ባዮ-ቴክኖሎጂ እና ግብርና…

በሁለቱ መካከል ስላለውም ሆነ ስለሚኖረው ትስስር ከውዝግብ ባለፈ አንድ ድምዳሜ ላይ አልተደረሰም። በጉዳዩ ላይ ቢያንስ ሁለት ጎራዎች ሊታረቅ እንኳን የማይችል በሚመስል መልኩ ሲፋለሙ ነው የሚታየው፤ የሚሰማውም ንትርክ እንደዛው ነው። አንደኛው ጎራ ”በአሁኑ ዘመን ያለ ባዮቴክኖሎጂ የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማነት መጠበቅ የዋህነት ነው” ሲል፣ ሌላኛው ጎራ በበኩሉ ይህንን አስተሳሰብ ራሱን ”የዋህነት” ይለዋል። ምክንያቱንም ”ባዮቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ውጤታማ መሆን በሰው ልጅ ሕይወትና ጤና ላይ መቀለድ ነው” ሲል ያቀርባል። ይህ አይነቱ ውዝግብ በአንድ ጋዜጣና ጋዜጠኛ የሚፈታ ባለመሆኑ ጉዳዩን ለባለ ሙያዎቹ ትተን እየሆነ፣ እየተደረገ ባለው ላይ እንነጋገር። አስቀድመን ግን የፅንሰ ሀሳቡን ባለቤትና ዘመን እንግለፅ፤ ውለታም ነውና እናስታውሳቸው።

”ባዮቴክኖሎጂ” የሚለው ፅንሰ ሀሳብ በ1919 ኤሬኪ (Ereky, Karl) የተባሉ ተመራማሪ ሀንጋሪ ውስጥ ባዘጋጁትና በርሊን አሳትመው በብዙ ሺህ ኮፒዎች በተቸበቸበውና በ1921 ወደ ደች ቋንቋ በተተረጎመው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ባተኮረው መጽሐፋቸው አማካኝነት ለአደባባይ የበቃና ወደ ተግባርም የገባ ነው፡፡ ጸሐፊውም አብዮት አስነስተሃል ተብለው ለእስር የተዳረጉ፣ እዛው እስር ቤትም እያሉ (ከ12 ዓመታት የእስር ቆይታ በኋላ) ጁን 17 ቀን 1952፣ በ74 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ለመግቢያ ይህል ይሄን ካልን ዘንድ ወደ ጉዳያችን እንመለስ።

በአሁኑ ዘመን እየተከናወነ ያለው የግብርናው ዘርፍ እንቅስቃሴ በበርካታ ዘርፎች እየተደገፈ ሲከናወን ነው የሚታየው። የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ውጤታማ ለመሆን እንደ ድሮው ማረሻና ሞፈር ብቻ በቂ ሆነው አልተገኙም። ይህ በተለይ ባደጉት ሀገራት የሚታሰብ አይደለምና ሙሉ ለሙሉ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ግብርና ነው እየተካሄደ ያለው። ከእነዚህም አንዱ አምስት ሰፋፊ ዘርፎች (ሰብዓዊ፣ አካባቢያዊ፣ ኢንዱስትሪያዊ፤ እንዲሁም እንስሳትን እና እፅዋትን የተመለከቱ) ያሉት ባዮቴክኖሎጂ ነው።

ይህ ሳይንሳዊ የምርምር ዘርፍ በግብርናው መስክ ሥራ ላይ የማዋል ጉዳይ ዘፈቀዳዊ ሳይሆን ታስቦበትና አስፈላጊው ደንብና መመሪያ ተዘጋጅቶለት የሚተገበር ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ ዘርፉ ለሚገለገልባቸው ሙያዊ መዝገበ ቃላት ሳይቀር የተዘጋጀለት መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም የአሜሪካውያኑን Agricultural Biotechnology Glossary በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።

ከ1970ዎቹ ጀምሮ በፍጥነት እየገሰገሰና በስፋት ሥራ ላይ እየዋለ ባለባት ሕንድ ከታች እስከ ላይኛው የትምህርት ተቋም ድረስ በትምህርትና ጥናት መስክነት ይሰጣል፡፡ የውጭ ተማሪዎችም በአገሪቱ ነፃ የትምህርት እድል እየተጠቀሙ ዘርፉን በማጥናት በ“ስፔሻላይዜሽን” ይመረቁበታል። ጉዳዩ እዚህ እንደምንፅፈው ቀላል አይደለምና፤ እያንዳንዱን ሰው፣ እንስሳ፣ እፅዋት፣ አዝርዕት፣ አካባቢ … ይመለከታልና እኛም አገር ወደ ፊት በኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና መሰል ተቋማት አማካኝነት ብዙ ይሠራል ብለን እንጠብቃለን።

ባደጉት ሀገራት ባዮቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ከዋለ ትንሽ ሰንበት ያለ ሲሆን፣ አፍሪካን በመሳሰሉና በማደግ ላይ ባሉ አገራት ቴክኖሎጂው ገና በመግባትና በትውውቅ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትንሽ ቀደም ባሉትና ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ባደረጉ ታዳጊ አገራት ላይ ግን ውጤት እየታየ ነው እየተባለ ሲሆን፣ ሁሉም ሀገራት ይህንኑ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ካሉባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊላቀቁ ይገባል የሚለው ምክረ ሀሳብ እያየለ በመምጣት ላይ ነው።

ከእነዚህ አገራት መካከል አንዷ ሀገራችን ስትሆን፤ ቴክኖሎጂውን በትውውቅ ደረጃ ከመጠቀም አልፋ ወደ እለት ተእለት ተግባራት ውስጥ ያስገባችው ይመስላል። ለዚህ ማሳያው ደግሞ በ”የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን” አማካኝነት ተዘጋጅተው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቀውና (BIODIVERSITY REGULATORY LEGAL FRAMWORKS OF ETHIOPIA, Addis Ababa 2022 በሚል ርዕስ) በአንድ ተሰንደው በOFAB Ethiopia (Open Forum on Agricultural Biotechnology) አማካኝነት ለባለ ድርሻ አካላት የተሰራጩት ፖሊሲዎች፣ ደንብና መመሪያዎች ናቸው።

ሰነዶቹ በሁለት ቋንቋዎች (አማርኛና እንግሊዝኛ) የተዘጋጁ ሲሆን፣ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን (በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሙያዎች፣ ባለ ሀብቶች፣ ተጠቃሚዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎች … ወዘተ) ያስተናገዱ፤ ስለ ጉዳዩ ግንዛቤን የሚያስጨብጡና በዘርፉ ለሚሠማራ አካል በራስ የመተማመን አቅምን የሚፈጥሩ ስለ መሆናቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲነገሩ ይሰማል።

በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶችም ሆኑ የዓይንና የብእር ምስክሮች እንደሚያስረዱት አፍሪካን ለመሳሰሉና በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ፤ በከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እየተጥለቀለቁና የእለት ጉርስ ለቸገራቸው፤ ነገር ግን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብትና እሴት ለተሞሉ አህጉራት ባዮቴክኖሎጂን የመጠቀም ጉዳይ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው። በልቶ ማደር ካስፈለገ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ካስፈለገ፣ ምርትን ለውጪ ገበያ ማቅረብና ምንዛሪን ማስገባት ካስፈለገ፣ የአገርን ጂዲፒ ማሳደግ ካስፈለገ …. ካስፈለገ … በግብርናው ዘርፍ ባዮቴክኖሎጂን መጠቀም የግድ እንጂ ለድርድር የሚቀርብ፤ “እንደ አስፈላጊነቱ …” የሚባል ጉዳይ አይደለም።

ከላይ በጠቀስነው የሀገራችን ሰነድም ላይ የሰፈረው የሚነግረን ይህንኑ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ኃይሉ ዳዲ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቆይታ የሚያሰምሩበት ይህንኑ ነው።

ከላይ የጠቀስነው የአሜሪካው መዝገበ ቃላት የግብርና ባዮቴክኖሎጂን A range of tools, including traditional breeding techniques, that alter living organisms, or parts of organisms, to make or modify products; improve plants or animals; or develop microorganisms for specific agricultural uses. Modern biotechnology today includes the tools of genetic engineering. በማለት የሚበይነው ሲሆን፤ ይህ ብያኔም በተለያዩ መንገዶች ከላይ በጠቀስነው የአዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ስብስብ ሰነድ ውስጥም ተጠቅሶ ይገኛል። genetic engineering የሚለው ”ዘረ መል” መሆኑ በማብራሪያ ተደግፎ፤ የአሠራር ብያኔ ተቀምጦለት ቀርቧል።

ወደ አፍሪካ እንመለስ፤ በአሁኑ ሰዓት ባዮቴክኖሎጂ በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ ሥራ ላይ ውሎ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። አገራትም ይህንኑ ቴክኖሎጂ እየተጠቀሙ በከፍተኛ ደረጃ እየተለወጡ እንደሚገኙ እየተነገረና እራሳቸውም ምስክርነትን እየሰጡ ይገኛሉ፤ ኢትዮጵያም አንዷ ናት። ምርታማነታቸው ከመጨመሩ የተነሳም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሀገራትም እየተረፉ እንደሚገኙም እየተናገሩ ይገኛሉ። ምርታቸውን እየላኩ ዶላሮችን እያስገቡ መሆናቸውም እንደዛው።

ሲጠቃለል፤ “አዝርዕትን፣ እንስሳትን፣ እንሰትን፣… የማላመድና ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ሥራ በ…. ተካሄደ/ተከናወነ …” ከሚለው ባለፈ ኅብረተሰቡ፣ ቢያንስ በጠቅላላ እውቀት ደረጃ የተወሰነ ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ ሊሠራ ይገባል። በሂደቱ ተሳታፊም ተጠቃሚም ይሆን ዘንድ አስቀድሞ የጋራ ግንዛቤ ሊኖረው ያስፈልጋልና ባልተቋረጠ መልኩ ሊሠራ ይገባል።

ከላይ ሀገራትን የጠቀስነውም ይህንኑ ልምዳቸውን ለማሳየት ነውና እኛም ወደ’ዛው ልናመራ የግድ ነው። ይህንን ስንል ያለ ምክንያት ሳይሆን በተጠቃሚውም ሆነ አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ዘንድ፣ ከአያያዝና አጠቃቀም (safety considerations የሚባለውን ጨምሮ) ያለው ግንዛቤ በቂ ነው የሚባልበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ቀርቶ ጭራሹንም ስለ መኖሩ የሚያሳዩ ምልክቶች ባለመኖራቸው ነውና ሊታሰብበት ይገባል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ህዳር 14/2015

Recommended For You