀመረች በኋላ ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በመንግሥት ግዥ እርካታ ማግኘቱን ገልጸዋል። ኢትዮጵያም ይህን ሥርዓት መጠቀም ብትጀምር በርካታ ገንዘብ ማትረፍ ትችላለች።
የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘዴዎችን በመጠቀም ግዥ ፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ጨረታ በአየር ላይ እንዲያወጡ የሚያደርግና ተጫራቾችም በኦንላይን ዘዴ ተጠቅመው እንዲጫረቱ የሚያደርግ ዘዴ ነው። መስሪያ ቤቶች ጨረታ በኦንላይን ካወጡ በኋላ የመጫረቻ ሰነዳቸውን፣ ቅሬታ ካላቸው ቅሬታቸውን በሲስተሙ ማስገባት ይችላሉ። ኦዲት የሚያደርጉ ተቆጣጣሪ አካላትም በሥርዓቱ ውስጥ ገብተው ኦዲት ማድረግ እንደሚችሉ አቶ ታደሰ ገልጸዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም