ከ“ቡና ቡና”ኅብረ ዝማሬ በስተጀርባ

29

የአንድ አንድ ሰዎች ታሪክ በሥራቸው ውስጥ ይገኛል፤ የአንዳንዶች ደግሞ ሥራቸው እንዳለ ሆኖ ታሪካቸው በስማቸው ይጻፋል። የቀደሙት ስማቸው ሳይጠራ በሥራቸው ውስጥ የገነኑ ናቸው፤ እነርሱ ሳይሆኑ ሥራቸው የተዘመረለት። እንደውም በዓለማችን ላይ የሚበዙት እንዲህ ያሉት ሳይሆኑ አይቀሩም። እንደዛ ካሉት ሰዎች መካከል ዛሬ አንድ እንግዳ ይዘናል። እንግዳችን የቡና እና ሻይ ልማት በሚኒስቴር ደረጃ በነበረበት ወቅት እንዲሁም አሁን ላይ ማለዳ የቡና ገበያ ዳሰሳ ሲቀርብ የምንሰማው፤ ለጆሯችን አዲስ ያልሆነው ኅብረ ዝማሬ ደራሲ ናቸው።

«የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና፤ የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና…» ከዶሮ አኩኩሉ ጩኸት ቀጥሎ ይህ ኅብረ ዝማሬ የየማለዳው ዜማ ነው። የቡና እና ሻይ መሥሪያ ቤት የዕለቱን የቡና ገበያ ዋጋ ያሳውቅበታል፣ ይነግርበታል። ሕፃናት አፋቸውን የሚፈቱበት በጣፋጩ አንደበታቸው እያዜሙ ከእንቅልፋቸው የሚነቁበት አይረሴ መዝሙር ነው።

ይህ ኅብረ ዝማሬ አሁን ላይ አርባ ዓመታትን አስቆጥሯል። የዚህ ኅብረ ዝማሬ ዜማና ግጥም ደራሲ መምህር ታረቀኝ ወንድሙ ይባላሉ። በሥራ አጋጣሚ በጅማ ከተማ በተገኘሁበት ወቅት ነው የተዋወቅነው። ለቃለመጠይቅ ስቀርባቸው አላንገራገሩም። ስለራሳቸው ጥቂት፣ ስለሥራቸው ግን በርከት አድርገው አጫውተውኛል። በዛም መምህር ታረቀኝ ዛሬ በ“ሕይወት እንዲህ ናት” አምዳችን እንግዳችን ሆነዋል።

ልጅነት

ትውልዳቸው በጅማ ከተማ ነው። ጅማ የከፋ ክፍለ አገር ዋና ከተማ ሆና ባገለገለችበት ጊዜ ከነበሩት ስድስት አውራጃዎች መካከል መምህር ታረቀኝ ልጅነታቸውን በቤንች ማጂ አሳልፈዋል። አባታቸው ብርቱ ወታደር እናታቸው ደግሞ የቤት እመቤት ነበሩ። ይሁንና የወላጆቻቸው ትዳር ጸንቶ እስከ ፍጻሜው አልቆየም፤ ተለያዩ። በዚህም ምክንያት መምህር ታረቀኝ ልጅነታቸውን ከእናታቸው ጋር አድርገው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በማጂ ተከታተሉ።

የቤተሰባቸው ሁኔታ ከትምህርታቸው አላገዳቸውም። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህ ርታቸውን እንዳጠናቀቁ በጅማ ከተማ በሚገኝ ሚያዝያ 27 የሚባል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ሊከታተሉ እኩዮቻቸውን ተቀላቀሉ። በዚህም እስከ10ኛ ክፍል ድረስ ከቀጠሉ በኋላ ለሁለት ዓመት የመምህራን ሥልጠና ወሰዱ። ከዚያም አልፈው በመምህርነት ደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛም ገብተው ለሁለት ዓመታት ተምረዋል።

መምህርነት

«ዕድሜዬን በመምህርነት ነው የጨረ ስኩት።» የሚሉት መምህር ታረቀኝ፤ በመም ህርነት ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሥራ የገቡት በ1964ዓ.ም ነው። በሙያው ማገልገል የጀመሩት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርነት ነው። ታድያ አስተማሪ የሆኑት በአጋጣሚ አይደለም፤ ከልጅነት ጀምሮ ፍላጎቱ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ። ሲናገሩም ተከታዩን ብለዋል፤ «የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለን ጀምሮ የሚያስተምሩን መምህራን በማህበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ቦታና ክብር እንደነበራቸው አያለሁ።

በሥነ ምግባር የሚደነቁና እንደ አርአያ የሚታዩ ነበሩ። እኔም በዚያ ምክንያት መምህር የመሆን ፍላጎት ከልጅነት ጀምሮ ነበረኝ።» ታድያ ሥራቸውን እንደቀጠሉ ትምህር ታቸውን ችላ አላሉም። ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ ጅማ ዙሪያ ባሉ በወቅቱ አጠራር አውራጃዎች በሚገኙ በተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አተምረዋል። ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የዘለቁት ግን የትምህርት ደረጃቸውንም ከፍ ወዳለ ደረጃ ካደረሱ በኋላ ነው። ሙያውን እያሳደጉ ለመሄድና የራሳቸውንም እውቀት ለማሳደግ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መጀመሪያ በዲፕሎም ከዚያ ደግሞ በዲግሪ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተመርቀዋል።

ከዚህ በኋላ ነው በጅማ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር ሆነው መቀጠር የቻሉት። በኋላም ሳይዘናጉ ለሁለተኛ ዲግሪያቸው መማር ጀመሩ፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ። ለሁለተኛ ዲግሪ ወይም ለማስተርስ የመረጡት ቴፍል / Teaching in foreign language/ የሚባለውን የትምህርት ዓይነት ነው። በዚህም ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። ይህ ሁሉ ሲሆን ጎን ለጎን መምህርነታቸውንም እየሠሩ ነበር። ታድያ መምህር ታረቀኝ በድምሩ ከ1964ዓ.ም ጡረታ እስከወጡበት እስካለፈው 2006 ዓ.ም ድረስ በመምህርነት ሳይታክቱ አገልግለዋል። ይህም ሲሰላ ለ42 ዓመታት በመምህርነት ሙያ ሠርተዋል ማለት ነው።

የ«ቡና ቡና» ልደት

አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ አሉ መምህር ታረቀኝ የ«ቡና ቡና» ኅብረ ዝማሬን ልደት ቅድመ ነገር እያስታወሱ። ጅማ በየአውራጃዎቹ ሠርተው ቆይተው በ1969 ዓ.ም መጨረሻ ክረምት አካባቢ ወደ ጅማ መሃል ከተማ ተገኙ። ይሄኔ ለመስከረም 2 በዓል የአብዮት ሰልፍ ነበርና፤ ያንን በዓል ለማክበር በሰልፍ ደማቅ ትርዒትና ልዩ ልዩ ዝግጅት ይደረጋል። ትርዒቱን ለማቅረብ የተመረጡ ልጆች ልምምድ በሚያቀርቡበት «ኪቶ ኳስ ሜዳ» በሚባለው አካባቢ የሚደረገውን ልምምድ መምህር ታረቀኝ ተመለከቱ። «በቦታው እኔም የሚደረገውን ልምምድ ለማየት ስሄድ በተለይ ሕፃናቱ ደስ ይሉ ነበር።» አሉ በትውስታ።

እናም ትርዒት የሚያቀርቡት ልጆች እንደው ዝም ብለው ከሚሰለፉ መዝሙር ነገር እየዘመሩ ቢሆንስ ሲሉ ለራሳቸው አሰቡ፤ ቀጥለውም ሰልፉን ለሚመራና ለሚያስተባብር ሰው ይህንኑ ሃሳብ አቀረቡ። ሃሳቡን የሰሙት የሰልፉ አስተባባሪ የመምህር ታረቀኝን ሃሳብ አልተቃወሙም፤ ተቀበሏቸው። መምህር ታረቀኝም «እስቲ እኔው ላዘጋጅ» ይሉና፤ በቁጥር 30 የሆኑ ሴትና ወንድ ትንንሽ ልጆችን እንዲሰጧቸው ይጠይቃሉ።

እነዚህም ዕድሜያቸው ከ9-11ዓመት ያሉትን ልጆች «ለአብዮቴ…» የሚል ኅብረ ዝማሬ አዘጋጅተው አስጠናኋቸው። መስከረም 2 ቀን የአብዮት በዓል በጅማ ከተማ በድምቀት ሲከበር እነዚህ ልጆች ከሰልፉና ካቀረቡት ትርዒት ጋር ኅብረ ዝማሬውንም አሰሙ። በዓሉ ወደ ሚከበርበት ስታድየም ሲሄዱ በዚሁ ኅብረ ዝማሬ ታጅበው ነበር። ታድያ በዓሉ ካለፈ በኋላ ሌሎች ለኅብረ ዝማሬ የሚሆኑ መዝሙራትን እንዲያዘጋጁ ለመምህር ታረቀኝ ጥያቄ ቀረበ። ልጆቹም የተሠራውን ወድደውት ነበርና ጥያቄው የእነርሱም እንደነበር መምህር ታረቀኝ ያስታውሳሉ። በሂደትና በተገኘው አጋጣሚ እንዲህና እንዲያ እያሉ ሌሎች ዝማሬዎችን ጨማምረው ሠሩ። በኅብረ ዝማሬው ሰበብ የተሰባሰቡ ልጆችም በዚያው የኪነት ቡድኑ መሠረቱ።

ይህም ቡድን «ቦሳ 4 ቀበሌ ሕፃናት የኪነት ቡድን» ተብሎ የሚጠራ ነበር። የኪነት ቡድኑ ታድያ በጅማ ከተማ እንዲሁም አልፎ እውቅናን በሰፊው አገኘ። በተለያዩ አገር አቀፍ እንዲሁም የከተማ ዝግጅቶች ላይ ሕፃናቱ መምህር ታረቀኝ ያቀበሏቸውን ኅብረ ዝማሬዎች እያስደመጡ ድምቀት ሆኑ። በአንድ ወገን ተወዳጅነትን ሲያተርፉ በተጓዳኝ በተለያዩ ውድድሮችም አሸናፊ እየሆኑ ቀጠሉ። ይህ ከሆነ ከአንድ ዓመት በኋላ የቡና እና ሻይ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ጅማ ከተማ ላይ በሥራ ምክንያት ይገኛሉ። በትላልቅ አገር አቀፍ ዝግጅቶች ላይ የሚጋበዘው የቦሳ 4 ቀበሌ ሕፃናት የኪነት ቡድንም በዚያ ሚኒስትሩ በተገኙበት መድረክ ላይ ዝግጅቶችንና የተለያዩ ትርዒቶችን ብሎም ኅብረ ዝማሬዎችን ያቀርባሉ።

ይህን ልብ ብለው ያዩት ሚኒስትሩ፤ «ቡናን የሚመለከት አንድ ሥራ ቢሠሩ ጥሩ ነበር!» ሲሉ ከጎናቸው ለተቀመጡት የከተማዋ አስተዳዳሪ ሃሳባቸውን አቀበሉ። ይኸው ጥያቄ በማግስቱ በጅማ ከተማ አስተዳደር በኩል ለመምህር ታረቀኝ ቀረበ። መምህር ታረቀኝ እዚህ ላይ የኪነትን ትልቅ ሚና ሳያነሱ አላለፉም። ሲናገሩም ያሉት እንዲህ ነበር፤ «ያኔ ኪነት ትልቅ ሚና ነበራት። ደርግ ኪነትን በተለይ ለዓላማው ለመቀስቀስና ለማነቃቃት ተጠቅሞበታል።» ታድያ መምህር ታቀረኝ የቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ኅብረ ዝማሬ አዘጋጁ።

«የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና

የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና

የእድገታችን ገንቢ ቡና ቡና

አውታር ነው ቡናችን ቡና ቡና…»

በዜማ ተቀናብሮ በኢትዮጵያ ራዲዮ ጣቢያ ተቀረጸ። «ከ1971 ጀምሮ ያንን ኅብረ ዝማሬ ቡና እና ሻይ ልማት ወሰደ። ዘወትርም የጠዋት ጠዋት የቡና ዋጋ መግለጫ ሆኖ ይሰማል። እስከአሁን በመዝሙሩ እየተጠቀሙበት ነው።» አሉ መምህር ታረቀኝ።

የኅብረ ዝማሬና ሙዚቃ ፍቅር

መምህር ታረቀኝ እንደሚሉት ከሆነ ወደ ኪነት ሲገቡ አርአያ ሆኗቸው የተከተሉት ሰው አልነበረም። «ወደ ኪነት ለመግባት ሮል ሞዴል የሆነኝ የለም። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት አውራጃ ላይ ነው። ጅማ ከተማ ላይም ቢሆን ሚያዝያ 27 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለስድስቱም አውራጃ አንድ ነበር።» ይላሉ። እንግዲህ ብዙ የቀረበ አማራጭ ባልነበረበት ጊዜ ነው መንገዳቸውን ፈልገው ለማግኘት ያልተቸገሩት። ነገር ግን የመምህራኖቻቸውን አስ ተዋጽኦ አይዘነጉም። ይልቁንም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳሉ መምህራኖቻቸው ቴአትር እየጻፉ ልጆች እንዲተውኑ በማ ድረግ፣ ነባር ሙዚቃዎችን በማስጠናትና በማዘጋጀት ተማሪዎች እንዲዘፍኑና መድረክ ላይ እንዲያጅቡ በማበረታታት በኩል ወደር የሌላቸው እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

 ከዚያ በተረፈ በሙያው በተለይም በኅብረ ዝማሬ ሥራ ላይ በቅርበት የሚያዩት አርአያ በሌለበት፤ ዘመን የተሻገረ ሥራን ሊሠሩ የቻሉት አስቀድሞም በውስጣቸው የኪነጥበብ ስሜት ስለነበረ እንደሆነ ያምናሉ። ያንን ስሜት በማውጣት እየሠሩ ራሳቸውን በሂደት ከፍ ማድረጋቸውንና ማደጋቸውንም ያነሳሉ። ከዚያ በተረፈ በግላቸው እነዚህን ሥራዎች ይሥሩ እንጂ፤ በጥቅሉ ለጥበባዊ ክዋኔዎች ፍቅር አላቸው። ጅማ ከተማ የሚዘጋጁና የሚመጡ ጥበባዊ ሥራዎችን በተገኘው አጋጣሚ ይመለከታሉ፤ ፊልምና ቴአትርም እንደዛው። «ችሎታ በውስጤ እንዳለ ግን አላውቅም ነበር። ለአብዮቱ በዓል ያችን አንዲት መዝሙር ሠርቼና ግፊቱ ሲያይል እየጨመርኩ ስሠራ ነው አቅሙ እንዳለኝ ያወቅኩት።» ብለዋል።

ከዚያ በኋላ ነው የተባሉትን ሥራዎች ሁሉ የሠሩት። በኑሮ በእንቅስቃሴአቸውም ሳይቀር ዜማና የግጥም ሃሳብ እየመጣላቸው ያንን እየቀዱና እያሰፈሩ ቀጥለዋል። ኪነት ቡድኑ እስኪፈርስ ድረስም ሳይታክቱ አገራቸውን በሙያቸው አገልግለዋል። ይህም ሁሉ ሲሆን የሙዚቃ መሣሪያ በአግባቡ ኖሯቸው አይደለም። ኪነት ቡድኑ በትኩስ ኃይል ሥራውን የጀመረ ጊዜም በእጃቸው የነበረው ጊታር ብቻ ነበር። መምህር ታረቀኝም ከሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ከበሮ ነበርና እርሱን ይዘው ነው ኅብረ ዝማሬዎች በራዲዮን እንዲተላለፉ ለማስቻል ይቀርጹ የነበሩት።

ያኔም ግጥምና ዜማ ከማዘጋጀት ባሻገር ከበሮውን በመያዝ በኩል ተሳትፎ ነበራቸው። ይህም የሆነው የኪነት ቡድኑ አባላት ያሉትን መሣሪያዎች አውቀው መጠቀም እስኪችሉ ነበር።

ኅብረ ዝማሬ ድሮና ዘንድሮ

ኅብረ ዝማሬዎች አንድ ሰው ብቻውን ከሚያሰማው ሙዚቃ የተለየ ጣዕምና ተደማጭነት አላቸው። በአገራችንም ሆነ በዓለም መድረክ ላይ፤ የጋራ ጥሪን ለማቅረብም በጋራ የቀረቡ ዝማሬዎች የበለጠ ተጽእኖ ፈጣሪ ሆነው ማየት ችለናል። አሁንም ቢሆንም አልፎ አልፎ ጣል እየተደረጉ የምንሰማቸው ኅብረ ዝማሬዎች አሉ። ይሁንና ዛሬ ላይ እንደ ቀደመው ጊዜ ኅብረ ዝማሬን በብዛት ለመሥራት አስቸጋሪ እንደሚሆን መምህር ታረቀኝ ይናገራሉ። ይህንንም በአንድ ወገን ከአገር ፍቅር ጋር ያገናኙታል። «አፌን ሞልቼ የምናገረው ያኔ በአብዛኛው ሰው ዘንድ የአገርና የወገን ፍቅር ስሜት አለ።» አሉ። ያኔ እንደ አሁኑ ለትንሽ ለትልቁ ገንዘብ አይጠየቅም ነበር። አሁን ላይ ግን ይህ ጥያቄ ቀድሞ የሚነሳ በመሆኑ ብዙዎች የሚሳተፉበት ኅብረ ዝማሬ ለሰዎች ለማቅረብ ከባድና ፈታኝ ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ያቀርባሉ። ኅብረ ዝማሬ ለመሥራት ከግጥምና ከዜማ ሥራው ውጪ ብዙ ገንዘብ ሊጠይቅ ይችላል ባይ ናቸው።

ያ ካልተሟላ ደግሞ ጊዜውን ሰጥቶ ከልቡ የሚሠራ ሰው ማግኘት ከባድ ይሆናል። ምንአልባት እንደያኔው «ምን ሠርቼ ለአገሬ አንዳች ነገር ላበርክት» የሚባልበት ጊዜ ከመጣ ግን በጥሩ ሁኔታ ሊሠራ ይችላል። «ቡና ቡና» የተሠራበት ጊዜ ግን የልጆቹ ክፍያ እውቅና፣ ሽልማትና ክብር ነበር እንጂ ሌላ አይደለም። ይህን ይበሉ እንጂ ሰው ከሥራው መጠቀም የለበትም ማለት እንዳይደለም አያይዘው ተናግረዋል። በተለይም ከ«ቡና ቡና» ኅብረ ዝማሬ ጋር አያይዘው፤ መዝሙሩን ከ1971ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ቡና እና ሻይ ለማስታወቂያ እየተጠቀመበት መሆኑንና ለእርሳቸው ግን ምንም ዓይነት ክፍያ አለመደረጉን አያይዘው ጠቅሰዋል።

በተለይም አሁን ላይ እየሠራ ባለው ሕግ መሠረት የጥበብ ሥራን ለገቢ ማስገኛ ካዋለው የሚከፍለው ክፍያ አለ። በዚህ መሠረት ከሆነ ታዲያ እርሳቸው በበኩላቸው ተጠቃሚ እንዳልሆኑ በቁጭት ይጠቅሳሉ። መዝሙሩን ለማስታወቂያነት የሚጠ ቀምበት ተቋም ሲሆን እኚህን ሰው አስቦና ያለ ጠያቂ አመስግኖና እውቅናን ሰጥቶ የሚገባውን እንዲያደርግ ይጠበቃል። ያ ባለመሆኑ ግን መምህር ታረቀኝ «ሄደህ አትጠይቃቸውም ወይ?» እያሉ መሥሪያ ቤቱን እንዲጠይቁ የገፋፏቸውን የቅርብ ሰዎቻቸውን ምክር ሰምተው ወደ ቡና እና ሻይ ተቋም አምርተው ነበር።

 በዚያም ኃላፊዎችን አነጋግረዋል፤ ቃላቸውንም ተቀብለዋል። ይሁንና ጊዜ ጊዜን እየተካ ዓመትም ዓመትን እየወለደ ይህን ታሪካቸውን እስካጫወቱን ጊዜ ድረስ የተሰጣቸው መልስ የለም። ቤተሰብ መምህር ታረቀኝ ገና ሥራ እንደጀመሩ አካባቢ ወጣት ሆነው ነው ትዳር የመሠረቱት። እንደውም ለሥራ ወደ ተመደቡበት አውራጃ ሲሄዱም ባለቤታቸውን ይዘው ነበር። በዚህም ትዳር አራት ልጆችን አፍርተናዋል። ይሁንና በተለያየ ምክንያት ትዳራቸው ፈርሷል። ኑሯቸውንም በየፊናቸው ሲቀጥሉ የጋራ የሆኑ ልጆቻቸው ደርሰው የልጅ ልጆች አሳይተዋቸዋል።

ቤተሰቦቻቸው በዚህም ሁኔታ ሆነው ሙያቸውን እንደሚደግፉና ብርታት እንደ ሚሆኗቸውም ያነሳሉ። እንኳንና የቅርብ የስጋ ዝምድና ያላቸው ቀርቶ የሚያውቋቸው የአካባቢያቸው ነዋሪዎች ሳይቀሩ በእርሳቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ነው የሚገልጹት። ይህንንም ሲገልጹ ከገጠመኞቻቸው መካከል አንዱን እንዲህ ያስታውሳሉ፤ ይህም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አርሂቡ ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆነው የቀረቡ ጊዜ ነበር። ይህን ቀድመው ያወቁ ተማሪዎቻቸው ለቤተሰቦቻቸው ነግረው ዝግጅቱን አምሽተው ተመለከቱ።በማግስቱም መምህራቸውን እያጨበጨቡ ተቀበሉ። በመምህራቸው የተሰማቸውንም ኩራት ተናገሩ።

ይሁንና ከስም ውጪ ያተረፉት አለመኖሩ በቅርበት የሚያውቋቸውም የሚናደዱበት ጉዳይ መሆኑን መምህር ታረቀኝ ይናገራሉ። «እኔ አሁን በሰው ሳይሆን በዕድሌ አዘንኩ። የረባ ነገር ያልሠራ ሰው ሁሉም ይሟላለታል፤ እኔ አቤት ብዬም ምንም ነገር አላገኘሁም።» አሉ በቁጭት። መምህር ታረቀኝ ያኔ ለአገርና ለአብዮት መሥራት እንጂ «ይህን ስጠኝ ወይም ያንን ክፈለኝ» የሚባል ነገር እንዳልነበረ ያስታውሳሉ። በዚህም መሠረት ከኪነት ቡድኑ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከቡና ቡና ውጪ ከስልሳ በላይ የኅብረ ዝማሬ ሥራዎች አሏቸው፤ ግጥም ጽፈዋል፣ ዜማ ፈጥረዋል። እነዚህ ሥራዎች አሁን ላይ እየተሰሙ አለመሆኑም ያስከፋቸዋል። ከሥራዎቻቸው መካከል «ለዓለም ሰላም»፣ «አለ ገና»፣ «እንሂድ» ወዘተ የሚሉ ሥራዎቻቸውን በጊዜው አቅርበዋል።

የራዲዮን ጣቢያዎች ዛሬ ላይ በታሪክ ያንን እያነሱ ቢሠሩ ደስ እንደሚሰኙም ይናገራሉ። እነዛ ሥራዎች ዘመን ተሻጋሪ የሚሆኑና ጊዜ የማይገድባቸው አልያም በትንሹ እርማት ተደርጎባቸው መቅረብ የሚችሉ መሆናቸውን ነው የሚገልጹት። በነገራችን ላይ የ«ቡና ቡና»ን ኅብረ ዝማሬን ያህል፤ የኅብረ ዝማሬው ደራሲና አዘጋጅ መምህር ታረቀኝ አይታወቁም። ደራሲው እርሳቸው መሆናቸው የታወቀበትን አጋጣሚ ሲያስታውሱም እንዲህ ነበር ያሉት፤ «እኔ የኅብረ ዝማሬው ደራሲ መሆኔን የሚያውቅ አልነበረም፤ ማን እንደደረሰው አይታወቅም ነበር። ነገር ግን 2000ዓ.ም ላይ በጅማ ሚሌኒየሙ ሲከበር መምህራንም በጋራ አክብረን ነበር።

በዚያም የበዓል መድረክ ላይ ሥነጽሑፍ እሞካክራለሁና አንድ ግጥም አቀረብኩ። አቀራረቤን ወደውት ነበር። በአጋጣሚ ለቀረጻው ከአዲስ አበባ የመጡ ጋዜጠኞች “ማን ነው?” ብለው ሲጠይቁ የሚያውቁኝ ሰዎች “ቡና ቡና” የተሰኘውን ኅብረ ዝማሬ ማዘጋጀቴን ነገሯቸው። ይህንንም ሲያውቁ ጋዜጠኞቹ አነጋገሩኝ።» ብለዋል። መምህር ታረቀኝ አሁን ላይ ከመምህርነት ሥራቸው በጡረታ ተሰናብተዋል።

በዕድሜ ጫና ምክንያት ደግሞም ጡረታ መውጣት የግድ ነውና ከመምህርነት እንዲገለሉ ግድ እንዳላቸውም ነው የነገሩኝ። ይሁንና ሥራ ትተው አልተቀመጡም፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። እኛም ዕድሜና ጤናን እየተመኘን፤ ጥሪና ጥያቄአቸውም አቤት ባይ እንደሚያገኝ ተስፋ እያደረግን በዚህ እንሰናበት። ሰላም!

አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2011

ሊድያ ተስፋዬ