ኢንስታግራም፣ ፌስቡክን እና ዋትስአፕን የሚያስተዳድረው ሜታ ኩባንያ ከፌስቡክ ገጾች ላይ የዜና ይዘቶችን ጨርሶ ሊያስወግድ እንደሚችል ዛተ። ይህ ዛቻ የመጣው የዜና አገልግሎቶችን ሜታ ከሚያጋብሰው ትርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ በአሜሪካ አንድ አዲስ ረቂቅ ሕግ መርቀቁን ተከትሎ ነው።
የዜናና መረጃ ነክ ይዘት ያላቸው የጋዜጠኝነት ሥራዎች በስፋት በገጹ እያጋራ ነገር ግን የማስታወቂያ ትርፉን ለብቻው ይወስደዋል በሚል ሲከሰስ የቆየው ሜታ በበኩሉ ‘እኔ ውለታ በዋልኩላችሁ…’ እያለ ነው።ድርጅቱ እንደሚለው ከዜናና መረጃ ነክ ገጾች የሚገኘው የማስታወቂያ ትርፍ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የሚዲያ መረጃዎችን ወደ ፌስቡክ እድምተኛ የምወስደውም በግድ እንዲነበቡ ለማድረግ ነው ይላል።
ኩባንያው እንደሚለው ተጠቃሚዎቹ ዜናና መረጃዎችን ከፌስቡክ ለማንበብ ፍላጎታቸው እምብዛምም ነው። የሚዲያ ተቋማት በበኩላቸው እኛ ለፍተን ደክመን ባሰናዳነው ዜናና መረጃ ፌስቡክ የማስታወቂያ ትርፍ ያጋብሳል፣ ለኛ ግን ጠብ የሚል ነገር የለም ሲሉ ያማርራሉ። ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ተቃውሞ ከሚዲያዎች ለፌስቡክ ቀርቦ ያውቃል፤ ይህም የሆነው በአውስትራሊያ አገር ነው።
ፌስቡክ በውስትራሊያ ቀርቦበት ለነበረ ተመሳሳይ ቅሬታ ‘እንዲያውም በገጼ ዜናን አላስተናገድም’ ሲል ዝቶ ነበር።የኋላ ኋላ ግን ሐሳቡን አጢኖ፣ ከመንግሥት ጋር ተደራድሮ ለሚዲያዎች ትርፍን የማጋራት ስምምነት ለማድረግ ተገዷል።በተመሳሳይ አሁን በአሜሪካ የቀረበው ረቂቅ ድርጅቱን ከሚያገኘው ትርፍ ከፊሉን ለመገናኛ ብዙኃን እንዲያካፍል ሊያስገድደው ይችላል።
በአሜሪካ የመገናኛ ብዙኃን ከትንሽ እስከ ግዙፎቹ ጭምር ‘ሜታ በኛ ላብ ሚሊዯን ዶላር ይሰበስባል’ ሲሉ የሚከሱት በተደጋጋሚ ነው። ፌስቡክ ግን ሁልጊዜም የሚለው ሚዲያዎቹ እንደሚያስቡት ይዘታቸው በገጹ ላይ በደንበኞች ተፈላጊም ተነባቢም አይደለም።
አሁን የቀረበውና በምህጻሩ ጄሲፒኤ የሚባለው ረቂቅ ሕግ በሚኔሶታ እንደራሴ በሆኑት አሚ ክሎቡቻር ፊታውራሪነት የቀረበ ነው።ረቂቅ ሕጉ በዲሞክራቶችና በሪፐብሊካኖች ዘንድም ከፍ ያለ ድጋፍ አለው።ረቂቅ ሕጉ ከጸደቀ ለሚዲያ ኩባንያዎች ትልቅ ድል ነው ተብሏል።ምክንያቱም መገናኛ ብዙኃኑ ለሚያመርቱት መርሃግብር ፌስቡክ ከትርፍ ሊያጋራቸው ይገደዳል።
ይህም በገቢ ድርቅ ለተመቱ አነስተኛና መለስተኛ የአካባቢ መገናኛ ብዙኃን እንደ አዲስ እንዲያንሰራሩ ሊያደርጋቸው ይችላል። በርካታ አነስተኛና መለስተኛ ሚዲያዎች በአሜሪካ በወረርሽኙ ጊዜ የትርፍ ማሽቆልቆል ገጥሟቸው ለመዘጋት ተቃርበው ነበር።በአንጻሩ የነርሱኑ ይዘት የሚያጋራው ፌስቡክ በትርፍ ተንበሽብሾ መሰንበቱ አይዘነጋም።
አሜሪካ ያለመጠን ገዝፈው የገበያ ውድድር እንዲቀጭጭ አድርገዋል ከምትላቸው ኩባንያዎች አንዱ ሜታ ነው።ሜታ ኩባንያ መቀመጫውን ካሊፎርኒያ ያደረገና ግዙፎቹን የማኅበራዊ ሚዲያዎች ማለትም ፌስቡክን ዋትስአፕንና ኢኒስታግራምን በባለቤትነት የሚያስተዳድር ድርጅት ነው።
የአሜሪካ የኢኮኖሚክ ሊበሪቲስ ፕሮጀክት ዳይሬክተር የሆኑት ማት ስቶለር ‘ሜታ ቀጫጭን ሚዲያዎችን ሰልቅጦ እየበላቸው ነው’ ሲሉ የውድድር ሜዳው እየጠፋ ስለመሆኑ አስተያየት መስጠታቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም