አገርና ሕዝብን ማገልገል ክብር ነው

“አገልጋይነት ታላቅነት ነው። ክብር የሚገኘው ከማገልገል ነው። ፈጣሪን፣ አገርን፣ ሕዝብን፣ ከማገልገል ውጭ ምን ሕይወት አለ። ሁላችንም በአንድ ቦታ አገልጋዮች በሌላም ቦታ ተገልጋዮች ነን። አገልጋይነት የሁላችንም ባህልና ሥነ ምግባር ከሆነ የትኛውም መስሪያ ቤት መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ይሆናል። የሆኑ አካላት ብቻ እንዲያገለግሉን ከጠበቅን ግን በአንዳንድ ቦታዎች ተፈልጎ የሚገኝ ብርቅ ሀብት ይሆንብናል። በቂና ብቁ አገልጋዮች የሌሏት አገር፣ በዕድገት መራቅና መምጠቅ ይቸግራታል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ናቸው።

አዎ ለገባው ወይም ለተገነዘበው ሰው አገልጋይነት ውድና ትልቅ ስጦታ ነው። ሰው በተሰጠው የስራ ድርሻ ሁሉ ሰዎችን ማገልገል መቻል አለበት። ይህንን በማድረጉ ደግሞ ከሚያገኘው ወይም ከሚሰማው የመንፈስ እርካታ በተጨማሪ አገሩ ትኮራበታለች፤ ህዝቡ በማገልገሉም የሚሰጠው ምስጋና በቀላሉ የሚታይም አይደለም።

የዛሬ የሕይወት ገጽታ አምድ እንግዳችን አገርና ህዝብን ከማገልገል በላይ ክብር የለም ይሉናል አቶ ሰለሞን ተስፋዬ።

አቶ ሰለሞን ተስፋዬ ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ መስፍን ሐረር መንገድ ወይም አዲሱ ገበያ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም በዳግማዊ ሚኒሊክ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መከታተላቸውን ይናገራሉ።

“……አባቴ በልጅነቴ ነው የሞተብኝ እኔም ያደኩት ከእናቴ እናት ከአያቴ ጋር ነበር፤ ያው የአያት ልጅ እንደሚባለው በሚችሉት አቅም በጥሩ ሁኔታ አሳድገውኛል። ትምህርቴንም በአግባቡ እንድማር አግዘውኛል። ሆኖም እኔም ትምህርቴን ሳልጨርስ አያቴ የህይወት ጥሪ ደርሷቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ከእናቴ ጋር መኖር ጀመርኩ” ይላሉ።

አቶ ሰለሞን ረዳት የሌላቸው እናታቸው ጋር ሲሄዱ ዝም ብለው ተማሪ ሆነው ብቻ አይደለም የቀጠሉት ይልቁንም በእናት ከሚገናኙት ወንድማቸው ጋር በመሆን የተለያዩ ስራዎችን በመስራት እናታቸውን እየደገፉ ትምህርታቸውንም እየተከታተሉ ለትንሽ ጊዜም አጎታቸው ጋር እየተቀመጡ ኑሮን ተያያዙት እንጂ።

እየሰሩ መማር ለአቶ ሰለሞን ከባድ ቢሆንም በትምህርታቸው ግን ቀልድን አያውቁም ነበርና ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ በደረጃም እየወጡ ነበር ሲማሩ የነበሩት።”……የትምህርት መጀመሪያዬ የቄስ ትምህርት ስለነበር ዘመናዊ ትምህርት ቤት ስገባ ብዙ አልተቸገርኩም፤ እንደውም ብዙ አገዘኝ እንጂ፤ በዚህ ምክንይት ደግሞ አንደኛና ሁለተኛ ነበር የምወጣው በመምህራኖቼም የምወደድ ተማሪ ነበርኩ” በማለት ስለራሳቸው ይናገራሉ።

በዚህ ሁኔታ እየተማሩ 12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ የግድ ከእናታቸው ጋር የኑሮን ጫና መተጋገዝ ስለነበረባቸው እሳቸው እየሰሩ መማሩን አላቋረጡም። በዚህ ላይ ደግሞ የደርግ መንግስት ቀይ ሽብር በሚል ምክንያት ብዙ ወጣቶችን ይገድል የነበረበት ጊዜ ስለነበር አስፈሪ ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ።

“……በወቅቱ የኑሮ ችግር ብቻ ሳይሆን ይገጥመን የነበረው ወታደራዊው ደርግ ወጣቶችን በገፍ እያፈሰ ጦር ሜዳ የሚልክበት እንዲሁም ቀይ ሽብር በማለት የሚረሽንበት ጊዜ ነበር። ብዙ ጓደኞቼም አገር ጥለው ከመሰደድ ጀምሮ ሕይወታቸውንም ያጡ ነበሩ፤ እኔም ገና የ12ተኛ ክፍል ተማሪ ብሆንም ከችግሩ ለማምለጥ ስል ብቻ በተማሪነት እድሜዬ ስራ ለዚያውም የመንግስት ስራን ማፈላለግ ጀመርኩ” ይላሉ።

አቶ ሰለሞን የመንግስት ሰራተኝነትን የሚገልጽ መታወቂያ ይዘው ወቅቱን ለማምለጥ ብዙ ጥረት በማድረግ በመጨረሻም በ1971 ዓ.ም አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት የሚባለው መስሪያ ቤት በጸሀፊነት የስራ መደብ በ55 ብር የወር ደመወዝ መቀጠራቸውን ይናገራሉ።

“…..ያኔ የመንግስት ሰራተኝነት መታወቂያ የያዘ ሰው ይከበራል፤ ኸረ እሱ ስራ አለው ይባልለታል፤ በተመደብኩበት የስራ መስክ ላይ እጅግ ደስተኛ ሆኜ እሰራ ስለነበር እንዲሁም የማሳየውም የስራ ተነሳሽነት ጥሩ ስለሆነ በዓመቱ የደመወዝ እድገት አግኝቼ ነበር” ይላሉ።

አሁን የ 12ተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀዋል እናም ስራ መቀየር ፈለጉና ስራ ሲያፈላልጉ በቀድሞ አጠራሩ ጭማድ በኋላም ኢጭማኮ የሚባለው መስሪያ ቤት ተወዳደርው በማለፋቸው በጸሀፊነት የስራ መደብ ከፍ ባለ ደመወዝ ተቀጠሩ፤ አሁን የስራ አካባቢው መቀየሩ የደመወዝ እድገቱ አስደሰታቸው እናታቸውንም በደንብ ለመደገፍ ስላስቻላቸው በሞራል ስራቸውን መስራት ቀጠሉ።

“……..ከዛን ጊዜ ጀምሮ ለእኔ አገርና ህዝብን እንደማገልገል ትልቅ ነገር አለ ብዬ አላምንም ነበርና ስራዬን ላቅ ባለ ትጋት መስራት ከትልቅ ትንሹ ጋር በተግባቦት መዋል ደግሞ የሕይወት መርሄ ስለነበር በስራ ላይ የከፋ ችግር ሳይገጥመኝ ለ 17 ዓመታት ያህል አገለገልኩ” ይላሉ።

ከጸሀፊነት ጀምረው እስከ ሂሳብ ሹምነት ድረስ ያሉ የስራ ኃላፊነቶችን ሁሉ በብቃትና በጥሩ የስራ ስነስርዓት የከወኑት አቶ ሰለሞን እግረ መንገዳቸውን የከፍተኛ ትምህርታቸውን እየተማሩ ዲግሪያቸውን ለመያዝ በቁ።

ሕይወት ሁሌም አዲስ ነገር ትፈልጋለች መኖር ካለ ለውጥ ይናፍቃል ለውጡ ደግሞ በደረጃም በደመወዝም ሲሆን ሙሉ ይሆናል የሚሉት አቶ ሰለሞን እሳቸውም 17 ዓመት ከሰሩበት ኢጭማኮ ለውጥን በመፈለግ ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን በሂሳብና በጀት የስራ መደብ ላይ ለመስራት ተቀጠሩ።

በድንገት እናታቸውን ለመርዳት እየረዱም ለመማር የገቡበት የስራው ዓለም እንዲህ እንዲህ እያለ እዚ ሲያደርሳቸው አቶ ሰለሞንም ለስራ የሚሰጡት ዋጋ ከፍ እያለ በኑሯቸውም ለውጥ እያመጡ ህዝብና አገርን የማገልገል ጽኑ ፍላጎታቸው እያደር እየዳበረ ሲመጣም ይሰማቸው ነበር። በዚህም ምክንያትም በፌደራል ከተሞች ልማት ኢንስቲትዩት በኦዲት መምሪያ ኃላፊነት። በስራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር በበጀት ዝግጅትና ክትትል ዋና ክፍል ኃላፊነት። በፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በኦዲት መምሪያ ኃላፊነት ። በጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊነት የስራ መደቦች ላይ እየተመደቡ ተቋምንም አገርንም የሚጠቅም አስተዋጽዖ አበርክተዋል።

አቶ ሰለሞን ይህ ማህበራዊ ተሳትፏቸው ብሎም በስራ ላይ የሚያሳዩት ትጋትና የስራ ፍቅር በአካባቢያቸው ነዋሪዎች ዘንድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤትን እንዲቀላቀሉ ምክንይት ሆናቸው።

“…..ህዝብን ማገልገል መታደል ነው እኔም በሰፈሬ አካባቢ የማሳየው ትጋት በበጎ ፍቃድ የምሰራቸው ስራዎች እንዲሁም በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሰማርቼ ስሰራ በነበረኝ የስራ አፈጻጸም ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ገብቼ ድምጽ እንድሆናቸው ጠየቁኝ እኔም ፍቃደኛ ሆኜ ተወዳድሬ በማሸነፍ በ2000 ዓ.ም ምክር ቤቱን በመቀላቀል ለአምስት ዓመታት ያህል የመረጠኝን ህዝብ ሳገለግል ቆየሁ “በማለት ይናገራሉ።

አቶ ሰለሞን የአምስት ዓመት የምክር ቤቱን አገልግሎታቸውን ቢጨርሱም ህዝቡ ግን ይሻለናል በማለቱ ምክንያት በ2005 ዓ.ም እንደገና ተመርጠው ገቡ።

ሆኖም አቶ ሰለሞን ከልጅነታቸው ጀምሮ ህልማቸው የነበረው ነገር አገልጋይነት የሚለው ስሜት ነውና ብዙ መስሪያ ቤቶች እየተዘዋወሩ ቢሰሩም ያን ያህል ግን በሚፈልጉት ልክ ማገልገል የቻሉ አይመስላቸውም። አቶ ሰለሞን ከመንግስት የስራ ኃላፊነታቸው ባሻገር ያለቻቸውን ትርፍ ሰዓት በአግባቡ በመጠቀም በሚኖሩበት አካባቢ ያሉ የህብረት ስራዎችን በመስራት ማህበረሰብን ማገልገል የተመሰከረላቸው ሚናቸውም ነው። ነገር ግን ከትልቁ ህዝብን የማገልገል ህልማቸው እንዳይቀሩ አንድ ጥሩ አጋጣሚ ተፈጠረላቸው፤ እሱም በምክር ቤት አባል እያሉ የራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ። አቶ ሰለሞን ይህንን እድል በቀላል አላዩትም ይልቁንም አገርና ህዝብ የሚማረርበትን የመንግስት የህክምና ተቋም አገልግሎት ላቅ ወዳለ ደረጃ አሸጋግረው ተምሳሌት ማድረግን ተመኙ እንጂ ።

ኃላፊነታቸውን ተቀብለውም ከፍ ባለ የስራ ትጋትና ያለመሰልቸት ብዙ ስራዎችን ማከናወን ጀመሩ፤ በዚህም በሆስፒታሉ ላይ የሚጠብቁትን አይነት ለውጥም የማየት እድሉን እያገኙ ሲመጡ ይበልጥ ለስራው ተነሳሱ። አሁን ሃሳባቸውም ስራቸውም ሆስፒታሉን መለወጥ ላይ ብቻ ሆነ፤ በዚህም ስራቸው ከህክምና ባለሙያዎች እስከ ታካሚዎች ድረስ ጥሩ ግንኙነትን በመፍጠር ችግሮችን እለት በእለት እንዲፈቱና እልባት እንዲያገኙ በማድረግ የማይናቅ ሚናን ተወጡ።

“……ራስ ደስታ ሆስፒታል በስራ አስኪያጅነት ስመደብ በጣም ነበር ደስ ያለኝ። በውስጤ ያለውን የማገልገል ፍላጎትና ፍቅር ላምወጣበት የምችልበት ብቸኛ ተቋምም እንደሚሆን አስብ ነበር። በዚህም ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ በሆስፒታሉ ውስጥ ጎደሉ የምላቸውን ነገሮች ሁሉ ለማሟላት ከፍ ያለ ጥረት ሳደርግ ህዝቡ ምን ዓይነት ህክምና አገኘ፤ ምን ጎደለው፤ የሚለውን ስከታተል ችግር በተፈጠረበት አካባቢም የመድፈን ስራ ስሰራ ነበር የምውለው በዚህም በጣም ደስተኛ ነበርኩ” በማለት የሆስፒታል ትዝታቸውን ይናገራሉ።

“…..ራስ ደስታ ሆስፒታል በከተማው ካሉ አጠቃላይ ሆስፒታሎች አንዱና ትልቁ ነው። ሆስፒታሉ ከገባሁ በኋላ ብዙ ስራ ነበር የጠበቀኝ። በተለይም ወቅቱ የመሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ (ቢፒአር) የተካሄደበት ስለነበር ሰራተኛውን ማረጋጋት ስራዎችን ለተገቢው ሰው መስጠት ይገባ ነበርና ይህንን ሁሉ ማቀናጀቱ ጊዜ ከመውሰዱም በላይ ስራውን ከባድ አድርጎት ነበር” ይላሉ።

ሆስፒታሉ ውስጥ ዶክተሮች ነርሶት እንዲሁም የአስተዳደር ሰራተኞች ስለሆኑ ያሉት እነዚህን በአንድ አቀናጅቶ መምራቱ ደግሞ ምናልባትም እውቀት የስራ ልምድ እንዲሁም ከፍ ያለ ተነሳሽነትን የሚጠየቅ ነበርና አቶ ሰለሞን እነዚህ አስታርቀው ሰውና ስራን በእኩል ለመምራት ከፍ ያለ ጥረትንም አድርገዋል።

“……ልክ ጠዋት በስራ ገበታዬ ላይ ስገኝ የመጀመሪያ የማደርገው ታካሚዎች ጋር ሄዶ መጎብኘት ምን ዓይነት አገልግሎት አገኛችሁ? አዳራችሁ እንዴት ነበር? ምን ዓይነት ችግር ገጠማችሁ? አሁን ምን እንዲደረግላችሁ ትፈልጋላችሁ? የሚያስፈልገውን መድሃኒት አግኝታችኋል ወይ? ዶክተሮችና ነርሶች ጎብኝተዋል ወይ? የሚለውን በመጠየቅ ምልሻቸው ማስታወሻዬ ላይ መዝግቤ ቢሮ በመግባት በተሰጡት አስተያየቶች ላይ ሜዲካል ዳይሬክተሩን ጠርቼ እናወራበታለን፤ እነዚህ በዚህ ይሻሻሉ የሚል የስራ መመሪያ እሰጣለሁ፤ በዚህ ሁኔታ ስናልፍ ደግሞ ችግሮች እየቀነሱ ስራዎች እየተስተካከሉ ታካሚዎች በሚያገኙት አገልግሎት እየረኩ ዶክተሮችና ነርሶችም በስራቸው ደስተኛ እየሆኑ ሄዱ፤ በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ የስራ ክፍሎችም በዚህ ሁኔታ በመደራጀታቸው አሁን ለተጠያቂነት ራሱ የሚመች ምህዳር ተፈጠረ “ በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።

የግል ህክምና መስጫ ማዕከል አጀማመር

በመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ ከስራ ሰዓት ውጪ የግል ህክምና መስጫ ተቋማት እንዲከፈቱ የሚያዘው መመሪያ ወጣ ። የዚህ መመሪያ መዘጋጀት ዋና አላማው ሀኪሞች በመንግስት ሆስፒታል ተቀጥረው ሲሰሩ የሚከፈላቸው ክፍያ በቂ ስላይደለ ከስራ ገበታቸው ላይ የመጥፋት አንዳንዴም ጨርሶ የመቅረት ሁኔታ ስለሚያሳዩ ያንን ነገር ለማስቀረት ነበር። አንድ ታካሚ ሆስፒታል መጥቶ በመረጠው ሐኪም እንዲታከም ማስቻል ሌላው ነው። ሆስፒታሎች በዚህ ሁኔታ አገልግሎት ሰጥተው በሚገኘው ገቢ ሆስፒታሉን ማስፋፋት የሚጎሉትን ነገሮች ማሟላት ከአላማዎቹ የሚጠቀሱ ናቸው።

እነዚህን ዓላማዎች ያነገበው የግል ህክምና መስጫ ማዕከል ምስረታ አስፈሪ ሆነ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ጤና ቢሮ ስርም ሆነ በፌደራል ጤና ሚኒስቴር የሚመሩ ሆስፒታሎች አገልግሎቱን ማስጀመር ፈሩ፤ መመሪያውን ታቅፎ ተፋጦ መቀመጥ እጣ ፋንታው ሆነ።

“…….ይህንን የህክምና ማዕከል ምስረታ ሁሉም ሆስፒታሎች መጀመሩን ቢያምኑበትም ደፍሮ ወደ ስራ ማስገባት ላይ ግን ከፍ ያለ ፍርሃት ነገሰ፤ በዚህ መካከልም የሚጀምረው አጥቶ መመሪያው ከወጣ በኋላ እንኳን ወራቶች ተቆጠሩ፤ እኔ ግን ማኔጅመንቱን ሰብስቤ እጃችን ላይ መመሪያ ደንብ አለ ወደተግባር ለመግባት የያዘን ነገር ምንድነው? ስል ጠየኳቸው፤ የእነሱ ምላሽ ተሞክሮ ከየት እናመጣለን የሚል ነበር “ ይላሉ።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን  ኅዳር 11/ 2015 ዓ.ም

Recommended For You