የመኸር እርሻና የማዳበሪያ አቅርቦት ዝግጅት

17

ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በመጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን ምርት ከአመት አመት እያሳደገች ትገኛለች፡፡ በዚህም የግብርናውን ምርት በ2010/2011 የምርት ዘመን ከ306 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማድረስ ችላለች፡፡ ይህን የምርት መጠን በ2011 /2012 የምርት ዘመን ከ406 ሚሊየን ኩንታል በላይ ለማድረስ ታቅዷል፡፡

የአነስተኛ አርሶ አደሮች የመኸር ሰብል ምርት በ2002 ከነበረበት 180 ሚሊዮን ኩንታል በ2007 ወደ 270 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል ማደጉም ለእዚህ አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የምርት አፈፃፀም በመጀመሪያ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን ተቀምጦ የነበረውን የዘርፉን መሠረታዊ የዕድገት አማራጭ ያሟላ እና አገራችን በምግብ ሰብል ራሷን እንድትችል ያስቻለ ነው፡፡

ሀገሪቱ የግብርናውን ምርትና ምርታማነት አሁንም ማሳደግ እንደሚኖርባት ይታመናል፡፡ ከህዝቧ 85 በመቶው አርሶ አደር እንደመሆኑና የኢኮኖሚው መሰረት አሁንም በግብርናው ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ የዘርፉ ምርትና ምርታማነት ማደግ አለበት፤ ሀገሪቱ አንደ ሀገር የምግብ ዋስትናዋን ብታረጋግጥም፣ በቤተሰብ ደረጃ ገና ብዙ መስራት የሚኖርባት እንደመሆኑም የምርትና ምርታማነቱ ማደግ አስፈላጊነት አያጠያይቅም፡፡

ሀገሪቱ ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ለያዘችው ራእይም የግብርናው ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይታመናል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች እየገነባቻቸው የሚገኙት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችም ግብአታቸውን የሚያገኙት ከእዚሁ ከግብርናው ዘርፍ ነውና የምርትና ምርታማነቱ ማደግ ወሳኝ ይሆናል፡፡

ለዚህም ግብርናውን ማዘመን ያስፈልጋል፡፡ ለዘመናዊ ግብርና በእጅጉ አስፈላጊ ከሆኑት ግብአቶች መካከል አንዱ ማዳበሪያ ነው፡፡ ሀገሪቱ ይህንን ማዳበሪያ የምትጠቀመው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ መድባ ከውጭ በማስገባት መሆኑ ይታወቃል።

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብአት ግብይት ዳይሬክቶሬት በግዢ የሚቀርቡ የግብርና ግብአቶች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘውዱ ስሜ እንደገለጹት፤ የሀገሪቱ የማዳበሪያ ፍላጎት ከአመት ወደ አመት እያደገ መጥቷል፤ የሚታረሰው መሬትና የአጠቃቀም ስልቱም እንዲሁ እያደገና ዘመናዊነትን እየተላበሰ ነው፡፡

በ2011 /2012 የምርት ዘመን እንደ ሀገር የሚያስፈልገው የማዳበሪያ መጠን ካለፈው የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር በ14 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ እንደሚጨምር ይገመታል፡፡ ያለፉት አመታት አፈፃፀምም ይህንኑ ያመለክታል። በ2008 አ.ም ሀገሪቱ 818 ሺ 217 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ተጠቅማለች፡፡ ይህ ፍላጎት በ2009አ.ም ወደ አንድ ሚሊየን 85 ሺ ሜትሪክ ቶን፣ በ2010 አንድ ሚሊየን 127 ሺ ሜትሪክ ቶን ደርሷል፡፡ በ2011 አንድ ሚሊየን 600 ሺ ሜትሪክ ቶን ይሰራጫል ተብሎ ይጠበቃል ።

በ2010/11 ምርት ዘመን የምርት ዘመን ያደረና ከውጪ አዲስ ተገዝቶ የገባውን ጨምሮ 1 ሚሊየን 598 ሺ 926 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ለምርት ዘመኑ ቀርቦ ነበር፡፡ ከዚህም ውስጥ አጠቃላይ ለበልግ፤ ለመኸርና ለመስኖም ጨምሮ 1 ሚሊየን 127 ሺ 111 ሜትሪክ ቶን አገልግሎት ላይ ውሏል፤ 332 ሺ 264 ሜትሪክ ቶን ግን አድሯል።

ያደረውን ጨምሮ በ2011/12 የምርት ዘመን አንድ ሚሊየን 613 ሺ 246 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ይሰራጫል ተብሎ ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅትም አንድ ሚሊየን 278 ሺ 982 ሜትሪክ ቶን ከውጪ ለማስገባት እቅድ ተይዞ እስካሁን እንድ ሚሊየን 175 ሺ ሜትሪክ ቶን የማዳበሪያ ግዢ ተከናውኗል፤ ይህም የእቅዱ 92 በመቶ ነው፡፡

በቅርቡ ተጨማሪ ግዢ ለማከናወን ጥያቄ በመቅረቡም በአሁኑ ወቅት 100 ሺ ሜትሪክ ቶን የማዳበሪያ ግዢ ታዟል፣ ባጠቃለይ እስካሁን አንድ ሚሊየን 27 ሺ 847 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ሀገር ውስጥ ገብቷል።

ወደብ የደረሰውን ማዳበሪያ ለየክልሉ ብሎም ለአርሶ አደሩ ለማድረስ የትራንስፖርት እጥረት አለ የሚሉት ባለሙያው። ይህንን ችግር ለመፍታት የተለያዩ የማጓጓዣ መንገዶች ስራ መዋላቸውን ያመለክታሉ፡፡

እንደ አቶ ዘውዱ ገለጻ፤ የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴርና የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች በየሳምንቱ በመገናኘት እየተወያዩ ለችግሮችም የመፍትሄ አቅጣጫ እያስቀመጡ ይገኛሉ። በዚህም መሰረት በቅርቡ አጋጥሞ የነበረውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል ለሁሉም ድንበር ተሻጋሪ አንደኛ ደረጃ ተሽከርካሪዎች ጥሪ በማስተላለፍ ማዳበሪያ እንዲጭኑ ተደርጓል፤

ይህም ሆኖ በአቅርቦቱና በአርሶ አደሩ ወቅታዊ ፍላጎት የተመሰረተ አቅርቦት ለመፈጸም ተግዳሮቶች እያጋጠሙ ናቸው። ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጋር በመሆን በተሰሩ ስራዎች ለኦሮሚያና አማራ ክልል አካባቢዎች አስራ ስድስት ዙር የጭነት መጓጓዝ ተከናውኗል።

አንድ ባቡር 37 ዋገን/ መጫኛ ያለው ሲሆን፣ እያንዳንዱ መጫኛ 700 ኩንታል በአንድ ግዜ ማንሳት ይችላል፤ በእንድ ጊዜ ሁለት ሺ 590 ሜትሪክ ቶን ይጭናል። ይህም 65 ድንበር ተሻጋሪ 400 ኩንታል የሚጭኑ መኪኖች የመጫን አቅም ጋር እኩል ነው። በዚህ መሰረትም ማጓጓዝ ተችሏል፡፡ ይህም በዚህ አመት ጥሩ አፈፃፀም ከተመዘገበባቸው አፈጻጸሞች አንዱ ነው።

ጭነቱን ከአንድ ባቡር ለማራገፍ የሚወስደው ጊዜ ቢበዛ ሶስት ቀን ነው፡፡ በመሆኑም ከሀገር ውስጥ የማዳበሪያ አቅርቦት 90 በመቶውን የሚጠቀሙት ኦሮሚያና አማራ ክልል እንደመሆናቸው የባቡሩን ጠቀሜታ ከፍተኛ አድርጎታል።

ባለሙያው በመጋዘን በኩል ዘንድሮ የተሻለ ዝግጅት እንዳለ ጠቅሰው፣ እንዲያም ሆኖ በሀገር ደረጃ ሳይንሳዊ መስፈርቱን ያሟላ መጋዘን በበቂ ሁኔታ አለ ማለት እንደማይቻልም ይጠቁማሉ። በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽንን ሳይጨምር በኦሮሚያ 53፣ አማራ 15፣ ደቡብ ዘጠኝ፣ትግራይ ሰባት፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሁለት ማራገፊያ ማእከላት እንደሚገኙ ተናግረው፣ እነዚህ ግን በቂ አይደሉም ይላሉ፡፡፡

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ፤ የመጋዘን አለመኖር ማዳበሪያ በስፋት ለማቅረብ ችግር እየሆነ መጥቷል፤ ይህ ጉዳይ አሁንም ትኩረት ይፈልጋል፡፡ ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውሰጥ የሚገባው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ወጥቶበት እንደመሆኑ በአግባቡ ሊቀመጥ ይገባል፤ ለብልሽት እንዳይዳረግ ሰፊ ጥንቃቄን ማድረግንም ይጠይቃል። በመሆኑም ቢያንስ በስፋት ማዳበሪይ በሚጠቀሙት ክልሎች ክልሎች ደረጃቸውን የጠበቁ በሳይንሳዊ መንገድ የተገነቡና ከአቅርቦቱ ጋር የሚመጣጠኑ መጋዘኖች ሊኖሩ ይገባል። መጋዘኖቹም ከመንገድ ጀምሮ ሌሎች ለሰራተኛ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ያሟሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

ከተገዛው ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ላይ የደረሰው 796 ሺ 230 ነጥብ 58 ሜትሪክ ቶን መሆኑን ባለሙያው አመልክተው፣ ከዚህ ውስጥ 701 ሺ 887 ያህሉ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ወደ ክልሎች እንዲጓጓዝ መደረጉን ያብራራሉ። ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያ ለሚያቀርቡት መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት 631 ሺ 457 ሜትሪክ ቶኑን ማድረስ ተችሏል፡፡ ከዚህም ውስጥ 236 ሺ 099 ሜትሪክ ቶኑን ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ተደርጓል።

አቶ ዘውዱ ከማዳበሪያ አይነቶች ዩሪያና ኤን ፔ ኤስ የተባሉትን በአብዛኛው ማስገባት መቻሉን ጠቅሰው፣ ኤን ፔ ኤስ ቢ የተባለው የማዳበሪያ አይነት እጥረት ማጋጠሙንም ያመለክታሉ። ይህም ሊፈጠር የቻለው በጣም ከፍተኛ የዋጋ ንረት ከመከሰቱ ጋር ተያይዞ መሆኑንና ዋጋ ለማስቀነስ በተደረገ ድርድር ሳቢያ መሆኑን ይጠቁማሉ።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ፤ በዚህም የተነሳ ኤን ፔ ኤስ ቢ እስካሁን አስር መርከብ ማዳበሪያ መግባት ሲኖርበት የገባው ግን ስድስት መርከብ ብቻ ነው፡፡ አንድ መርከብ የሚጭነው 50 ሺ ሜትሪክ ቶን ሲሆን፣ ባጠቃለይም እስካሁን 300 ሺ ሜትሪክ ቶን ገብቷል። ይህንንም ችግር በመፍታት በወቅቱ ማዳበሪያውን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ በመንግስት በኩል ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በበልግ አብቃይና የአገዳ እህሎች በሚዘሩባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ዝናብ ቀድሞ በመግባቱ የማዳበሪያ እጥረት ገጥሟል ያሉት ባለሙያው፣ ይህንንም በመገንዘብ በቅድሚያ ማዳበሪያው እንዲደርስ እየተደረገ ያለው ለእነዚህ አካባቢዎች ብቻ መሆኑንም ያብራራሉ፡፡

አቶ ዘውዱ በአጠቃላይ ወደ ሀገር ውስጥ የገባውን ማዳበሪያ ወደ ክልሎች ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማዳበሪያው እየተሰራጨ ያለው ለአምስት ክልሎች ነው ይላሉ።

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በኦሮሚያ 541 ሺ 325 መቅረብ ያለበት ሲሆን፣ እስካሁን 493 ሺ 665 ነጥብ ስምንት ሜትሪክ ቶን መግዛት ተችሏል፤ ይህም የፍላጎቱን 91 በመቶ መከናወኑን ያመለክታል። ወደብ ላይ ከደረሰው 328 ሺ 604 ሜትሪክ ቶን ወደ ክልሉ የተጓጓዘ ሲሆን፣ 106 ሺ 896 ያህሉም ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል። በዚህም በክልሉ ምእራቡ ክፍልና አርሲና ባሌ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

የአማራ ክልል በሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ማዳበሪያ በመጠቀም እንደሚታወቅ ጠቅሰው፣ለክልሉ 557 ሺ 124 ሜትሪክ ቶን መቅረብ እንዳለበትም ይጠቁማሉ፡፡ እንደ ባለሙያው ማብራሪያ፤ እስካሁን ለክልሉ የ496 ሺ500 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ግዢ የተፈፀመ ሲሆን፣ወደብ ከደረሰው ማዳበሪያ 280 ሺ 907 ሜትሪክ ቶኑ ወደ ክልሉ ገብቷል፡፡ ከዚህም ውስጥ 110 ሺ237 ሜትሪክ ቶኑ ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጭ ተደርጓል።

በክልሉ ምእራብ ክፍል ምእራብ ጎጃም ከፍተኛ የኤን ፒ ኤስ ማዳበሪያ ፍላጎት መኖሩን ጠቅሰው፣ከዚህ ጋር ተያይዞ እጥረት ገጥሞ እንደነበርም ያመለክታሉ፡፡ በምስራቁ የክልሉ ክፍል አጠቃለይ ጥሩ አፈፃፀም መኖሩንም ጠቅሰው፣ በዚህ አካባቢ የተወሰኑ ቦታዎች ዝናቡ ቀድሞ በመግባቱ ማዳበሪያውን በፍጥነት ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ደቡብ በፍላጎት ጥያቄው መሰረት መቅረብ ያለበት 65 ሺ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ሲሆን፣ እስካሁን 18 ሺ 527 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ግዢ ተከናውኗል፡፡ የግዢው መጠን የቀነሰበት ምክንያት ባለፈው አመት እንደ ሀገር ሳይሰራጭ የቀረ ያደረ 111 ሺ 967 ሜትሪክ ቶን በመኖሩ ነው፡፡ ግዢው ከተከናወነውም 31 ሺ 971 ሜትሪክ ቶኑ ክልሉ የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 16 ሺ 857 ለአርሶ አደሩ ደርሷል።

በክልሉ አቅርቦትና የአርሶ አደሩ ፍላጎት አለመጣጣም እንደሚታይ አቶ ዘውዱ ጠቅሰው፣ የክልሉ የማዳበሪያ ፍላጎት ትኩረት የሚፈልግ መሆኑ በባለሙያ የመስክ ምልከታ መረጋገጡንና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ለእዚህ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል የምርት ዘመኑ የማዳበሪያ ፍላጎት 44 ሺ 736 ሜትሪክ ቶን መሆኑን ተናግረው፣ ከእዚህም ውስጥ የ38 ሺ 595 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ግዥ መከናወኑን ይገልጻሉ፡፡ ወደብ ከደረሰው ማዳበሪያም 20 ሺ 809 ሜትሪክ ቶኑ ወደ ክልሉ ደርሶ ለአርሶ አደሩ የተሰራጨው ሲሆን 2 ሺ 107 ሜትሪክ ቶን ነው ዝቅተኛ የሆነው የሚዘራበት ወቅት ስለሚዘገይ ነው።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማዳበሪያ መጠቀም የጀመረው በቅርቡ መሆኑን ባለሙያው ይገልጻሉ፡ ፡ በ2010/2011 የምርት ዘመን ከክልሉ ቀርቦ የነበረው የማዳበሪያ ጥያቄ 15 ሺ 797 ሜትሪክ ቶን መሆኑን ተናግረው፣ይህም ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ተመልሷል ይላሉ። ይሄ የሆነበትም ምክንያት ክልሉ ገና የኤክስቴንሽን ስራ መተግበር የጀመረ በመሆኑ አና በወቅቱ ደርሶ አስፈላጊውን ድጋፍና ቁጥጥር መደረግ ስለሚገባ ነው።

እንደ ባለሙያው ገለጻ፤ ለክልሉ እስካሁን 8 ሺ 669 ነጥብ እምስት ሜትሪክ ቶን ነው። ከፀጥታና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በተፈለገው ደረጃ መሰራጨትና ለአርሶ አደሩ በወቅቱ መድረስ አልቻለም። የሶማሌ ክልልም ማዳበሪያ መጠቀም መጀመሩን ተናግረው፣ ማዳበሪያው የሚቀርብለት በግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በኩል እንደሆነም ገልፀዋል።

የማዳበሪያ ፍላጎቱን ለማወቅና አስፈላጊውን ግዥ ለመፈጸም እየተደረገ ያለው ጥረት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የሰኔ ወር በአብዛኛው የመኸር የዘር ወቅት የሚጀመርበት እንደመሆኑ ማዳበሪያውን ከወደብ አርሶ አደሩ ዘንድ የማድረሱ ስራ አሁንም ርብርብን የሚጠይቅ ተግባር ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን ግንቦት  6/2011

በራስወርቅ ሙሉጌታ