‹‹ዝቅተኛ የኤክስፓርት ቡና መሸጫ ዋጋ እንዲወሰን ለማድረግ የሚያስችል ልምድ ተገኝቷል››አቶ ዳሳ ዳንሶ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ግብይት ባለስልጣን የግብይትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር

109


ቡና የሀገራችን የውጭ ምንዛሬ ምንጭ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዋጋው በአለም ገበያ የሚወሰነው ይህ ሰብል ባለፉት ዓመታት የመሸጫው ዋጋ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ዘንድሮም እንዲሁ ዋጋው መቀነሱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ግብይትና ልማት ባለስልጣን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለቡና ዋጋ መውደቅ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህን ችግሮች ተቋቁሞ ቡና ተገቢውን ዋጋውን እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን የባለስልጣኑ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ግብይት ባለስልጣን የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳሳ ዳኒሶ ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ባለስልጣኑ የአጭር እና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ነድፎ የግብይቱን ደንቃራዎች ለማስወገድ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ይጠቅሳሉ፡፡ ከአቶ ዳሳ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

አዲስ ዘመን በተያዘው በጀት አመት ምን ያህል ቡና በመላክ ምን ያህል የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ታቅዶ ነበር ?

አቶ ዳሳ ዴንሶ በአመቱ 300 ሺ 420 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር፡ በዘጠኝ ወራትም 195 ሺ 574 ቶን ቡና በመላክ 706 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ገቢ ይገኛል ተብሎ ታቅዷል፡፡ በእነዚህ ወራት 151 ሺ 211 ቶን ቡና በመላክ 498 ነጥብ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተገ ኝቷል፡፡ አፈጻጸሙም በመጠን 77 በመቶ ሲሆን በገቢ ደግሞ 70 ነጥብ 8 በመቶ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ዘንድሮ ለአለም ገበያ የቀረበው ቡና ከፍተኛ ቅንሽ የታየበት መሆኑን ሰሞኑን የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፤ዋጋው የቀነሰባቸው አብይት ምክንያቶች ምንድን ናቸው ?

አቶ ዳሳ፡አለም አቀፍ የቡና ዋጋ በዚህ አመት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት ዋጋ ከ20 በመቶ በላይ ነው ቅናሽ ያሳየው፡፡ ምክንያቶቹ ውጪያዊና ውስጣዊ ናቸው፡፡

ለዚህ አንዱ ዋና ምክንያት ምርቱ ነው። አለም አቀፉ የቡና ምርት ከፍላጎቱ በተወሰነ ደረጃ ከፍ ብሎ ተገኝቷል፡፡ ይህ በመሆኑም ገዥዎች እጥረት እንደማይኖር ስላወቁ ተረጋ ግተው ለመግዛት ዋጋ ቀንሰው ያቀረቡበት ሁኔታ አጋጥሟል፡፡ ሁለተኛው አለም አቀፍ የቡና ግብይቱ በጥቂት ከፍተኛ ቡና ቆዪዎችና

 ቡና ነጋዴዎች ተጽእኖ ውስጥ መውደቁ ነው። በዚህ የተነሳም አንድ ኪሎ ቡና ከአንድ ስኒ ቡና ዋጋ በታች እየተሸጠ ነው፡፡

አለም አቀፉ ዋጋ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት በአሜሪካ ሳንቲም 20 በመቶ ቀን ሷል፡፡ ወደ ውጪ የሚላከው የቡና መጠንም እንዲሁ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ወደ አምስት በመቶ የመጠን ቅናሽ አሳይቷል፡ ፡ በገቢም 10 ነጥብ 9 በመቶ ቅናሽ አለው፡፡

ውስጣዊ ሁኔታዎችን ስንመለከት በቡና ግብይት የተሰማሩ አካላት የስነ ምግባር ጉድለት ይጠቀሳል፡፡ ላኪዎች እርስ በርስ ገበያ የሚሻሙበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ከገበያ ዋጋ በታች ዋጋ ዝቅ አርጎ በመሸጥ ወደ ተመሳሳይ ሀገሮች ይላ ካል፡፡ ይህም በብቃት ተደራድረን የተሻለ ዋጋ የምናገኝበትን እድል አጥቧል።

አዲስ ዘመን፡ቡና ከውጭ ምንዛሬ ጋር ይያያዛል፡፡ ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ውስጥ ትገኛለች፡፡ የውጭ ምንዛሬ የማግኘት እቅዳችሁን እንዴት ለማሳካት አስባችኋል ?

አቶ ዳሳ፡የቡና ሴክተሩ እንደ ሀገር ያለው ተልእኮ በተለይ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት አኳያ ከፍተኛ መሆኑን መስሪያ ቤቱ ያምናል። አመታዊ አቅዱን ሲያዘጋጅም አምና ከነበረበት የቡና ኤክስፖርት በመጠን በ26 በመቶ ገቢውንም በ30 በመቶ ለማሳደግ አቅዶ ነበር። ይህ ቢሳካ እንደ ሀገር በውጭ ምንዛሬ ግኝት የራሱን ድርሻ ማበርከት ይችል ነበር፡፡ ይሁንና ይህ ሊሳካ ግን አልቻለም፡፡

ምናልባት በቡና ኤክስፖርት ታሪክ

 አራተኛው ሩብ አመት ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት ለግብይት የሚወጣበት በመሆኑ የቅስቀሳ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ ከላኪዎችና በአጠቃላይ ከግብይት ተዋንያን ጋር በመሆን በቀሩት ወራት ለማካካስ የሚስችል ስራ ለመስራት አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

አዲስ ዘመን ስራዎቹ ምንድን ናቸው ?

አቶ ዳሳ፡ላኪዎች በእጃቸው ያለውን ኮንትራት ፈጥነው እንዲያወጡ ማድረግ አንዱ ስራ ይሆናል፡፡ የሎጂስቲክስ ችግሮችን ከአጋሮች ጋር በመሆን ለመፍታት ይሰራል፡፡ ለምሳሌ ለቡና ዝግጅት ከፍተኛ ድርሻ ያለው የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ እና አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ የቡና ምርት በሚወጣበት ወቅት የኮንቴይነር አገልግሎት ችግር ያጋጥማል፡፡

ሌላው ከአጭር ጊዜ በሁዋላ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች በሚዘጋጁ የቡና ኢግዚቢ ሽኖች ፣ኮንፈረንሶች ላይ ላኪ ድርጅቶችን በማስተባበር እየተሳተፍን እንገኛለን፡፡ በቅርቡ በአሜሪካ ቦስተን በተካሄደ መድረክ ተገኝተን ምርታችንን አስተዋውቀናል፡፡ በሩሲያም ባለፈው ወር ተመሳሳይ የቢዝነስ ፎረም በማዘ ጋጀት የቡና ኤክስፖርት እንዲያድግ የሚያስችሉ ተግባሮችን አከናውነናል፡፡

ከረጅም ጊዜ አኳያም ዘላቂ የገበያ እድል የሚያስገኙ አማራጮችን በመቅረጽ እየሰራን ነው፡፡ ከእነዚህም አንዱ ‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ›› የሚባል አለም አቀፍ የቡና ጥራት ውድድር ነው፡፡ ይህም በፊት በጥቂት ቡና አምራች ሀገሮች ብቻ ይካሄድ የነበረ ሲሆን፣ እንደ አዲስ በኢትዮጵያ የሚካሄድበትን አማራጭ በመፍጠር ቡናችን የተሻለ ዋጋ የሚያገኝበትን ሁኔታ ለመፍጠር ስራ ተጀምሯል፡፡ ለዚህም ከአዘጋጅ አለም አቀፍ ተቋማት ጋር ለመስራት ስምምነት ተፈራር መናል፡፡

አዲስ ዘመን፡ የቡና ዋጋ መውደቅ በሚያጋ ጥምባቸው ወቅቶች መንግስት የውጭ ምንዛሬ ግኝት እቅዱን ለማሳካት ይጠቀምበት የነበረው አንዱ አቅጣጫ ቡና በብዛት መላክ ሁለተኛ ደግሞ እጅ ውስጥ ያለውን ቡና በተገኘው ዋጋ እንዲወጣ ማድረግ ነበር፡፡ እነዚህ አሰራሮች አሁን ይተገበራሉ ?

