– በሦስት ወራት ከ1 ሺህ 600 በላይ የሳይበር ጥቃቶች ተፈጽመዋል
አዲስ አበባ፡- በ2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች ከ2012 ዓ.ም ከተደረጉ የሳይበር ጥቃቶች ጋር ሲነፃፀሩ የስምንት እጥፍ ጭማሪ ማሳየታቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለፀ፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሶሎሞን ሶካ እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች በእጅጉ ጨምረዋል፡፡ ይህም በንፅፅር ሲታይ በ2014 ዓ.ም የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች ከ2012 ዓ.ም የሳይበር ጥቃቶች ጋር ሲነፃፀር በስምንት እጥፍ ከ2013 ዓ.ም የሳይብር ጥቃት ደግሞ በሦስት እጥፍ ከፍ ብሏል፡፡
እንደ አቶ ሶሎሞን ገለፃ፤ በሦስት ዓመታት ውስጥ በተለይ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጦርነት ጋር በተያያዘ በሚመስል ሁኔታ በአገሪቱ የሳይበር ጥቃት ሙከራ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ በ2012 ዓ.ም አጠቃላይ የተሞከረው የሳይበር ጥቃት 1 ሺህ 80 ሲሆን ይህ ቁጥር በ2013 ዓ.ም ወደ 2 ሺህ 800 ከፍ ብሏል። የ2014 ዓ.ም አጠቃላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራ ደግሞ 8 ሺህ 900 ደርሷል፡፡
የ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶች ቁጥር 1 ሺህ 613 መድረሳቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የተደረጉ ጥቃቶችም አብዛኞቹ ያነጣጠሩት በፋይናንስ ተቋማት ላይ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
የሳይበር ጥቃቶችን 97 በመቶ ያህል መከላከል መቻሉን ያነሱት አቶ ሶሎሞን፤ ሆኖም በ2014 ዓ.ም የበጀት ዓመት በኢትዮጵያ በተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ኪሳራን ማስቀረት ቢቻልም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብሮችን አገሪቱ እንዳጣችም አክለው ገልጸዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሳይበር ጥቃት ማደግ ምክንያት ከሆኑት መካከል የሰው ልጆች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ግንዛቤ ማነስና የቴክኖሎጂ ጥገኝነት ሆኖ እንደሚገኝ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህን በመረዳትም አስተዳደሩ የአገርን የሳይበር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የአገሪቱን ቴክኖሎጂ ባለቤትነት ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማሳደግና የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ባለቤትነት ማረጋገጥ አገሪቱ ወደ ዲጂታላይዜሽን ለምታደርገው ጉዞ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ፣ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታላይዜሽን የምታደርገው ሽግግር ለአገሪቱ ሁሉን አቀፍ ልማት የሚኖረው ሚና የሚያጠያይቅ ባይሆንም የዲጂታል ሽግግሩን የሚመጥን የሳይበር ደህንነት ሥራዎች መሥራት ካልተቻለ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ብለዋል፡፡
ለዚህም እንደ ማሳያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሳይበር ምህዳሩን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር መጨመርን ተከትሎ በግለሰቦች እና ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች ያደረሱትን ኪሳራ ማንሳት በቂ እንደሆነም አቶ ሶሎሞን ጠቁመዋል።
ውብሸት ሰንደቁ
ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓም