አዲስ አበባ፡- በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ሕግና መመሪያ ያላከበሩ 3 ሺህ 800 አመራሮች እና ባለሙያዎች ተጠያቂ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን ቢሮው የከተማዋ ተቋማት ለነዋሪዎች በሚሰጡት አገልግሎት ዙሪያ ትናንት ከነዋሪዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ሲያደርግ እንዳስታወቁት፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የታዩ ችግሮችን በመፈተሽ 3 ሺህ 800 አመራርና ባለሙያዎች በተለያየ መንገድ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
በዚህም በአገልግሎት አሰጣጡ ከሕዝብ በቀረቡ ጥቆማዎች መሰረት በአድልኦ የሚሰሩ፣ በሌብነት የተጠረጠሩ፣ ሕዝብን ለእንግልት የዳረጉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተጠያቂ ሆነዋል።
በከተማዋ 47 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መኖራቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ ሂክማ፤ ከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንዳይኖር፣ አገልግሎቶች ፍትሐዊ፣ ውጤታማና ቀልጣፋ እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ሕግና ስርዓትን የተከተለ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር የሚያደርገውን ቁጥጥር ያሳድጋል፤ በቀጣይ በሚኖሩ መድረኮች ሁሉም ተቋማት ከሕብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንዲያደርጉና በውይይቱ የሚነሱ ሃሰቦች ምላሽ እስከሚያገኙ ድረስ ቢሮው ክትትል ያደርጋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ የከተማ አስተዳደሩን ተቋማት አፈጻጸም በመገምገም ማሻሻያዎች እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
ሌብነትና ብልሹ አሰራርን መከላከል፣ የተለያዩ ግብዓቶችን ማሟላት፣ ምቹ ስራ አካባቢን መፍጠርና የተገልጋይ እርካታን መመዘን ላይ ትኩረት ያደረገ ስራ በቀጣይ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
ቢሮው በመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ በመልካም አስተዳደርና በማህበራዊ ዘርፍ የተደራጁ ተቋማት በአገልግሎት አሰጣጥ ጉዳይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቀጥታ የሚገናኙበትን ስድስት ዋና መድረኮችን ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
በተጨማሪ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በመተባበር በየሳምንቱ የሬዲዮና የቴሌቪዥን የቀጥታ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የተቋማት አመራሮች ከሕዝብ በሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ላይ ምላሽ እንዲሰጡም እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በቢሮው የተዘጋጁ መድረኮችና የመገናኛ ብዙሃን ፕሮግራሞች ላይ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሻሻል የሚረዱ ግብቶችን ለመሰብሰብ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን አመልክተዋል።
በውይይት መድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ የሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ የባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮና የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊዎች ከባለድርሻ አካላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም