ሱሉልታ:- የጸረ ሙስና ትግሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከንግግር ባለፈ ተግባራዊ ርምጃን እንደሚሻ ተገለጸ። የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የጸረ-ሙስና ቀንን አክብሯል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በዓለም አቀፍ ለ19ኛ ጊዜ እና በሀገር አቀፍ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ ሙስና ቀንን “ሙስናን መታገል በተግባር” በሚል መሪ ሀሳብ ትላንት በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሁነቶች አክብሯል። ሙስና የሀገርን ኢኮኖሚ የሚገታ እንደመሆኑ ትግሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከንግግር ባለፈ ተግባራዊ ርምጃን እንደሚሻ ተመላክቷል።
የአካዳሚው የሥነምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክተር ወይዘሮ አልማዝ መኮንን ባቀረቡት ጽሑፍ፣ በኢትዮጵያ ሙስናና ብልሹ አሠራር ስር እየሰደደ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ይህ የሀገሪቱን የዕድገትና የብልጽግና ጉዞ የሚያደናቅፍ እንደሆነም አመላክተዋል።
በተገኘው መድረክ ሁሉ የሙስናን አስከፊነት፣ የሚያደርሰውን ጉዳት በመደስኮር ብቻ የመልካም አስተዳደር ችግር የሆነውን ሙስናን ማስወገድ እንደማይቻልም አስገንዝበዋል።
ከመቼውም ጊዜ በላይ የፀረ ሙስና ትግል ከንግግር ባለፈ ተግባራዊ ርምጃን ይሻል ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ባለ ድርሻ አካላት በሙሉ የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዳይሬክተሯ ከንግግር ተሻግሮ መረጃና እውቀት ላይ የተመሠረተ ተግባር ማሳየት ይገባል በማለት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን መለየት፣ ማጋለጥና ማረም፣ እንዲሁም የሥነ ምግባርና የሞራል እሴቶች ግንባታን በማጠናከር የልማትና የመልካም አስተዳደር ነቀርሳ የሆነውን ሙስና ከስር መሠረቱ ለመንቀል ሁሉም እንደየሚናው ቁርጠኛ መሆን ይገባል ሲሉ መክረዋል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ ሙስናን ለመግታት ጅምር እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም ከተሠራው ይልቅ ያልተሠራው ያመዝናል። በቀጣይ ከፍተኛ ጥረትና የተቀናጀ ርብርብ ካልተደረገ የሙስና ስጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲሄድ ዕድል ይፈጥራል።
የተቋማት የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራር ሥርዓት ዝርጋታ ክፍተት መኖር፣ ሕዝቡ በጸረ ሙስና ትግሉ በበቂ ሁኔታ አለመሳተፍ፣ የባለድርሻ ተቋማት የተቀናጀና የተደራጀ የጸረ ሙስና እርምጃ አለመውሰድና የሙሰኞችን የሥነ ምግባርና የሞራል መዛነፎች በበቂ ደረጃ አለማረም የጸረ ሙስና ትግል የሚፈለገውን ያህል ውጤት እንዳያስመዘግብ ያደረጉ ምክንያቶች እንደሆኑ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
ተቋማዊ አደረጃጀትና አሠራር ማጠናከር፣ የሥነ ምግባርና የሞራል እሴቶች ግንባታና የሙስና መከላከል ጥናትና ክትትል አሠራርን ማጠናከር የጸረ ሙስና ትግል ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ለዚህም የመንግሥት ተቋማት አመራሮች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ ቤተሰብ፣ የትምህርት ተቋማትና ማኅበራዊ ተቋማት የተጠናከረ የጸረ ሙስና ትግል በኢትዮጵያ እንዲቀጣጠል የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ምክትል ርዕሰ አካዳሚው ዶክተር ወንድዬ ለገሰ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፣ ሙስና የሀገር ነቀርሳ መሆኑን በመጥቀስ መንግሥት ይህንን ትኩረት አድርጐ እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
ዶክተር ወንድዬ ሙስናን ማጥፋት የውሳኔ ጉዳይ እንደሆነ በመጥቀስ መንግሥት ይህንን ትኩረት አድርጐ እየወሰደ ያለውን ርምጃ ሁሉም ሊደግፈውና ለተግባራዊነቱም ተባባሪ መሆን እንዳለበት አስታውቀዋል። አካዳሚው ግንዛቤ በመፍጠር የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም ገልጸዋል።
በተጠናከረ ቅንጅታዊ አሠራር ሌብነትን እና ብልሹ አሠራርን መታገል እንደሚገባም የሁነቱ ታዳሚያን ተናግረዋል።
አካዳሚው ከጸረ-ሙስና ቀን በተጨማሪ የጸረ-ጾታዊ ጥቃትና የኤች አይቪ /ኤድስ ቀንን በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሁነቶች አክብሯል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም