አዲስ አበባ፡- ዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት /ኢንተርፖል/በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታወቀ።
በዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት /ኢንተርፖል/ የፀረ ሽብር ማዕከል የአፍሪካና የአውሮፓ ማዕከል ኃላፊ ዳንኤል ዳምጃኖቪክ በአዲስ አበባ ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ባለው በ24ኛው የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ጠቅላላ ስብሰባ በመካፈል ላይ ይገኛሉ። ኃላፊው እንደገለጹት፤ድንበር ዘለል ሽብርተኞችን መከላከል የኢንተርፖል ዋነኛ ተልዕኮው ነው። በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነት በመዋጋት የኢትዮጵያን የላቀ ሚና የሚደነቅ ነው። ዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረት ይደግፋል።
በዓለም 195 አገራትን በአባልነት ያቀፈው ኢንተርፖል በየአህጉራቱ ከሚገኙ የፀረ ሽብር የቀጣና ማዕከላት መካከል አንዱ በኬንያ ናይሮቢ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። በተለይም የሽብርተኝነት ስጋት ባለበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ከሚመለከታቸው የሀገራቱ የጉምሩክ፣ ኢሚግሬሽን፣ የፖሊስና ሌሎችም ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ስብሰባም በርካታ ባለድርሻ ተቋማት ጋር ለመምከር ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።ላለፉት አምስት ዓመታት ከየሀገራቱ የጉምሩክ፣ ኢሚግሬሸን፣ ከፖሊስና ሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሽብርተኞችን ለመከላከል በርካታ ርምጃዎችን ወስዷል ብለዋል።
በስብሰባው የቀጣናው ሀገራት የጸረ ሽብር ትግል ተሞክሯቸውን ያጋሩ መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ልምድ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ኢንተርፖል በፀረ ሽብር ግዳጅ አፈጻጸም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎችም ሀገራት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲሁም ተሞክሮ እንዲለዋወጡና አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያደርገውን ድጋፍና ትብብር ያጠናክራል ብለዋል።
በጸረ ሽብር የትግል እንቅስቃሴ ኢንተርፖል ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።ኢትዮጵያ በቀጣናው የሽብር ተጋላጭነት ስጋት ካለባቸው አገሮች መካከል መሆኗን ጠቅሰው የመከላከል ሥራው በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል ይገባዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም