አዲስ አበባ፡- የቢክ ኢትዮጵያ በግብርና ቴክኖሎጂና በግብርና ንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎችን ለማገዝ የአምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ። ፕሮጀክቱ እንደ አገር ለተያዘው የሥራ ፈጠራ እቅድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ፕሮጀክቱ ይፋ በሆነበት ወቅት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን እንደገለጹት፤ የቢክ ኢትዮጵያ ድጋፍ በአገራችን በግብርናው ዘርፍ እንደ አገር ለተያዘው የሥራ ፈጠራ እቅድ የሚኖረው ድጋፍ ከፍተኛ ነው።
አቶ ንጉሡ እንዳሉት ፕሮጀክቱ፤ ለአራት አመት የሚቆይ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ ማድረጉ በሁሉም ዘርፍ የሥራ አጥነትን ቁጥር ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የአውሮፓ ሕብረት ዘርፉን ለመደገፍ ላደረገው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
እንደ አቶ ንጉሡ ገለጻ፤ በተለያዩ ምክንያቶች በኢትዮጵያ ያለው የሥራ አጥነት መጠን ከፍተኛ ነው። ይህን ከፍተኛ የሥራ አጥነት ሁኔታን በተጨባጭ ለመለወጥ እንደ አገር የሥራ ክፍተቶችን በማስተካከል ለሁለት ሚሊዮን አዲስ ገቢዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው። ይህ በመንግሥት አቅም ውስንነት የሚሳካ ባለመሆኑ የአጋር፣ የግሉ ዘርፎችና ሌሎች አካላት የነቃ ተሳትፎ ያስፈልጋል።
የቢክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ክርስቲያን ቤክ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚውል ከአውሮፓ ሕብረት የተገኘ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዩሮ ተመድቧል። በግብርና ቴክኖሎጂና በግብርና ንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎችን ለማገዝ እንዲውል በማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
በዚህ ፕሮጀክት አራት የተለያዩ ሥራዎች ይሠራል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የአቅም ግንባታ፣ በግብርና ቴክኖሎጂና በግብርና ንግድ ዘርፎች የተሰማሩ የሥራ ፈጣሪዎችን ማቋቋም፣ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግና የግንኙነት መድረኮችን መፍጠር መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር አስራ አምስት የሥራ ሃሳብ ፈጣሪዎችን ወደ ቢዝነስ እንኪዩቤተሮች፣ ለሰባት መቶ ወጣቶች የሚሆን የመነሻ ካፒታል፣ ለሁለት ሺህ ስምንት መቶ ስልሳ አነስተኛና መካከለኛ ሰልጣኞች ስልጠና መስጠትና ለሁለት ሺህ አምስት መቶ ሰዎች አዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር የፕሮጀክቱ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
የቢክ ኢትዮጵያ ቡድን መሪ ኦሊቨር ፔትዞይት በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ በሥራ ፈጠራ ዘርፍ የሚውል ሲሆን፣ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአውሮፓ ሕብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በጋራ በመሆን የሚተገበር ነው ብለዋል።
ይፋ የተደረገው የቢክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት በአውሮፓ ሕብረት ድጋፍ የተገኘ ሲሆን የተመደበው አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዩሮ አቅም የሌላቸውን ሥራ ፈጣሪዎችን የፈጠራ ሥራቸውን እውን በማድረግ የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሳድጉ ያግዛቸዋል ብለዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓም