– ንብ ማነብ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጓል
ባህርዳር፡- በአማራ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ በወሳኝ ተልዕኮ እየተሠራ መሆኑንና በበጀት ዓመቱም ለአንድ ሚሊዮን 203 ሺ180 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ። ከተለዩት የሥራ ዘርፎች የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝና በዚህም ወደ 529 ሺ ወጣቶችን ለማሠማራት መታቀዱ ተጠቁሟል።
የአማራ ክልል የሥራና ሥልጠና ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች በማኅበር ተደራጅተው በንብ ማነብ ላይ የተሠማሩ ወጣቶች ያመረቱትን የማርና ማር ውጤቶችን የማስተዋወቅና የማነቃቃት መርሐግብር ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ በተካሄደበት ወቅት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ለአንድ ሚሊዮን 203 ሺ180 ወጣቶች ሥራ ለመፍጠር መታቀዱንና የሥራ ዕድል ለመፍጠርም የግብርናው ዘርፍ በተለይም ንብ ማነብና የእንስሳት ሀብት ልማት ትልቅ አቅም ያለው ሆኖ ተገኝቷል። በዚሁ መሠረትም የሥራ ዕድሉ ከሚፈጠርላቸው አንድ ሚሊዮን 203 ሺ180 ወጣቶች መካከል 529 ሺ ወጣቶች በግብርናው ዘርፍ የሥራ ዕድል የሚፈጠርላቸው ናቸው።
እንደ አቶ አወቀ ማብራሪያ በግብርናው ዘርፍ በተለያየ መንገድ ወጣቶችን በማገዝ ውጤታማ ለማድረግ 25 የሚሆኑ ግብረሰናይ ድርጅቶች ይገኛሉ። የተቋማቱን አቅም የበለጠ ለመጠቀም የሥራና ሥልጠና ቢሮ ጥረት እያደረገ ነው።
ተሞክሯቸውን ለማስፋት፣ የአሠራር ድግግሞሽ እንዳይኖርና የሀብት ብክነት ሳይኖር አቅማቸውን አሟጠው ከመንግሥት አቅም ጋር የተቀናጀ ሥራ እንዲሠሩ ግብረሰናይ ድርጅቶቹ የጋራ የሆነ ፎረም ኖሯቸው ለመንቀሳቀስ የሚችሉበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ቢሮው ከግብረሰናይ ድርጅቶቹ ጋር በመነጋገር የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት ጥረት እያደረገ እንደሆነም ተጠቁሟል።
ቀድመው ሥራ የጀመሩ ውጤታማነታቸው እየታየ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አወቀ፤ በተለይም በንብ ማነብ የክህሎት ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ ምርት ተመርቶ ለገበያ እስኪደርስ ድረስ ባለው ሂደት ወጣቶችን በማብቃት፣ለንብ ማነብ አስፈላጊ የሆነ ቁሳቁስ በማሟላትና በተለያየ መንገድ በመደገፍ በክልሉ አዊ፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎ፣ዋግ ኽምራና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ዓለምአቀፍ ሥነ ነፍሳትና ሳይንስ ሥነምህዳር ማዕከል (አይ.ሲ.አይ.ፒ ኢ) የሞይሽ ፕሮግራም በውጤታማነት እንደሚጠቀስ አመልክተዋል።
በፕሮግራሙ እየታገዙ ወጣቶችም ከባዕድ ነገር ነፃ የሆነ (ኦርጋኒክ) ማርና ሰም አምርተው ለገበያ በማቅረብ ኮለን ወይንም ንብ አባዝተው ለንብ አናቢዎች በመሸጥ በገቢ ተጠቃሚ ከመሆናቸው በተጨማሪ ክልሉንም በማር ልማት እንዲታወቅ በማድረግ ውጤታማነታቸው እየታየ መሆኑን አስረድተዋል። አሳሳቢ የሆነውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ በክልሉ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ ፕሮግራም እንደሆነም ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት ከአጠቃላይ እቅዱ 15 በመቶ ለመፈጸም ወይንም ለ180 ሺ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሆነ የገለጹት አቶ አወቀ፤ በሩብ ዓመት ለ129 ሺ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል። በክልሉ የሥራ ፈላጊው ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፣53ሺ የዩኒቨርስቲና 81ሺ151 የኮሌጅ ተመራቂዎች፣ በድምሩ ወደ 912 ሺ ሥራ ፈላጊዎች መመዝገባቸውን አመልክተዋል። ለሥራ ፈላጊው ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል መመሪያ በማዘጋጀት፣በርብርብ ለመሥራት ከታች እስከ ላይ ያለው አመራር በጋራ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል። ጦርነት ቆሞ ሰላም እየተፈጠረ ባለበት በዚህ ወቅት በጦርነቱ የተጎዳው የማኅበረሰብ ክፍል ሥራ ፈላጊ በመሆኑ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተግባር ለነገ የሚባል እንዳልሆነ አስምረውበታል።
ዓለም አቀፍ ሥነ ነፍሳትና ሳይንስ ሥነ ምህዳር ማዕከል (አይ.ሲ.አይ.ፒ ኢ) የሞይሽ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ወርቅነህ አያሌው በበኩላቸው፤ በሞይሽ ፕሮግራም ወደ 10ሺ የሚሆኑ ወጣቶች ተሳታፊ መሆናቸውንና ፕሮግራሙም ተገምግሞ ጥሩ ውጤት በማስገኘቱ ሞይሽ የሚለው ሁለተኛው ፕሮግራም መጀመሩን ገልጸዋል። በሞይሽ ፕሮግራም በአማራ ክልል ወደ 19ሺ ወጣቶች መካተታቸውንና በአጠቃላይ በክልሉ ወደ 30ሺ ወጣቶች በንብ ማነብ መሠማራታቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ በጦርነት ቀጣና ውስጥ በነበሩ ጥቂት አካባቢዎች ወደኃላ ቢቀሩም በንብ ማነብ የተፈጠረው የሥራ ዕድል መልካም ውጤት እያስገኘ መሆኑን አስረድተዋል። ዋና መሥሪያ ቤቱን ካናዳ ባደረገው ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ ሥነ ነፍሳትና ሳይንስ ሥነምህዳር ማዕከል (አይ.ሲ.አይ.ፒ ኢ) በእስካሁን እንቅስቃሴው በአማራ፣በኦሮሚያ፣በደቡብና በትግራይ ክልሎች 70ሺ ወጣቶችን በንብ ማነብ በማሰልጠን ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል። በአምስት ዓመት ጊዜ 100ሺ ወጣቶችን በልማቱ ውስጥ ለማስገባትና እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም