የምሽቱን ጨለማ በቀኗ ፀሐይ

27

አፍሪካ ካሏት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊየን ህዝቦች የሚበዙት የገጠር ነዋሪ ናቸው፡፡ በገጠር ነዋሪ ከሆኑት ህዝቦች ውስጥ 218 ሚሊየኑ በፍጹም ድህነት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ስድስት መቶ ሚሊየን ያህሉ ደግሞ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አያገኙም፡፡ በአፍሪካ ከሰባት ሰዎች አንዱ በኃይል እጦት ምክንያት ሻማ፣ ነጭ ጋዝና ባትሪዎችን በመጠቀም ህይወቱን ይገፋል የሚለው “ኢንተር ፕራይዝ ቻሌንጅ ፈንድ” በመባል የሚታወቀው ለትርፍ ያልተቋቋመው ድርጅት ነው፡፡

ድርጅቱ የፀሐይ ቴክኖለጂን ለገጠሩ ህብረተሰብ ለማዳረስ የሚሰራ ሲሆን ያቀረበው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ እየጨመረ የመጣው ፍላጎት የኤሌክትሪክ ዋጋ ውድ እንዲሆንና ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ገጠራማ አካባቢዎች አቅርቦቱ ውስን እንዲሆን አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያም 11 ሚሊየን የሚደርሱ የገጠር መኖሪያ ቤቶቸ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አያገኙም፡፡ አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ከታዳሽ ኃይል የምታመነጨው ኃይል 18 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ከፀሐይ ብርሃን የሚገኝ ኃይልን ማስፋፋት በርካታ ዕድሎችን የሚፈጥርና የሚሊዮኖችን ሕይወት የሚለውጥ ነው፡፡

የአፍሪካ “ኢንተር ፕራይዝ ቻሌንጅ ፈንድ” በፀሀይ ኃይል አቅርቦት ላይ ለተሰማሩ አገር በቀል የግል ተቋማት ውድድር በማዘጋጀት የስራ ዕቅድ አቅርበው እንዲወዳደሩ በማድረግ ለአሸናፊዎቹ የስራ ማስኬጃ ይሰጣል፡፡

ከዚህ በፊት የመጀመሪያው ፕሮግራም እንደ ዛምቢያና ዙምባብዌ ባሉ አራት ደቡባዊ የአፍሪካ አገራት ላይ ተተግብሮ ወጤት ተገኝቶበታል፡፡ ከተጠቀሱት አገራት የተገኘውን ልምድ በመያዝ የቀጠለው ሁለተኛ ዙር ወደ ምስራቅ በማምራት አምስት አገሮችን ያሳትፋል፡፡ አገራቱም ኢትዮጵያ፣ ሱማሊያ፣ ጋና፣ ናይጄሪያና ሴኔጋል ናቸው፡፡

ፕሮጀክቱ ከሰሃራ በታች ባሉ አራት የአፍሪካ አገሮች ተግባራዊ ተደርጎ የተገኘውን ውጤት በመመልከት የፕሮጀክቱ ድጋፍ ሰጪ የዩናይትድ ኪንግ ደም ዓለም አቀፍ ተራድዎ ድርጅት ደረጃውን ከፍ በማድረግ በአምስት አገራት እንደገና እንዲሰራ ድጋፍ ያደረገው “AECF” በሚባለው ድርጅት በኩል ነው:: ድጋፉ ተግባራዊ የሚደረገው “The African Enterpruse Challenge Fund (AECF)” ስሙ እንደሚያመለክተው በውድድር በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡

 በኢትዮጵያ ከጸሐይ ብርሃን በሚገኝ ኃይል ላይ ለሚሰሩ የግሉ ዘርፍ ድርጅቶች በሙሉ ይህ ውድድር ለተሳትፎ ክፍት ነው፡፡

ፍላጎቱና አቅሙ ያላቸው ከፀሐይ ብርሃን በሚገኝ ኃይል ዙሪያ የሚሰሩ ኩባንያዎች በሚያቀርቡት የስራ ዕቅድ ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው ሌሎች አራት አገራት በተመሳሳይ መንገድ ከሚቀርቡ ድርጅቶች ጋር ይወዳደራሉ፡፡ በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ደካማ የስራ ዕቅድ አቅርበው ዕድሉን እንዳያጡ በቂ ዝግጅት አድርገው ጠንካራ የስራ ዕቅድ ይዘው ሊቀርቡ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

ለተወዳዳሪ ድርጅቶቹ የመጀመሪያው መስፈርት የግል ድርጅቶች መሆናቸው ነው:: ሁለተኛው ፒ ኤል ሲ መሆን አለባቸው:: ሶስተኛው የሚያቀርቡት የስራ ዕቅድ ላይ የሚጠይቁት የገንዘብ ድጋፍ በ 100 ሺህ እና በ 1 ነጥብ አምስት ሚሊየን ዶላር መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም የሚቀርበው የስራ ዕቅድ ጥራትና በገንዘብ አጠቃቀምና በአሰራር ያላቸው አቅምም ተጨማሪ ማወዳደሪያ ነጥቦች ይሆናሉ፡፡

በፕሮጀክቱ ከአንድ አገር ቢያንስ አንድ ድርጅት የገንዘብ ድጋፉን ያገኛል፡፡ ነገር ግን ቀሪው በአገራቱ ባሉት ድርጅቶች ጥንካሬ የሚወሰን ነው፡ ፡ ምናልባትም ከፍተኛውን ገንዘብ ጥራት ያለው አሳማኝ የስራ ዕቅድ ማቅረብ የቻሉ የአንድ አገር ድርጅቶች ሊያገኙት የሚችሉበት ዕድል ሊኖር ይችላል፡፡ የዩናይትድ ኪንግድም መንግስት በአምስቱ አገራት ለሚተገበረው ለዚህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 16 ሚሊየን ፓውንድ መድቧል፡፡

ከፀሐይ የሚገኝ ኃይል በምሽት ብርሃን ከማግኘት ባለፈ መሰረታዊ ለሆኑ ፍላጎቶች ስልክን ኃይል ለመሙላትና ሬዲዮና ቴሌቪዥን ለመከታተል ያገለግላል፡፡ በገጠር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የእጅ ስልካቸውን ኃይል ለመሙላት 20ና 30 ኪሎ ሜትሮችን ርቀው ይጓዛሉ፡፡

ከፀሐይ የሚገኝ ኃይል ይህን አይነት እንግልት እንዳይኖር ያደርጋል:: የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በእነዚህ አካባቢዎች እስኪደርስ ድረስ ከፀሐይ ኃይል የሚገኝ ኃይልን እንደ ቅድመ ኤሌክትሪክ ማዳረስና ለቀጣዩ የመስመር ኤሌክትሪክ ልምምድ ማድረጊያ የሚወሰድ ነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በጣም አስፈላጊ ነው ተብሏል፡፡

የውሃ፣መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሀና በስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር “የሁለተኛው ብሔራዊ ኤሌክትሪክ ማዳረስ ፕሮግራም ላይ እንደተቀመጠው ሁሉም ዜጋ በ2025 የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል:: ነገር ግን ሁሉም በገመድ ዝርጋታ ሊፈጸም አይችልም፡፡ ባለን እቅድ እስከ 65 በመቶ የሚሆነውን ከግሪድ ጋር የማገናኘት እቅድ ተይዟል፡፡

ቀሪው 35 በመቶ በየቤቱ ከፀሀይ ኃይልና አንድ ቦታ ሰብሰብ ያሉ ነዋሪዎች ከሆኑ ደግሞ በአነስተኛ ግሪድ እንዲሸፈኑ ይደረጋል፡ ፡ ስለዚህ ይህ ፕሮግራም ከፀሐይ በሚገኝ ኃይል የገጠሩ ክፍል እስካሁን ከነበረው በተሻለ መልኩ በማዳረስና የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ያግዘናል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ የአገር ውስጥ ተቋማትን በመደገፍ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ብለዋል፡፡

አሁን 12 የገጠር ከተሞችን በፓይለት ለማገናኘት ጨረታ ወጥቶ እየተገመገመ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በጥራትና በዋጋ የተሻሉ ካምፓኒዎች ከታወቁ በኋላ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደስራ ይገባሉ፡፡ በቀጣይ ከነዚህ ከተሞች ተሞክሮ በመነሳት ከ250 ለሚበልጡ የገጠር ከተሞች የፀሀይ ሚኒ ግሪድ የማስፋፋት ስራ ይሰራል፡፡

በቅርቡ በተደረገ ጥናት የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ በአገር ደረጃ 44 በመቶ ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 33 በመቶ ከግሪድ የሚገኝ ሲሆን 11 በመቶ ደግሞ ከተለያዩ የፀሐይ ኃይልና ሌሎች አማራጮች የሚገኝ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፕሮጀክቱ አስተባበሪ አቶ መልሳቸው ሻንቆ በበኩላቸው “ይህ ለየት ያለ አጋጣሚ ወይም እድል ነው፡፡ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ የግል ዘርፉ በቂ ድጋፍ አይደረግለትም፤ የውጭ ምንዛሬ ችግር አለበት እየተባለ ሁል ጊዜ ይነገራል፡፡ በአንድ በኩል ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ፍላጎት አለ፡፡

በሌላ በኩል የእንግሊዝ መንግስት ለግል ዘርፉ ብቻ የተመደበ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡ ፡ ስለዚህ እነዚህን አጋጣሚዎች መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ኤሌክትሪክን ለማዳረስ የመንገድ መሰረተ ልማት መኖር ግድ ነው፡፡ ይህ ችግር እስኪፈታ ከመጠበቅ ይልቅ ከፀሐይ የሚገኝ ኃይልን በመጠቀም ራቅ ባሉ የገጠር ክፍሎች የሚኖሩ በርካታ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ጥሩ አማራጭ ነው” ብለዋል፡፡

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011

 በየትናየት ፈሩ