በሰላም አብሮ የመኖር አለም አቀፍ ቀን

14

 በሰላም በፍቅር ተከባብሮ ልዩነትን አቻችሎ ተደማምጦ በሀገር ላይ በጋራ የመኖርን ጸጋ የመሰለ ነገር የለም፡፡ ዛሬ በአብዛኛው የአለማችን ሀገራት መሰረታዊ ችግር የሆነው በውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች መደማመጥና አንዱ ሌላኛውን መስማት ተስኖአቸው፤ ልዩነትን በማጥበብ በመከባበር ለሰላምና ለሀገር ደህንነት ሲባል መቆም አለመቻላቸው ነው፡፡ ይህ ነው በአለማችን ውስጥ ሕዝቦችንና ሀገራትን ታላቅ የጥፋት ዋጋ እያስከፈለ ያለው፡፡ ለሰላሙም ሆነ ለጦርነቱ መሰረታዊ ምክንያት የሚሆኑት የፖለቲካ ኃይሎች ይህንን መሰረታዊ ችግር መፍታት ቢችሉ አለማችን በሰላም በፍቅር በመከባበር በአንድነት የሚኖርባት ውብ ምድር ትሆናለች፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በቁጥር 72/130 ሜይ 16(ግንቦት 8 ) በአለም አቀፍ ደረጃ በሰላም አብሮ የመኖር ቀን ሆኖ እንዲከበር ወስኖአል፡፡ ይህም የአለም አቀፉን ሕብረተሰብ አቅም በማንቀሳቀስ ሰላም፤ መቻቻል፤ ትእግስት፤ ሁሉን አቃፊነት፤ መደማመጥ ሕብረትና አንድነት ለማስፈን ያለመ ነው፡፡

የሰላምና የአብሮነት ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ መከበር ዋናው አላማ በጋራ የመኖርና የመንቀሳቀስ፤ የአብሮነት መንፈስን ለማሳደግ ሲሆን ልዩነቶችንና ብዝሀነትን ይዞ በአንድነት መቆምን በዚህም ዘላቂ ሰላም ሕብረትና ፍቅር የሰፈነባትን አለም መገንባት መቻል ነው፡፡

ቀኑ ሀገራት የበለጠ ለእርቅና ሰላም መስፈን ለልማትና እድገት ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ከኃይማኖት መሪዎችና ከሌሎች ጠቃሚ የሕብረተሰብ ተዋናዮች ጋር በመሆን ለእርቅ የሚበጁ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ወደ ተግባር እንዲገቡ በግለሰቦችም መሐል ይቅርታ ምህረትና መቻቻልን እንዲያበረታቱ የሚያግዝ ነው፡፡

ይህንን አለም አቀፍ የሰላምና አብሮነት ቀንን ማክበር ያስፈለገበት የራሱ መሰረታዊ ምክንያት አለው፡፡ ወደኋላ ታሪኩ ስንመለስ ሁለተኛው የአለም ጦርነት ያስከተለውን ጥፋትና ውድመት ተከትሎ ተከታታዩን ትውልድ ከጦርነት ለመታደግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋቋመ፡፡ የድርጅቱ አንደኛው አላማ አለም አቀፋዊ ችግሮችን ለመቅረፍ አለም አቀፍ ትብብር ያስፈልጋል፤ መሰረታዊ ነጻነቶች ዘር፤ ጾታ፤ ቋንቋና ኃይማኖት ሳይለይ ለሁሉም መከበር አለበት የሚል ነው፡፡

በ1997 የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በቁጥር 52/15—–2000 ዓ.ም (እኤአ) የሰላም ባሕል ቀን ተብሎ በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ወስኖአል፡፡ በ1998(እኤአ)ከ2001 እስከ–2010(እኤአ) ያለው ጊዜ አለም አቀፍ አስርት ሆኖ ለአለም ሕጻናት የሰላምና አመጽ አልባ ባሕል እንዲገነባ በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር አውጆአል፡፡

በ1999 የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በውሳኔ ቁጥር 53/243 የሰላም ባሕል እንዲገነባ አዋጅና የተግባር መመሪያ አውጥቶአል፡፡ ይህም ለአለም አቀፉ ማሕበረሰብና በተለይም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አመጽ አልባ የሆነ የሰላምን ባሕል እንዲያስፋፋ ልዩ ኃላፊነት የሰጠ የሰው ልጅ በሙሉ የዛሬውም ሆነ ቀጣዩ ትውልድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያለመ ነው፡፡

ይህ አዋጅ የወጣው ለረዥም ጊዜ በዩኔስኮ ሕገ ደምብ ውስጥ ተጠቅሶ በቆየውና “ጦርነቶች የሚጀምሩት በሰው ልጆች አእምሮ ውስጥ በመሆኑ ሰላምን የመከላከል ተግባርም መገንባት ያለበት በሰው ልጆች አእምሮ ውስጥ ነው “ ከሚለው ጽንሰ ሀሳብ የተነሳ ነው፡፡

አዋጁ ሰላም ማለት በቀላሉ የግጭቶች አለመኖር ማለት አይደለም የሚለውን መርህ ያቀፈ ነው፡፡ ሰላም ቀናና ንቁ የሆነ የተሳትፎ ሂደትን ይጠይቃል ። ውይይቶች ይበረታታሉ፤ በጋራ የመግባባትና የመተባባር መንፈስ ግጭቶች ይወገዳሉ፡፡

አዋጁ ይህንን ፍላጎት ለማሳካት ሁሉንም አይነት አድልዎና መድልዎ በዘር፤ በቀለም፤ በቋንቋ፤ በኃይማኖት፤ በፖለቲካና በሀሳብ ልዩነት በብሔር በጎሳ፤ በማሕበራዊ መሰረት፤ በሀብትና ንብረት፤ በአካል ጉዳት በውልደትና በሌሎችም ያሉትን ልዩነቶች ሁሉ ማስወገድ እንደሚገባ ያምናል፡፡

አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2011

 ወንድወሰን መኮንን