–የአፍሪካ ልማት ባንክ የ14 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ተፈራርሟል
አዲስ አበባ፡- ጃፓን በኢትዮጵያ በድርቅና ግጭት ለተጎዱ ወገኖች የአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር የሰብዓዊ ድጋፍ ልታደርግ መሆኑን በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ገለጸ።
በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ መረጃ እንዳመለከተው የጃፓን መንግሥት በኢትዮጵያ በድርቅና ግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ሰብዓዊ ድጋፍ ሊያደርግ ነው። ድጋፉም በአማራ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ትግራይ እና ሶማሌ ክልሎች በሚገኙ የጉዳቱ ተጋላጭ ወገኖች የሚሰጥ ነው።
ከጃፓን መንግሥት በሚገኘው ዕርዳታ፤ የምግብ ዋስትናና ደኅንነትን ለማረጋገጥ፣ እናቶችን እና ሴቶችን በሥርዓተ ፆታና ሥነ ተዋልዶ በኩል በመድረስ የጤና ክትትል እና ድጋፍ ለማድረስ ያለመ መሆኑን ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ለሕፃናት አልሚ ምግብ ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም የእንስሳት ክሊኒኮችን በማቋቋም ክትባቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ ተመላክቷል።
በክልሎቹ በተከሰተው ግጭትና ድርቅ ምክንያት ለተፈናቀሉ እና ወደ ቀያቸው ለተመለሱ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፉ ተደራሽ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
ጃፓን ድጋፉን የምታቀርበው በምግብ ፕሮግራም፣ በምግብ እና እርሻ ድርጅት እንዲሁም በፍልሰተኞች ድርጅት አማካኝነት መሆኑን ያመላከተው መረጃው፤ በቀይ መስቀል ኮሚቴ እንዲሁም በተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ እና በዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅትም ሰብዓዊ ዕርዳታው እንዲዳረስ እንደሚሠራ መረጃው አትቷል። በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ እንዲሁም በሌሎችም ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች በኩል መሆኑን አስታውቃለች።
በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ቆላማ አካባቢዎች ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የ14 ሚሊዮን ዶላር የዕርዳታ ስምምነት መፈረሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል ቆላማ አካባቢዎች ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የ14 ሚሊዮን ዶላር የዕርዳታ ስምምነት የተፈረመው በገንዘብ ሚኒስቴርና በአፍሪካ ልማት ባንክ መካከል ነው። ገንዘቡ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአካባቢ ልማት፣ ሥርዓተ ፆታን ያገናዘበ የተቀናጀ ዘላቂ የውሃ ልማት፣ የአካባቢ እና የግል ንጽሕና አገልግሎትን ለማስፋፋት እንደሚውል ተነግሯል።
በተጨማሪም በውሃ አጠር አከባቢዎች ለሚኖሩ አርብቶ አደሮች የከርሰ ምድር ውሃ ተደራሽ የሚሆንበት ፕሮጀክት እንደሚተገበር እና የገንዘብ ድጋፉ በጤና፣ በማኅበራዊ ኑሮ፣ በሥነ-ምግብ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትን ለመደገፍ እንደሚውል ተገልጿል።
የዕርዳታ ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱል ካማራ መሆናቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም