ሲዳማዎች የሚወዱትን ሰው ሲቀበሉ ‹‹ዳዮኤ ቡሹ›› ይላሉ፤ አፈር ይምጣብኝ ማለታቸው ነው። እጅ ሲነሱ፣ ከልብ የመነጨ ፍቅራቸውን ሲገልጹ ነው። ሰው ወዳድነታቸውን የሚያስመሰክሩበት እና ልዩ አቀባበል የሚያደርጉበት አባባላቸው ነው።
ሲዳማዎች ከሁሉም ክልሎች የተወከሉ ወንድምና እህቶቻቸውን ‹‹ዳዮኤ ቡሹ›› ለማለት ደፋ ቀና ማለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። የባህላዊ ጭፈራቸውን እና ምግባቸውን ሊጋብዙ ጓጉተዋል።
እንኳን ሰው እንስሳው በፍቅር የሚቀበልባት፣ ጽዱ ከተማዋ፣ አረንጓዴ ልማቷ፣ የፍቅር እና የመቻቻል ሀገሯ ሲዳማ ልምዷን ለማካፈል፣ በረከቷን ለማቋደስ ዝግጅት ላይ ትገኛለች።
ነዋሪዎቹ አካባቢውን በማስተካከል ሽር ጉድ ላይ ናቸው። ‹‹አቦ›› ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓታቸውን ተሞክሮ ሊያጋሩ የቀኑን መድረስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። የየክልሉ ተወካዮችም የአካባቢውን ጸጋ ለማየት፣ በተፈጥሮ ፍል ውሃ ለመጠመቅ ጓጉተዋል።
የሚጎበኙ የቱሪስት መስህብ ታሪካዊ ቦታዎችን እያጸዱ፣ እያሰናዱ እና እያደሱ ይገኛሉ። እንግዶቻቸውን ጥቁር ሐይቅ ዳር ሊያዝናኑዋቸው፣ በጀልባ ሊያንሸራሽሯቸው፣ ታቦር ተራራን ሊያስጎበኙ በዋዜማው ሥራ በዝቶባቸዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት የሚከበረው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን “ኅብረብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ የማጠናቀቂያ በዓሉ ኅዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ለ17ኛ ጊዜ ለማክበር ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቅቋል።
የአባዬ ሎጅ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛው ግርማ፤ ሐዋሳ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ፣ በእንግዳ ተቀባይነቷ የምትታወቅ ከተማ መሆኗንም ይጠቁማሉ። መርሐ ግብሩ በተደጋጋሚ የተደረገ ቢሆንም የሐዋሳ ባለሃብቶች ከወትሮው በተለየ መልኩ ተዘጋጅተው እየጠበቁ እንደሚገኙም ይጠቁማሉ።
ሲዳማ የራሱን ክልል ካደራጀ በኋላ ከተማው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበር መሆኑ በዓሉን ከወትሮው ለየት ያደርገዋል የሚሉት አቶ ግዛው፤ ሲዳማ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፎ በመያዝ የሚታወቅ ነው።
እንግዶቻችን በነጻነት ተደስተው ተዝናንተው እንዲመለሱ ተዘጋጅተን እየጠበቅን እንገኛለን ይላሉ።
በይርጋለም ከተማ አረጋሽ ሎጅ ባለቤት ግሪጎሪ ሚሳይለዲስ፤ በእናቴ ኢትዮጵያዊ በአባቴ ግሪካዊ ብሆንም በሲዳሞ ተወልጄ በማደጌ ብዙዎች እንደሚቆጥሩኝ የውጭ አገር ዜጋ ሳልሆን እግዚአብሔር የሰጠኝ ኢትዮጵያዊ የሲዳማ ተወላጅ ነኝ›› ይላሉ።
ተፈጥሮ ያደለው አካባቢ ውስጥ ነው የምኖረው፣ በሲዳሞ ቤት አሠራር በቀርከሃ ቤት አሠራር ለሙሚኔ በተባለው የጥበብ ቤት ውስጥ ነው የምኖረው። የሲዳሞ የቤት አሠራርን አስተዋውቄያለሁ ብለዋል።
ድሮም የማውቀው ሲዳሞ ክፍለ ግዛት ሲባል ነው። ፊደል ማንበብ የጀመርኩት ‹‹ሲዳማ›› በሚለው ነበር። ስለዚህ ሲዳማ አዕምሮዬ ውስጥ ተቀርጿል፣ ልቤ ውስጥም ተቀምጧል፣ ለእኔ ሲዳሞ ትልቅ ትርጉም አለው።
ዛሬ በክልልነት ተደራጅቶ ሳየው፣ ሕዝቡን ስመለከት በጣም ደስ ይለኛል። በአካባቢው ጫማ እና ደህና የለበሰ፣ የተማረም መመልከት ብርቅ ነበር፤ ዛሬ ሁሉም ጫማ ለብሶ መመልከት ለእኔ ኩራት ነው ሲልም ደስታውን ገልጿል።
ልዩነት አላውቅም። እኔ ያደግኩት በአንድ ኢትዮጵያዊነት፣ በፍቅር ነው። አሁንም አንድነትን ነው የምመኘው። አንድነቱ ሲመጣ ለእኔ ትልቅ ደስታ ነው። ለእኔ የሚገባኝ ኢትዮጵያዊነት አብሮ መኖር ማለት ነው።
እኛ ሁል ጊዜ ተዘጋጅተን ነው የምንጠብቀው። እንግዳ መቀበል ለእኛ አዲስ አይደለም። ከዓለም ዙሪያ እንግዶች መጥተው ያርፋሉ። እንደወትሮው እንግዶቻችንን ዳዮኤ ቡሹ ብለን በክብር ተቀብለን አስተናግደን ለመሸኘት ዝግጁ ነን።
በክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ማሪሞ፤ ዘንድሮ በክልሉ በሚከበረው በዓል አንዱ የጉብኝት መስመር ይሆናል ተብሎ ከተዘጋጀው መካከል መዳረሻ ተብሎ ከሚጠበቀው መካከል ይርጋዓለም ከተማ አንዱ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ሲዳማ ክልል ዕድሜ ጠገብ ከሆኑ ከተሞች አንዱ ሲሆን፤ በደርግ ዘመን የሲዳማ አውራጃ የአካባቢው አስተዳደር ወደ ሐዋሳ ከተማ ከመዘዋወሩ አስቀድሞ ለረጅም ጊዜ የሲዳማ ጠቅላይ ግዛት የአካባቢው የአስተዳደር ማዕከል በመሆን ያገለገለች ከተማ መሆኗን ይጠቁማሉ።
በዚህ ምክንያት የተለያዩ ቅርሶች ያሏት ከተማ መሆኗን፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ልጅ የራስ ደስታ ባለቤት የልዕልት ተናኜ ቤት፣ ዋሻዎች፣ ቤተ መንግሥቶች ያሉበት፣ በአካባቢው መጀመሪያ ትምህርት ቤት ያለበትና ጥንታዊ ከተማ መሆኗን ነው የሚናገሩት። የይርጋዓለምና አካባቢዋን የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ እየተጎበኘ ይገኛል።
አረጋሽ ሎጅ ለቱሪስት መዳረሻ ትልቅ አገልግሎት በመስጠት ትልቅ ሚና የተጫወተ ማኅበረሰብ አቀፍ ቱሪዝምን ያስለመደ፣ ባህላዊውን የሲዳማን የደጋ መንደር የቀርከሃ ቤት አሠራር ጥበብን በመከተል የተገነባ ሰላማዊ ለውጭ ጎብኚዎች የሚመረጥ ቦታ መሆኑን ይናገራሉ። በቦታው ላይ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መስህቦች መሆኑንም ይገልጻሉ።
የሐዋሳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ምክትል ኃላፊና የማስፈጸም አቅም ግንባታና የአካባቢ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ታመነ እንደሚሉት፤ ከተማዋ የምትታወቅበትን የፍቅር ከተማነቷን፣ ጽዱ፣ ውብ፣ አረንጓዴና የቱሪስት ከተማነቷን ለእንግዶች ለማስተዋወቅ እየተሠራ ይገኛል።
በተለይ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የቱሪስት ቦታዎችን የማልማት ሥራ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ጀምሮ የመጨረስ ትግበራን እውን ለማድረግ የሥራ ባህልን በመቀየር እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት እየተሰራ ነው።
የታቦር ተራራን ኢኮ ቱሪዝም ስፍራን ለጎብኚዎች ዝግጁ ለማድረግ የግንባታ ሥራው እየተከናወነ ይገኛል። መግቢያው በእርግብ አምሳል የሚገነባው ይህ ስፍራ ከተማው የሰላም ከተማ መሆኗን የሚያሳይ መሆኑን ነው የሚጠቁሙት።
እዚሁ ስፍራ ሲዳማዎች አገጭ ለአገጭ ተገጫጭተው የሚታይበት ገጽታ የሲዳማ ባህላዊ ጭፈራን የሚንጸባርቅ ከመሆኑም ባሻገር ባህልን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው የሚናገሩት።
እንደርሳቸው ገለጻ፤ ለብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል እንግዶች በሰላም ገብተው በሰላም እንዲወጡ፣ ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የእግረኛ መንገዶችን የማስተካል ሥራም እየተሠራ ይገኛል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም