ሰሜን ኮሪያ በ37 ዓመት ታሪክ ያልታየ ከባድ ድርቅ አጋጠማት

20

 

ሰሜን ኮሪያ በ37 ዓመት ታሪክ ያልታየ እጅግ ከባድ ድርቅ እንደገጠማት ይፋ ያደረገች ሲሆን፤ በድርቁ ምክንያትም ሰብሎች ደርቀዋል፤ ዜጎች የሚበሉትን ለማግኘት ተቸግረዋል ተብሏል።

የሰሜን ኮሪያው የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ‘ኬ ሲ ኤን ኤ’ እንደዘገበው፤ በዚህ ዓመት የመጀመሪያ አምስት ወራት ውስጥ እጅግ ዝቅተኛ መጠን ያለው ዝናብ በአገሪቱ የዘነበ መሆኑን የዘገበው ሚዲያው፤ ከአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር 1982 ጀምሮ የዘነበው አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሆነ ገልጿል። ይህም አገሪቱ አሁን ላይ ያጋጠማት ድርቅ እጅጉን የከፋ እንዲሆን ያደረገው ሲሆን፤ብዙ ዜጎች በምግብ እጥረት ምክንያት ህይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችልም ዘግቧል።

ከሁለት ዓመት በፊት መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም ቀላል የማይባል ጉዳት ያደረሰ ድርቅ አገሪቱ ገጥሟት የነበረ መሆኑን ሚዲያው አክሎ ገልጾ፤ በድርቁ ሳቢያ እንደ ሩዝ፣ በቆሎ፣ ድንችና አኩሪ አተር የመሳሰሉ ዋነኛ የአገሪቱ ምርቶች ቀንሰው እንደነበር ጠቁሟል። በመሆኑም አሁን ላይ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም አገሪቱ ሊከብዳት እንደሚችል ተዘግቧል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ እንዳስታወቀው፤ አሥር ሚሊዮን የሚደርሱ ሰሜን ኮሪያውያን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ገልጾ፤ በዚህ ዓመት እያንዳንዱ ሰሜን ኮሪያዊ የእለት የምግብ ፍላጎቱን ለማርካት 300 ግራም የምግብ ፍጆታ ብቻ እንደሚያገኙ ህብረቱ አስታውቋል። በመሆኑም መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ አገሪቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ምግብ ከውጭ አገራት ማስገባት ካልቻለች ችግሩን አሳሳቢ እንደሚያደርገው ህብረቱ አስታውቋል።

እ.ኤ.አ በ2018 አገሪቱ ያመረተችው ምርት እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያስታወቀ ሲሆን፤ የሰሜን ኮሪያ አብዛኛዎቹ የግብርና መሣሪያዎች ኋላ ቀርና ሳይንሳዊ የአስተራረስ ዘዴን የማይጠቀሙ በመሆኑ፤ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የምርት መጠን ማግኘት ባለመቻሏ እንደዚህ ዓይነት ተፈጥሯዊ ድርቅና አደጋ ሲያጋጥም የአርሶ አደሮች ምርት በእጅጉ ያሽቆለቁላል ተብሏል።

የሰሜን ኮሪያ መንግሥት በበኩሉ፤ አገሪቱ ባጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ምግብን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እንዳልቻለች በተደጋጋሚ መንግሥት ማስታወቁን ገልጿል። እንዲሁም እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ አገሪቱ

ምርቶቿን ለውጭ አገራት በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ ከልክሏት ቆይቷል ብሏል።

በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር 1990 አካባቢ በአገሪቱ በተከሰተ ድርቅና ረሀብ ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰሜን ኮሪያውያን ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም

ሶሎሞን በየነ