አዲስ አበባ፡- በ2014 በጀት ዓመት ጉዳት የደረሰባቸው ውሃማ አካላት እንዲያገግሙ ለማስቻል የተሠሩ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፣ በተለይም ቀደም ሲል በእንቦጭና በኬሚካል ጉዳት የደረሰባቸው ሐይቆች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን ለመቀልበስ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ ሲከናወን ቆይቷል፡፡
በተሠሩ ሥራዎችም ምንም እንኳን አረሞችን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባይቻልም በጣና እና ዝዋይ ሐይቆች ላይ ከማኅበረሰቡ ጋር በተደረገ ርብርብ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
በጣና ሐይቅ ላይ ይነሳ የነበረው የእንቦጭ ጉዳይ በአካባቢው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በባለቤትነት መንፈስ ከአረም የማላቀቅ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዝዋይ ሐይቅ ላይም የአካባቢውን ባለሀብቶች በማስተባበር አብዛኛውን የውሃውን አካል ከብክለት የማፅዳት እና ከእንቦጭ ነፃ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
መጤ አረሞች እና እምቦጭን የመሳሰሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ሐይቆች ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን ሲያደርሱ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ ጣና ሐይቅ በእምቦጭ ምክንያት ለረጅም ጊዜ ሲጎዳ መቆየቱም የማይዘነጋ ነው ብለዋል፡፡
ጣና ላይ በተደረገው እንቦጭን የመከላከል ርብርብ አካባቢው የእኔ ነው ብሎ የሚሠራ ራሱን የቻለ ተቋም መፍጠር ተችሏል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አብዛኛው የሚኒስቴሩ ሥራም ይህንን የተፈጠረ ተቋም በሃሳብና በተለያዩ ነገሮች የመደገፍ ሥራ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ ከአቅም በላይ እየሆነ የመጣው የዝዋይ ሐይቅ ጉዳት ደርሶበታል ያሉት ሚኒስትሩ የቆቃና የዓባያ ሐይቆችም በመጤ አረሞች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡
የዝዋይ ሐይቅ ከከተማ አስተዳደሩ እና ከወረዳው እንዲሁም ከአካባቢው በተውጣጡ ማኅበረሰቦች በተሠራ ሥራ ጥሩ የሚባል ውጤት ተገኝቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ዘርፍ የሠሩ ባሀብቶችን ዕውቅና በመስጠት ለወደፊቱም ተመሳሳይ ሥራዎች እንዲሠሩ መሠረት ተጥሏል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የ2014 በጀት ዓመት በሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው ውሃማ አካላት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ትምህርት የተገኘበትና ዝግጅት የተደረገበት ዓመት ነውም ብለዋል፡፡
በዋናነት በትኩረት ሲሠራ የቆየው የውሃማ አካላት ደህንነት ጥበቃ ላይ እንደሆነ የገለፁት ሚኒስትሩ፤ በቀጣይም ውሃማ አካላት ላይ ብክለት እንዳይኖርና ብክለት ሲኖርም ብክለቱ የሚያደርሰው ጉዳት የሚቀንስበትን መንገድ ማመቻቸት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ገልፀዋል፡፡
በተለያዩ ውሃማ አካላት ላይ የተፈጠሩ እምቦጭን የመሳሰሉ አረሞችን በተለይ በሰው ኃይል ለማስወገድ የማይቻልባቸው እንዳሉ ያስታወቁት ሚኒስትሩ፣ ለአብነትም አዞን የመሳሰሉ እንስሳት በውሃማ አካባቢዎቹ መኖር በሰው አማካኝነት ለማፅዳት አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀነ 2015 ዓም