 አቶ ዳሳ፡እርግጥ ነው፤ ባለፉት 13 አመታት የቡና ገበያ ዋጋ እየቀነሰ መጥቷል፡ ፡ አሁን ያለው የቡና ዋጋ የዛሬ 13 አመት እና ከዚያ በፊት ጋር ሲታያይ የሚመሳሰል ወይም የሚቀነስ ነው፡፡

መንግስት ቡና ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመፍታት በትኩረት መስራት ጀምሯል፡፡ በግብርና እና በንግድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሲመሩ የነበሩትን በአንድ ተቋም እንዲመሩ ነው ለማድረግ የቡናና ሻይ መስሪያ ቤትን እንደገና ያቋቋመው፡፡ መስሪያ ቤቱም ከተቋቋመ በኋላ የህግ ማሻሻያዎችን ጨምሮ እነዚህን ችግሮች የሚፈቱ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡

የኤክስፖርት መቀዛቀዝ በሚፈጠርበት ወቅት ዋና ዋና ላኪዎችን በማስተባበር በመቀስ ቀስ በዋጋቸውም ጭምር በመላክ በዋጋ መቀነስ ያጣነውን የውጭ ምንዛሬ በመጠን በብዛት በመላክ እንድናገኝ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ባሳለፍነው አመት የአለም የቡና ዋጋ በቀነሰበት ወቅት በመጠን የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ለማሳካት በተደረገው ጥረት በኢትዮጵያ የቡና ኤክስፖርት ታሪክ ትልቁ የሚባል መጠን 238 ሺ ቶን ቡና ተልኳል፡፡ ዘንድሮም ይህን ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

ከክምችት አኳያ አንደኛ ገበያው ሲቀዛቀዝ ዋጋቸውን ጭምር መሸፈን በማይችሉበት ሁኔታ ላኪዎች ቡናውን ይዘው ይቆያሉ፡፡ በ2010 መላክ የነበረበት ወደ 30 ሺ ቶን ቡና በዚህ አመትም በላኪዎችና በአንዳንድ አቅራቢዎች እጅ ይገኛል፡፡ ዘንድሮም በገበያ ዋጋ መውረድና አንዳንድ ላኪዎች ገበያ በማጣታቸው ሳቢያ በክምችት የሚገኝ ቡና አለ። በእዚህ ላይ እንደ ተቋም ብቻ ሳይሆን እንደ መንግስት መወሰድ ያለበት አቋም መወሰድ ይኖርበታል። ችግሮችን ለመፍታት በቀጣይ በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቋማችን አቅዶ እየሰራ ነው፡፡

 አሁን ያለውን ክምችት የሚቀንስበትን ሁኔታ ካላመቻቸን ክምችት እያለ መላክ የማንችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ሁለተኛ ይህ ክምችት እንዳለ ገዥዎች መረጃው ስለሚኖራቸው ፈጥነው ቡና የማንሳት እድልና ፍላጎታቸው ይቀንሳል፡፡ እጥረት ይኖራል ብለው በሚያስቡበት ሁኔታ ግን ፈጥነው ኮንትራት የመግባት እንዲሁም ኮንትራት የገቡትን የማንሳት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ክምችት ሲበዛ የገዥ አገሮች ኩባንያዎችም ጭምር የገቡትን ኮንትራት ጭምር በተለያዩ ምክንያቶች ሀገር ውስጥ እንዲዘገይ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር ለመፍታት በእጃችን ያለውን ክምችት ፈጥኖ አንድ አቅጣጫ ሊይዝ የሚችልበትን ሁኔታ በልዩ ሁኔታ ለማመቻቸት ተቋማችን አቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡አቅራቢዎች ከባንክ ብድር እየወሰዱ ነው የሚሰሩት፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ሲያጋጥሙ አሁን እያሉት ያለውን መምከር በባንኮች በኩል ድጋፍ የሚደረግበት ሁኔታ በሌለበት ሁኔታ አስቸጋሪ አይሆንም ወይ ?

አቶ ዳሳ፡ከስራችሁ ሽጡ የሚል ስራ አንሰራም፡ ፡ ቡና ሲከማች ጥራቱን እያጣ ይሄዳል፡፡ በመሆኑም ለሌላ ኪሳራ ይዳርጋል፡፡ ብዙ ትርፍ ሳይጠብቁ በዋጋው ጭምር የሚሸጡበትን መንገድ መከተል አንዱ ስልት ነው፡፡ አዋጁም ቡና ከአንድ የምርት ዘመን በላይ እንዲከማች አይፈቅድም፡፡ ስለእዚህ ከህግ አኳያ ጥሰት ስለሚሆን ቢያንስ የመግዣና የዝግጅት ወጪያቸውን በመሸፈን ብዙ ትርፍ ሳይጠበቁ እንዲሸጡ እናበረታታለን፡፡

በተለይ በአቅራቢዎች ደረጃ ዛሬም ቢሆን የባንክ ብድር አንድ ፈተና ነው፡፡ ብድር በሚፈለገው መጠን የማይገኝበት ሁኔታ አለ፤ ወለድ የሚበዛበት ሁኔታም አለ፡፡ ከዚህ አንጻር ቅሬታ ይነሳል፡፡ የኤክስፖርት ብድር አቅርቦት የጎላ ችግር የለበትም፡፡ ወለዱም በተነጻጻሪ አነስ ያለ ነው፤ ለአቅራቢዎች የሚቀርበው ብድር ግን ወለዱ ከፍ ያለና ለማግኘትም ውስብስብ ችግር ያለበት ነው፡፡ አቅርቦቱም ውስብስበና ማስያዣ (‹ኮላተራል) የሚጠየቅበትም ነው፡፡ እንደዚህ አይነት የገበያ መዋዠቅ ሲኖር አቅራቢዎችን የሚጎዳበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

አዲስ ዘመን፡ለዋጋ መውረድ ምክንያት የሆኑት የሀገር ውስጥና የውጭ ተግዳሮቶች እንዴት ይፈታሉ ብለው ያምናሉ፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት ምን እየተከናወነ ይገኛል ?

አቶ ዳሳ፡አለም አቀፍ ምክንያቱ እንዳለ ሆኖ የግብይት ተዋንያኑ ስነ ምግባር አለመጠበቅ ተጠቃሽ ችግር እንደሆነ አንስቻለሁ፡፡ አንዳንድ ላኪዎች ከገዙበት ዋጋ ቀንሰው በወረደ ዋጋ ለገበያ ያቀርባሉ፡ ፡ እነዚህ ላኪዎች የትርፋቸው ምንጭ ሌሎች አማራጮችን ያደረጉ ናቸው፡፡ ቡናው በዚህ አይነት መልኩ ሲሸጥ እንደ ሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እናጣለን፡፡

ሁለተኛ ሌሎች ተደራድረው በተሻለ ዋጋ እንዳይሸጡ እንቅፋት ይሆናሉ፡፡ ይህን ለመከላከል ከብሄራዊ ባንክ ጋር በዝቅተኛ ዋጋ የሚሸጡ አካላትን በማስጠንቀቅ እንዲያስተካክሉ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

ይህም በወሳኝ መልኩ ችግሩን ይቀርፋል ተብሎ ስለማይታመን እንደ ሌሎች አምራች አገሮች ዝቅተኛ የኤክስፖርት መሸጫ ዋጋ እንዲወሰን ማድረግ የሚያስችለንን አሰራር ከሎሎች አገሮች ልምድ አግኝተናል፡፡ በቡናም ሆነ በሌሎች ሰብሎች ዝቅተኛ የኤክስፖርት የመሸጫ ዋጋ ቢወሰን አገራዊ ጉዳት በሚያስከትል መልኩ በዝቅተኛ ዋጋ የሚሸጡ ላኪዎችን ለመቆጣጠር በሚል የውሳኔ ሀሳብ ለመንግስት ቀርቧል፡ ፡ ይህ ሲወሰን ቢያንስ በጣም በዝቅተኛ ዋጋ የሚሸጡ አካላትን መከላከል ይቻላል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

ሌላው ቡናችንን በአግባቡ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ተቋም እስከ አሁን የተሰራው በቂ ነው የሚል እምነት የለንም፡፡ ስለዚህ በማስተዋወቅ እና ብራኒድኒግ ስራችን ላይ ጠንካራ ስራ በመስራት የተሻለ ዋጋ የሚከፍሉ ገበያዎችን ማግኘት ይቻላል። እነዚህን ገበያዎች ሰብሮ ለመግባት የሚያስችል የማስተዋወቅ ገበያ ውስጥ ለመግባት በቂ ሀብት መመደብ ያስፈልጋል፡ ፡ ይህን ማድረግ እንደሚገባ አምነን አቅደን እየሰራን ነው፡፡

ቀደም ብዩ እንዳነሳሁት ‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ›› የሚባሉት የቡና ጥራት ውድድሮች ሲኖሩ የተሻለ ጥራት ያላቸው ቡናዎች በከፍተኛ ዋጋ የሚሸጡበት እድል ይፈጠራል፡፡ በውድድር ያሸነፉ በከፍተኛ ዋጋ ሲሸጡ ሌሎች ገዥ ድርጅቶችን የመሳብ እድል ስለሚፈጥር የተሻለ ገበያ ለመፍጠር እየተሞከረ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ቡና በዝቅተኛ ዋጋ የሚሸጡ ላኪዎች እንዴት አይነት ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ባለኝ መረጃ መሰረት አስመጪዎችም ይሁኑ በሌላ የንግድ ዘርፍም የሚሰሩ ሆነው የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሬ ለዚያ ስራ የሚያውሉ ናቸው ይባላል፡፡ ይህ ምን ያህል ትክክል ነው፤ የውጭ ምንዛሬን በዚህ መልኩ መጠቀምስ ይቻላል ወይ ?

አቶ ዳሳ፡በእርግጥ በመንግስት በኩል በቀጥታ አንድ ላኪ ድርጅት ልኮ ባስገኘው የውጭ ምንዛሬ ልክ ለገቢ ንግድ ያገኛል የሚል አሰራር የለም፡፡ በተዘዋዋሪ የምንሰማው ግን እነዚህ ድርጅቶች በወረደ ዋጋ ይሸጣሉ፤ ነገር ግን አይከስሩም የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ግልጽ ባልሆነ መልኩ በውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም ላይ ያሉ ችግሮች ለእዚህ መንስኤ ናቸው ብለን እንወ ስዳለን፡፡ እንደኛ በገቢ ምርት ለማካካስ እያሰቡ በዝቅተኛ ዋጋ ይሸጣሉ፡፤

ይህን እንዳያደርጉ በአለም ቡና ዋጋ ተመ ጣጣኝ ነው ተብሎ የሚታሰብ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ መወሰን ለእዚህ ተግዳሮት መ ሸጋሪያ ነው ተብሎ ታስ ቧል፡፡ ይህም በየጊዜው የሚከለስና ብዙ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ስራ ይሆናል፡፡

የሎጂስቲክስ አገልግሎቱ ከፍተኛ ወጪ ያለበት ነው፡፡ ተወዳዳሪነትን የሚቀንስ ነው። የእሴት ሰንሰለቱ መርዘም ሌላው ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ሊቀርፍ የሚችል የቡና ግብይት አዋጅ እና ደንብ ወጥተው መተግበር ጀምረዋል፡፡ ይህን በተሟላ መልኩ መሬት ላይ እንዲወርድ በማድረግ ችግሮቹን ለመፍታት እየሰራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ቡና በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ጥሩ ገበያ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ቡና የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ ከመሆኑ አኳያ ቡናው በዚህ መልኩ ሀገር ውስጥ መባከኑ በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አያሳርፍም ወይ ?

አቶ ዳሳ፡ሁለት አይነት ገጽታ ነው ያለው፡፡ ሀገር ውስጥ የሀገር ውስጥ የቡና ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑ በራሱ ችግር ነው ብዬ አልወስድም፡፡ ምክንያቱም የአለም የቡና ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ በሚቀንስበት በዚህ አይነቱ ወቅት በተለይ አምራቹ እንዳይጎዳ በመከላከልና ቡናችን ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ያደር ጋል፡፡ አምራቹ ከቡናው የሚያገኘውን ጥቅም እያየ ነው የሚያመርተው፡፡ ስለዚህ ከቡና ልማት እንዳይወጣ ብዙ ጠቅሞናል ብዬ አስባለሁ፡፡

በእርግጥ የሀገር ውስጥ ገበያው ወደ ውጪ ሊላክ የሚችል ቡናን ይሻማል፡፡ ሆኖም ግን በራሱ ችግር ስላልሆነ ለሀገር ውስጥም በቅቶ በፈለግነው ደረጃና መጠን መላክ የሚያስችለንን ልማቱን ማስፋፋትና ምርታማነትን መጨመር ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል እንጂ የሀገር ውስጡን እንደ ችግር መውሰድ አይገባም፡፡

አንዳንድ አገሮች ቡናቸው በሀገር ውስጥ እንዲጠጣ ጊዜ ሰጥተውና አቅደው ያስተዋውቃሉ፡፡ እኛ በታሪክ ያገኘነው የሀገር ውስጥ ቡና ገበያ የሚናቅ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሀገር ውስጡንም የውጪ ገበያውንም ሊመግብ የሚችል የቡና ምርታማነት ማረጋገጥ ላይ መስራት ይኖርብናል፡፡

አዲስ ዘመን፡የቡና ዋጋ መውረድ በአርሶ አደሩ በአቅራቢው በላኪው እና በቀጣይ ቡና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳርፍ ይታወቃል፡፡ በተለይ ከባንክ ተበድረው የሚያቀርቡት በጣም ሲጎዱ ይስተዋላልና ከዚህ አንጻር ዘንድሮ ከቡና ዋጋ መውደቅ ጋር ተያይዞ በእነዚህ ወገኖች የቀረበ ጥያቄ አለ ?

አቶ ዳሳ፡– አርሶ አደሩ አካባቢ አበረታች የቡና ክፍያ የለም፡፡ በተለይ ለጥራት የሚደረግ ክፍያ የለም፡፡ በዚህ የተነሳም ወደ ሌሎች ምርቶች ፊትን የማዞር ነገር እንዳለ ጥቆማዎች ይደርሳሉ፡፡

የአቅራቢዎች ጥያቄ ግን ጎልቶ መጥ ቷል፡፡ አቅራቢዎች ቡና ሲገዙ ሸጠው አይደለም፡ ፡ ከገዙ በኋላ የአለም የቡና ገበያ በሚፈጥረው እድል ነው ገቢያቸው የሚወሰነው፡፡ በአለም ገበያ ከፍ ያለ ዋጋ ሲኖር ይጠቀማሉ፤ ዝቅ ሲል ደግሞ ይጎዳሉ፡ ፡ ባለፉት አመታት ያጋጠመን አይነት የዋጋ መውደቅ ሲኖርና ሲገዙ በነበረበት ወቅት የነበረው ዋጋ በአለም ገበያ ሲሸጥ የሚቀንስ ከሆነ በተለይ በአቅራቢዎች ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ይህ በመሆኑም አቅራቢዎች የባንክ ብድራቸውን መክፈል እንዳልቻሉ ይገል ጻሉ፡፡

ይህን ተከትሎም በተደረጀ እና ባልተደራጀ መልኩ ለመንግስት እዳ ይሰረዝልን እስከሚል የሚደርስ ጥያቄ ባለፈው አመትም አቅርበው እየተከታተሉ ናቸው፡፡ ብድር እንዲራዘምላቸውም ይጠይቃሉ፡፡ ሲበደሩ ከፍተኛ ማስያዣ ይጠየቃሉ፡፡ ለኤክስፖርቱ እንደሚደረገው ዝቅ ተኛ ወለድ ያለው ፋይንናስ እንዲመቻችላቸው ይጠይቃሉ፡፡ የደረሰባቸው ኪሳራም በመንግስት የአሰራር ችግር የተፈጠረ መሆኑን በመጥቀስ እዳ ይሰረዝልን የሚል ጥያቄ በአቅራቢ ማህበራት በኩል ያቀረቡበት ሁኔታም አለ። በተለይ ብድር እጦት ላይ መንግስትም የተወሰነ ድጋፍ ያደረገበት ሁኔታ ቢኖርም፣ አሁንም በብድር እጦት ወደ ስራ ሳይገቡ የቀሩ አቅራቢዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡

አዲስ ዘመን፡ከቡና ጋር ተያይዞ እንደሌሎች አገሮች አርሶ አደሮች መንግስትን የሚያስጨንቀው ነገር የለም ?

አቶ ዳሳ፡አርሶ አደሮች የቡናቸው ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ የተሻለ የግብይት ስርአት ባላቸው አገሮች ኤክስፖርቱ ከሚያስገኘው ገቢ እስከ 94 በመቶው አምራቹ ዘንድ ይደርሳል። በኛ ሀገር የእሴት ሰንሰለቱ የተራዘመ በመሆኑ የማምረቻና የሎጂስቲክስ ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ የወረደ ዋጋም ኤክስፖርቱ የሚያስገኘው ገቢ አርሶ አደሩ ዘንድ የሚደርሰው ከ60 በመቶ በታች ነው፡፡

ይህ ደግሞ የማምረቻ ዋጋችንን የሚያካክስ አይደለም ሲሉ አርሶ አደሮች ይጠይቃሉ፡፡ አሁንም ችግሩ አልተፈታም፡፡ ስለዚህ እንደ ሀገር የኤክስፖርቱን ዋጋ ለማሳደግ የተለያዩ አዳዲስ አማራጮችን በመፍጠር በነባር ገበያዎች ያለንን የገበያ ድርሻ በማሳደግ በሚሰራው እቅድ ይህን ለመፍታት የሚያስችል እድል ይፈጠራል ብለን እናስባለን፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት አርሶ አደሮች ከኤክ ስፖርቱ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ለማድረግ በአዲሱ የቡና ግብይትና ቁጥጥር አዋጅ አርሶ አደሩ በቀጥታ ወደ ውጪ የሚልክበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ግን ብዙሃኑን አርሶ አደር መድረስ የሚያስችል አይደለም፤ በዚህ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት ጥቂት ሞዴል አርሶአደሮች ናቸው፡፡ በእርግጥ በማህበራት ሲልኩ መወዳደር የሚችሉበትን አቅም ይፈጥራሉ፡፤

ቡና ዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡ በዚህም አርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የእሴት ሰንሰለቱን የሚያሳጥሩ ስራዎች ይሰራሉ፡፡

በአጠቃላይ ግን በአለም ገበያ የቡና ዋጋ ዝቅተኛ እየሆነ ቢመጣም ጠባብ ሆነው

/ ስፔሻሊቲ ቡና/ የተሻለ ተጠቃሚ በሚያ ደርጉ ገበያዎቸ ላይ አቅዶ በመስራት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይቻላል፡፡ እንደ ሀሳብና እንደ አቅጣጫም የቡና ፈንድ ይቋቋማል የሚል እቅድ አለ። ይህ ሲቋቋም አርሶ አደሩ የሚሸጥበትን ዝቅተኛ ዋጋ በመወሰን አቅራቢው ለአርሶ አደሩ በመክፈሉ ሊያጋጥመው የሚችለው ኪሳራ የሚካካስበትን ሁኔታ ለመፍጠር ታስቧል፡፡ይህን አጠናክሮ መቀጠል የመፍትሄ አካል ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡ላደረጉልን ትብብር በጣም እናመስግናለን፡፡

አቶ ዳሳ፡እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2011

በኃይሉ ሣህለድንግል