አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያደገ ከመጣው የደንበኞች ፍላጎት ጋር ተያይዞ ተጨማሪ 36 አውሮፕላኖችን ለማስገባት ትዕዛዝ መስጠቱን አስታወቀ::
አየር መንገዱ የመጀመሪያው ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ በረራ የጀመረበት 10ኛ ዓመት አክብሯል። በበዓሉ የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄ፣ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የቦይንግ ኩባንያ ተወካዮች እና ሌሎች አካላት በተገኙበት ተከብሯል::
በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደገለፁት፤ አየር መንገዱ እያደገ ከመጣው የደንበኞች ፍላጎት ጋር ተያይዞ ሁለት ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላንን ጨምሮ የተለያየ ሞዴል ያላቸውን ሠላሳ ስድስት ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ለማስገባት ትዕዛዝ ሰጥቷል ብለዋል:: ሁለቱ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚገቡም ተጠቁሟል::
አየር መንገዱ 140 አውሮፕላኖች ውስጥም 27 አውሮፕላኖች ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተጨማሪ ሁለት አውሮፕላኖች በአንድ ዓመት ውስጥ ሲገቡ የቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖችን ቁጥር 29 ያደርሳል ነው ያሉት::
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኑን ሲያስገባ ከአፍሪካ የመጀመሪያው፤ በዓለም ደግሞ ከጃፓን ቀጥሎ ሁለተኛ አየር መንገድ ነው:: ይህም አየር መንገዱ ሁልጊዜም በአየር ትራንስፖርት ውስጥ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቀዳሚዎቹ አየር መንገዶች አንዱ መሆኑን ያሳያል ሲሉ አስረድተዋል::
እንደሳቸው ገለፃ፤ በአሁኑ ሰዓት አየር መንገዱ 130 መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን የበረራ አውሮፕላኖች ቁጥርም ወደ 140 ደርሷል ነው ያሉት። የቦይንግ ኩባንያ ተወካዮች በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። አየር መንገዱ የመጀመሪያውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ነሐሴ 2012 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደሀገራችን ማስገባቱ ይታወቃል::
ፀጋዬ ጥላሁን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2015