“ዛይሴ” በጋሞ ጎፋ

21

ከአርባ ምንጭ ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን፣ ኮንሶና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች የሚያቋርጠው አውራ መንገድ አልፈው የኤልጎንና የወዘቃ ቀበሌዎችን ዘልቀው ሲሄዱ ዓይንን የሚይዝ፣ ቀልብ የሚስብ ልዩ መልክዓ ምድር በግራና በቀኝ ይቃኛሉ፡፡ በዚህ ውብ በሆነው መልከአምድር ውስጥ የሚገኙት ደግሞ “ዛይሴ” ወይም “ዘይሴ ”ብሔረሰብ በመባል ይታወቃሉ። የዛይሴ ብሔረሰብ በጋሞ ጎፋ ዞን በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ኤልጎ፣ወዘቃ እና ዛይሴ ደንብሌ በሚባሉ የገጠር ቀበሌዎች የሚገኙ ናቸው።

ብሔረሰቡ በዋናነት የሰፈረባቸዉ ቀበሌዎች የመሬት አቀማመጥ የጫሞ ሐይቅ ዳርቻን የጋሞ ሰንሰለታማ ተራሮችንና የመጨረሻ ጫፍ ኮረብታማ አካባቢን ይዞ የሚገኘውን ለእርሻና ከብት እርባታ ምቹ የሆነ ለም መሬትን ሲያካትት፤የአየር ንብረቱ ደጋ፣ ወይናደጋና ቆላማ ነው።

ቋንቋ

በብሔረሰቡ አባላት ቋንቋቸው «ዘይሴቴ» ተብሎ ሲጠራ ሌሎች ደግሞ «ዛይሴኛ» ይሉታል። የዛይሴቴ ቋንቋ ከምሥራቅ ኦሞአዊ ቋንቋዎች ቤተሰብ ውስጥ የሚመደብ ሲሆን፤ ከጋሞና ከኮሬቲቴ ቋንቋዎች ጋር ይመሳሰላል። ሆኖም ቋንቋው ከመግባቢያነት አልፎ ለሌላ ተግባር አልዋለም።

ታሪካዊ አመጣጥና አሠፋፈር

የብሔረሰቡን ታሪካዊ አመጣጥና አሰፋፈር ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ ጎሳዎች በፈጠሩት የረጅም ጊዜ ማህበራዊ መስተጋብር የዛይሴን ብሔረሰብ እንዳስገኙ ይነገራል። እነዚህ ጎሣዎች በአካባቢው የሰፈሩትም ለእርሻና ለከብት እርቢ ምቹ፣ ለኑሮ ተስማሚ በመሆኑ ነው። በብሔረሰቡ በርካታ ጎሣዎች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህም መካከል “ቡቡር”፣ ”ብልዝና” “ማልዝ” ነባር ጎሣዎች ሲሆኑ የተቀሩት ከጋሞ፣ከደራሼ፣ ከሞሲዬና ከኮሬ በተለያዩ ጊዜያት መጥተው የተቀላቀሉ መሆናቸውን የብሔረሰቡ አዛውንቶች ይናገራሉ። ቀደም ባሉት መንግሥታት በሥራና በሰፈራ ምክንያት ከጋሞ፣ ከኮንሶ፣ ከወላይታ፣ ከጎፋና ከአማራ የመጡ ሕዝቦች ከብሔረሰቡ ጋር አብረው እንደሚኖሩም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ባህላዊ አስተዳደር

ዘይሴዎች የራሣቸው የሆነ ጥንታዊ ባህላዊ አስተዳደር አላቸው። የባህላዊ አስተዳደሩ ቁንጮ «ካቲ» ወይም ንጉሡ ይባላል፤ ካቲዎች የንግስና አመጣጥ ከጋሞ ኮሌ አካባቢ “ዝሄ” ከሚባል ሥፍራ “ከዙሌሣ” ጎሣ ነው። የካቲው ሥልጣን የዘር ሀረግን ተከትሎ ከአባት ወደ ልጅ በውርስ የሚተላለፍ ሲሆን ለመሪነት የሚያበቃው ገና ሲወለድ የእህል ዘር፣ እርጥብ ሣር ወይም የከብት እበት ይዞ ከእናቱ ማህፀን የሚወጣው ወንድ ልጅ ነው ተብሎ ይነገራል። ይህም በባህሉ “ኤቃ” የመልካም ገድ ተምሳሌት ነው ተብሎ ይታመናል። ከካቲው ልጆች መካከል የመጨረሻ ወይም ታናሽ እንኳን ቢሆን ከኤቃ ጋር ከተወለደ የካቲው ወራሽ ይሆናል። ወራሽ ልጅ መሪው ወይም ካቲው በሕይወት እስካለ ድረስ ከአባትየው ርቆ እንዲኖር ይደረጋል። ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቀሰው ወራሹ ከአባቱ ጋር ከኖረ ለአባትየው ሕይወት አስጊ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው።

ከባህላዊ መሪው በታች አቻ ሥልጣን ያላቸው በሕዝብ የሚመረጡ «ማጋ» የተባሉ ሰባት የሕዝብ መሪዎች አሉ። የማጋዎቹ ሥልጣንም እንደ ካቲው ሁሉ የዘር ሐረግን ተከትሎ ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ነው። ከማጋዎች ቀጥለው የሚገኙት የሥልጣን አካላት «ሶሮፋዎች» ሲባሉ ዋና ተግባራቸው ለበላይ መሪዎች የማማከር አገልግሎት መስጠት ነው። የሚመረጡትም በሕዝብ ሸንጎ ነው። በወታደራዊ አመራር ረገድ “ቶራ ቃራ” የሚባሉ የጦር አዛዦች እንደነበሩ ይነገራል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ባህላዊ አስተዳደር አካላት በአስተዳደሩ ማዕከል በሆነው “ማርታ” ወይም ቤተመንግሥት ዙሪያ በመሰባሰብ የፖለቲካ አስተዳደሩን ይመሩ ነበር። ንጉሡ የራሱ የጦር ሠራዊት አለው። በዚህ ጦር ውስጥ ዕድሜው 18 ዓመት የሞላው ወጣት ለካቲው ይሰጥና ወታደራዊ ሥልጠና ይወሰዳል። ከሥልጠናው መልስ ምሽግ በመቆፈር አካባቢውን በመጠበቅ ወታደራዊ ግዴታውን የመወጣት ኃላፊነት ይሰጠዋል።

በባህላዊ አስተዳደሩ የሴቶች ተሣትፎ ዝቅተኛ ነው። በቤትና በሸንጎ የመስተንግዶ ሥራን ከመምራት ውጪ የመዳኘት መብት የላቸውም። ይሁንና የካቲው ሚስት ባሏን በማማከር ትረዳዋለች። የሴቶች ምክርና ግሣፄ ይደመጣል። ምክንያቱም ግሣፄዋን የጣሰ ያሰበው አይሳካለትም ወይም አይሟላለትም ተብሎ ስለሚታመን ነው። በሌላ በኩል ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር አለመግባባት ሲከሰት “ኦጌማጋ” በሚባል አገናኝ አማካይነት በመላላክ “ዱላታ” /የሕዝብ ሸንጎ/ ተካሂዶ የዕርቅ ሥርዓት ይፈፀማል። ጉዳዩ ጠንከር ያለ ከሆነ በካቲውና በማጋዎች አማካይነት በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ይፈታል። በዚህም የተነሣ የዛይሴ ብሔረሰብ ከአጎራባች ብሔረሰቦች ጋር በርካታ ባህላዊ ጉዳዮችን ይጋራል። በአስተራረስ፣ በአለባበስ በሠርግና በለቅሶ ስርዓት አፈጻፀምና በሌሎችም ባህላዊ ወጎች ተመሳሳይነት አለው። ይሁንና ብሔረሰቡ ራሱን በራሱ ሲያስተዳድር ከነበረበት የቀድሞ ሁኔታ በውጫዊ ተጽዕኖዎች ምክንያት ባህላዊ አስተዳደሩም ሆነ ሌሎች ባህላዊ ዕሴቶቹ መዳከማቸው አልቀረም። በባህላዊ ሥርዓቱ ላይ ጫና ከፈጠሩበት ምክንያቶች የአፄ ምኒልክ የመስፋፋት ዘመቻ እና የጣሊያን ወረራ ለአብነት ይጠቀሳሉ።

የጋብቻ ሥርዓት

በብሔረሰቡ የጋብቻ ሥርዓት የሚፈፀመው በአቻ ጎሣዎች መካከል ነው። በአንድ ጎሣ ውስጥ የሚመደቡ እርስ በእርስ ጋብቻ አይፈፅሙም። በብሔረሰቡ ባሕል ሴቶች ፈፅሞ አይገረዙም፣ ወንዶች አልፎ አልፎ በስለት ወይም ቆንጨኮ (ወተት የሚወጣውን ተክል) በመጠቀም ግርዛት ይፈጽማሉ። ለጥሎሽ ጥንት በዓይነት እስከ ሰባት ከብት፣ ለልጅቱ ወላጆችና ቤተዘመድ ይከፈል ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የጥሎሹ መጠን በጥሬ ገንዘብ ከአንድ ሺ እስከ ሁለት ሺ ብር እንደደረሰ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የበዓላት አከባበር

ብሔረሰቡ ከሚያከብራቸው መንፈሳዊና ባህላዊ በዓላት “ደሴከሶ”፣ “ኤቃ”፣“አልሶ” “መስቀል”፣ “ገና” የተባሉት ተጠቃሽ ናቸዉ። “ደሴ ከሶ” በተመሳሳይ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በአማካይ ሥፍራ ተሰብስበው የብሔረሰቡ ባህል ወግና ታሪክ ለወጣቶች በብሔረሰቡ አዛውንቶች ይተረክላቸዋል። እነርሱም የታሪክ ተረካቢ መሆናቸው እየተገለጸላቸው ለክብረ በዓሉ ከተዘጋጀው ድግስ በጋራ እየበሉና እየተጫወቱ በአገሬው ሽማግሌዎች ይመረቃሉ። ይሄ በዓል የአንድ ትውልድ ስያሜ የሚያገኙበትም ነው።

“ኤቃ” መስዋዕት የማቅረቢያ በዓል ሲሆን በዚህ ሃይማኖታዊ በዓል “ማጋዎች” ለአካባቢያቸው ሰላምና ብልፅግናን በመሻት ፈጣሪአቸው “ኢንአ” ወይም “ማካ” በሚባሉ የባህላዊው ሥርዓተ አምልኮ ፈፃሚዎች አማካይነት ለብሔረሰቡ አምልኮት መስዋዕት በማቅረብ ፀሎት የሚያቀርቡበት ሥርዓት ነው። በአካባቢው ተፈጥሯዊ ክስተቶች እንደ ድርቅ፣ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ፣ ወዘተ… ሲከሰት ከዚህ መቅሰፍት እንዲታደጋቸው ካቲውና ማጋዎች በፀሎትና በምልጃ ለፈጣሪያቸው መስዋዕት የሚያቀርቡበት ሥርዓት ነው። የመስቀል በዓል ካቲውና ማጋዎች ለበዓሉ ተለይቶ በተዘጋጀ ሥፍራ ደመራ ደምረው ችቦ በማቀጣጠል የአካባቢው ሕዝብ እየበላና እየጠጣ በጭፈራ የሚያከብረው በዓል ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከክርስትና እምነት ጋር በተያያዘ የገናና የፋሲካ በዓላት በአካባቢው ብሔረሰብ በድምቀት ያከበራሉ።

ባህላዊ ጨዋታዎች

በባህላዊ ጨዋታዎች ረገድ ሴቶችና ወንዶች በአንድነት ተሰባስበው ሴቶቹ በስነ ቃል ጎሣቸውን ሲያሞግሱ ወንዶች በጭብጨባና በክራር በታገዘ እንቅስቃሴ ሽቅብ እየዘለሉ ይጨፍራሉ። ከሙዚቃ መሣሪያዎች ዋሽንት ወይም ሱልንጌ፣ ክራር ወይም ዝንቤ፣ ዛዬ የትንፋሽ መሣሪያ በራሣቸው ጥበብ በመሥራት ደስታቸውንና ሃዘናቸውን በሚገልጹበት ወቅት በማጀቢያነት ይጠቀሙበታል። ለዚህ ፅሑፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰቡ ላይ የተሠራ ጥናታዊ ጽሑፍ እና የተለያዩ ሰነዶችን በምንጭነት ተጠቅመናል፡፡ ሰላም!

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም

 በጋዜጣው ሪፖርተር