አዲስ አበባ፡- በ2015 የትምህርት ዘመን መጨረሻ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ 37 ተማሪዎችን በቡና ሳይንስ የትምህርት መስክ እንደሚያስመርቅ ቦንጋ ዩንቨርሲቲ አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው ካለው 200 ሄክታር መሬት ውስጥ በ150 ሄክታሩ ላይ የግብርና ምርቶችን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የቡና ምርት ኢትዮጵያ ትልቁ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበት ሸቀጥ በመሆኑ በ2015 ዓ.ም መጨረሻ 37 ተማሪዎችን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በቡና ሳይንስ የትምህርት መስክ ይመረቃሉ፡፡
ኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም ያበረከተች ሀገር ብትሆንም እስካሁን ድረስ የቡና ትምህርት መስክ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት አዳጋች ሆኖ ነበር ያሉት ዶክተር ጴጥሮስ፤ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት የቡና ሳይንስ ትምህርት ክፍል እራሱን ችሎ በ2012 ዓ.ም እንዲከፈት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በቡና ምርት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመመርመር ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ቡናን በትምህርትና ምርምር አስደግፎ ለመምራት ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ የቡና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል በማቋቋም ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሚቀጥለው ዓመት በሁለተኛ ዲግሪ በቡና ሳይንስ ተማሪዎች የሚመረቁ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ጊዜትም የቡና ሳይንስ ትምህርት መስክን በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ማስተማር እንደሚጀምር ዶክተር ጴጥሮስ ጠቁመዋል፡፡
ስለ ቡና ታሪክና ተክል እንኳን በተግባር የተደገፈ ልምድ መስጠት የማይችሉ የሌሎች ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች በድፍረት ስለ ቡና ሳይንስ እያስተማሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የቡና መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ሳይንሱ እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ ሳይሰጥ መቆየቱን ጠቁመው፤ በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ መጀመሩ የሀገሪቷን የቡና ተጠቃሚነትን የሚያሳድግና በኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ከርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ እንደ ቡና ያሉ ምርቶችን በትምህርትና ምርምር አስደግፎ መምራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመሆኑም ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ችግሩን ለመፍታት በቡና ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ በሀገር ደረጃ የመጀመሪያ የሆነው የቡና ሳይንስ የትምህርት ክፍል በማቋቋም ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ረገድ በአካባቢው ያለውን ሀብት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል፣ ማህበረሰቡን በሰፊው ተጠቃሚ ለማድረግና በስራ ላይ ሊገጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች ላይ ሰፊ ጥናት መደረጉን አብራርተዋል፡፡
የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ ዋናው መንገድ ጽንሰ ሃሳብን ወደ ተግባር መለወጥ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህም እንዲረዳ በዩኒቨርሲቲው ግቢ በ82 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ የቡና እርሻ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ቦንጋ ዩኒቨርስቲ ካለው 200 ሄክታር ለተለያዩ ግንባታዎች የሚውለውን 50 ሄክታር በመለየት በተቀረው 150 ሄክታሩ ላይ ቡና፣ ማንጎ፣ አቦካዶ፣ አናናስ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ቅመማቅመም፣ አፕልና እንሰት ምርቶችን በስፋት በማምረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ምርቶቹን ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ በመቀየር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት እንደታሰበም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
እ.አ.አ. በ2030 ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም በአፍሪካ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባር ቀደም የመሆን ራዕይን ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር በተጨማሪ በግብርናና በማህበረሰብ አቀፍ ተግባራት እንደሚሳተፍ ዶክተር ጴጥሮስ ተናግረዋል፡፡
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 9 ቀን 2015 ዓ.ም