ከስሜት ይልቅ ለምክንያታዊ አስተሳሰብ እንገዛ

24

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የቆየ አብሮ ተሳስቦና ተከባብሮ በጋራ የመኖር አኩሪ ባህል ያለን ህዝቦች ነን። በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ዘልቆ ያልተጋባ፣ ያልተዋለደና ያልተቀየጠ ህዝብ የለም። ይህ የሚያሳየው በደም መተሳሰራችንን ነው። ይሁንና አሁን መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ስናይ ይህ ውህደታችንና አንድነታችን ቀስ በቀስ እየተሸረሸረና ልዩነቶቻችን እየሰፉ ‹‹እኛና እነርሱ›› የሚል አጥር ተበጅቶ አንዱ ሌላውን ማጥቃት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ከዚያም አልፎ ችግሩን ለማስፋት የሚደረጉ አስተያየቶችና ጉንተላዎችም በየቦታው በዝተዋል፡፡

በሚዲያውና በተለያዩ መድረኮችም ‹‹ይህ የኛ ነው፣ እናንተ መጤ ናችሁ…›› ወይም ‹‹አይነት ካልሆንን አንድ አይደለንም›› የሚለው አስተሳሰብ የዚህ ትልቅ ማሳያ ነው። መነሻና ምንጩም በምክንያታዊነት ላይ ያልተመሰረተ ጭፍን ጥላቻ ነው። ይህ ደግሞ ስሜትን አግሎና አንሮ እዚህም እዚያም ህይወት እንዲጠፋና ዜጎች ለአመታት ከኖሩበት ቀዬ እንዲፈናቀሉ አድርጓል። እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ የኛ ባህል አልነበረም፡፡

እንዲህ አይነት ድርጊት ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ካዳበሩት አብሮ የመኖር ባህልና የማህበራዊ ህይወት መስተጋብር በእጅጉ ተጻራሪ ነው። በህብረተሰቡ ውስጥ በስፋት የነበረው ምከንያታዊነትና አስተዋይነት የተላበሰው እሴት ለምን ተዳከመ? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ግን ዝርዝር ጥናት ይፈልጋል። ምክንያታዊ ለመሆን በቅድሚያ አዕምሮን ክፍት አድርጎ ጥቂት ማሰላሰልን ይጠይቃል። ከዚህም ባሻገር በነጻነት ማሰብን፣ ሚዛናዊነትን፣ የምንሰማውን ነገር ሁሉ ከመጠቀማችን ወይም ለድርጊት ከመነሳታችን በፊት ማገናዘብን፤ ወዘተ ይጠይቃል፡፡

ከማሰብና ማስረጃንና መረጃን መሰረት አድርጎ ሀሳብን ከመዳሰስ፣ ከመፈተሽ፣ ከመመርመር፣ ከመሞገት፣ ከማውጣትና ማውረድ ጋርም በእጅጉ የተያያዘ ነው። ምክንያታዊነት ከእሴትና ሞራላዊ ጉዳዮች፣ ለእውነትና ለፍትህ ወግኖ ከመቆምና ከመቆርቆር ፣ ከመቻቻልና ከመከባበር፣ ሰውን በሰውነቱ ከመመዘንና ዋጋ ከመስጠት ጋር ይቆራኛል። በአንጻሩ ዘርን፣ ቋንቋን፣ ሃይማኖትን፣ ጾታን፣ ወዘተ መሰረት አድርጎ በሰዎች መካከል ልዩነት መፍጠር፣ መጠቃቀም ወይም በእነዚህ ልዩነቶች ላይ በመመርኮዝ መጠቃቃት ምክንያታዊነትንና አርቆ አሳቢነትን አያመለክትም።

ምክንያታዊ ስንሆን ግጭት፣ ንትርክ፣ በጭፍን መጠላላት፣ ጠመንጃ ማንሳትና መገዳደል፣ መጎዳዳት ወዘተ አይኖርም። የሚያስፈልገን የሀሳብ ልእልናና የአስተሳሰብ የበላይነት ነው። ይህ ደግሞ እውን የሚሆነው ጤናማ በሆነ ውይይትና በመደማመጥ ላይ በተመሰረተ ንግግር ነው። ምክንያታዊነት ሰውን በሰውነቱ፣ በአስተሳሰቡና በማህበራዊና ፖለቲካዊ የህይወት እንቅስቃሴ ውስጥ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ የሚመዝን እንጂ በደም፣ በጎጠኝነት፣ በቡድንተኝነት ወይም በመጠቃቀም ላይ የተመሰረተ የእከክልኝ ልከክልህ ግንኙነት አይደለም።

ያለምክንያታዊነት፣ ያለሚዛናዊ ሀሳብና ያለ መርህ በሚመራ ግንኙነት ውስጥ አይሎና ገዝፎ የሚንጸባረቀው ስሜታዊነት እንጂ ምክንያታዊነት አይደለም። ከምክንያታዊነት ስንርቅ ስሜታችን ለጅምላ ፍረጃ ቅርብ ይሆናል፡፡ ብዙዎቻችን በጭፍን ድምዳሜ እንዋጣለን፡፡ አንድን ነገር ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ መርምረን፣ በምክንያት ተንትነን እንዲሁም መረጃና ማስረጃ አቅርበን እውነታው ላይ መድረስ ሲገባን በስሜት ብቻ እንጓዛለን፡፡

አብሮና ተሳስቦ መኖርንም ዋጋ እናሳጣዋለን። ባስ ሲልም የመንጋ ፍትህ እንሰጣለን፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ሚዛናዊ አስተሳሰብና ሰብአዊነት ተሸርሽሮ ጠባብነትና ራስ ወዳድነት ሲናኝ ነው። ይህ ችግር በፖለቲካ ፓርዎችም ውስጥ በስፋት ይንፀባረቃል፡፡ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ርእዮተ አለማቸውን ለህዝቡ በማሳወቅና በማስረዳት ደጋፊዎችን ከማፍራት ይልቅ አባሎቻቸውን በስሜት ቆስቋሽ ጉዳዮች በመጥመድ ደጋፊን በማብዛት ላይ ስለሚያተኩሩ የህዝቡን ንቃተ ህሊና ከፍ በሚያደርጉ ሃሳቦች፣ በህዝቡ ችግሮችና በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ በሰከነ መንገድ የሚካሄዱ ንግግሮችና ውይይቶች አነስተኛ ይሆናሉ።

ሀሳብና ምክንያታዊነትን የሚያበረታታ ሁኔታ በሌለበት ስፍራ ደግሞ ቦታውን የሚይዘው ግጭት፣ ንትርክ፣ አሉቧልታና ውዝግብ ነው። ምክንያታዊ ብንሆን አሁን ላይ እንደሚታዩት ንትርክ፣ ግጭትና መፈናቀል ባልተከሰተ ነበር። ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ በርካታ ችግሮች ያሉባት ሀገር ናት። በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ በርካታ የልማት ጥያቄዎች አሉ። በአንጻሩ ደግሞ ዓለም መጥቃ በብዙ ርቀት ጥላን ሄዳለች።

ስለሆነም ባሉት ችግሮችና ጥያቄዎቻችን ላይ በመወያየት ወደ እውነቱና ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ወደሚያጠናክረው መንገድ ተያይዘን መጓዝ ከሁላችን ይጠበቃል። ከምክንያታዊነት በራቀ ሁኔታ ጫፍና ጫፍ ይዘን መሄድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ስለሆነም ለችግሮቻችን መፍትሄ ሰጪዎቹ እኛው እንደሆንን አምነን ለዚሁ በሙሉ ልብ እንነሳ፡፡

አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2011