አዲስ አበባ፡- በድሬዳዋና አካባቢዋ ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች የሚውል ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የአካል ድጋፍና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
በድሬዳዋ ከተማ ሐምሌ 24 የተከበረውን የአካል ጉዳተኞች ቀንን አስመልክቶ የተሰጠው ድጋፍ ዊልቸር፣ ክራንች፣ አጋዥ የድምጽ መሣሪያና የአይነስውራን በትር መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገልጸዋል።
እንደ ዶክተር ኤርጎጌ ገለጻ በኢትዮጵያ ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ የአካል ጉዳተኞች ሲኖሩ ለዘመናት ከተሳትፎና ተጠቃሚነት ተገፍተው ቆይተዋል። ይሄንን ለመቅረፍ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሠራ መሆኑንና የአካል ጉዳት በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ላይ ሊከሰት የሚችል የሕይወት አጋጣሚ መሆኑን መረዳት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሚኒስትሯ ለአገር ሕልውና ዋጋ የከፈሉ ጀግኖች ተገቢውን ክብርና እንክብካቤ እንዲያገኙ የሚያስችል የኢትዮጵያ ጀግኖች የጦር አካል ጉዳተኞች የተሐድሶና ስልጠና ማዕከል ማቋቋሚያ አዋጅ ተጠናቆ ለመንግሥት መቅረቡንም ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኝነትን ከሚያስከትሉ በሽታዎች እና ሁኔታዎች አብዛኞቹ በቀላሉ መከላከል ይቻላል ብለዋል። ሁለንተናዊ የሕክምና ተቋማትን አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች አካታች ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እንደ ዶክተር ሊያ ገለጻ በቅርቡ በጤና ትምህርት ዘርፍ የተከሰተው በትምህርትና ሥልጠና አካታችነት ላይ ውስንነት መኖሩን ያሳየ ነው። በቀጣይ ሙያው የሚፈልገው ክህሎት እንዲኖር መሠረታዊ ጉዳዮችን ባሟላ መልኩ የአካል ጉዳተኞች በጤና ሙያ ስልጠና ውስጥ የሚካተቱበት አግባብ መስፋት እንዳለበት ያሳየ መሆኑንና ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር ስለ አካል ጉዳት ሲታሰብ የችሮታ ጉዳይ መሆን እንደሌለበት ገልጸዋል። የከተማ አስተዳደሩ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ወይንሸት ሙሉሰው የአካል ጉዳተኞች ችግር የሚፈታው ሁሉም በትብብር ሲሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ በጥቂት ሰዎች ሲከበር የነበረው በዓል በአመራሩ ዘንድ የተሻለ ግንዛቤ በመፈጠሩ በክልሎች ተሳትፎ በየክልሉ በዙር እየተከበረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኅብረተሰቡና የመንግሥት አካላት በተለይ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው፣ መስማትና ማየት የተሳናቸውና የአዕምሮ መታወክ ያጋጠማቸው ወገኖችን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ ላይ የአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱና መብት እንዲከበር የሠሩ የክልል ቢሮዎች፣ ኤምባሲዎች ዓለም አቀፍና ሀገር በቀል የግብረሰናይ ድርጅቶች የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የ2016 ዓመት የአካል ጉዳተኞች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚከበር ይሆናል።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም