‹‹ለም የእርሻ መሬት ሳይቀር በህገወጥ ግንባታ እየተዋጠ ነው››አቶ ዳዊት አብዲሳ በኦሮሚያ ክልል የመሬት ግጭት አወጋገድ ህገወጥ ይዞታ ቁጥጥር እና ክትትል ዳይሬክተር

42


 በኦሮሚያ ክልል በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ በልዩ ዞኖች እና በትንንሽ ከተሞች ሰፋፊ ግንባታዎች ይታያሉ። ግንባታዎቹ ሲከናወኑ ጉዳዩ ከሚመለከተው ኃላፊና ባለሙያ ባሻገር ወጪ ወራጁ ሲመለከት ሰንብቶ በድንገት ደግሞ ህገወጥ ነው በሚል የማፍረስ ሥራ ሲሰራም ለትዝብት እየዳረገ ይገኛል። ህገወጥ ግንባታ በየትኛዎቹ አካባቢዎች በስፋት ይታያል? ለምን ተስፋፋ? ከማፍረስ ይልቅ ግንባታው ከመከናወኑ በፊት ቀድሞ መከላከል ለምን አይቻልም? በሚሉት እና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በኦሮሚያ ክልል መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ የመሬት ግጭት አወጋገድ ህገወጥ ይዞታ ቁጥጥር እና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ዳዊት አብዲሳን ጠይቀን የሰጡንን ምላሽ እነሆ ብለናል።

 አዲስ ዘመን፡በኦሮሚያ ክልል ህገወጥ ግንባታ ምን ያህል ነው?

አቶ ዳዊት፡በኦሮሚያ ክልል በተወሰነ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በከተማም ሆነ በገጠር በስፋት ህገወጥ ግንባታ እየታየ ነው። የክልሉ ደንብ በእርሻ እና በግጦሽ ቦታዎች ላይ ግንባታን ቢከለክልም በገጠር አካባቢ ህገወጥ ግንባታ በእርሻ እና በግጦሽ ቦታዎች ላይ ሳይቀር በስፋት እየተካሄደ ይገኛል። አርሶ አደሩ ራሱ የራሱን ቤት ለማሻሻል ቢፈልግ እንኳ የመሬት አስተዳደሩ ሲፈቅድለት ብቻ ግንባታ ማካሄድ ቢኖርበትም ይህ እየተተገበረ አይደለም። ፈቃድ የሚጠየቀው እንዲሁ ለልማድ ሳይሆን ተገቢ የመሬት አጠቃቀም አሰራር እንዲተገበር ታስቦ ነው። አሁን እንደውም በገጠር ይዞታ ላይ ግንባታዎች በፍፁም አይፈቀዱም። ነገር ግን በህገወጥ መንገድ ተግባሩ እየተፈፀመ ነው።

አዲስ ዘመን፡በገጠር ይዞታ ላይ ግንባታዎች አይፈቀዱም ሲሉ አርሶ አደሩ ቤት መገንባት አይችልም ማለት ነው?

አቶ ዳዊት፡አርሶ አደሩ ለመኖሪያ ቤት መስሪያነት በያዘው መሬት ላይ የራሱን ቤት ህጋዊ በሆነ መልኩ ፈቃድ አውጥቶ መገንባት ይችላል። ነገር ግን የእርሻ መሬቱ ላይ ቤት መገንባት አይችልም። የግጦሽም ሆነ የደን መሬት ላይ ቤት መገንባት ፍፁም የተከለከለ ነው።

አዲስ ዘመን፡በክልሉ በእርሻ እና በግጦሽ መሬት ላይ በስፋት ግንባታ እየተካሄደ ያለው በየትኛው አካባቢ ነው?

አቶ ዳዊት፡ለከተማ የቀረቡ ገጠሮች በህገወጥ ግንባታ እየተወረሩ ነው። በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች አካባቢ በስፋት ግንባታዎች ይታያሉ። በተጨማሪ ምስራቅ ሸዋ አዳማ ወረዳ አካባቢ፣ ምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ አካባቢ በጣም እየተስፋፋ ነው። በጅማ ከተማ አቅራቢያ እና ሌሎችም ለከተማ የቀረቡ የገጠር ወረዳዎች አካባቢ ህገወጥ ግንባታ በገጠር መሬት ላይ እየተካሄደ ነው።

ከከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ግንባታው በመከናወን ላይ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከል ምስራቅ ሸዋ አደአ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው ግንባታም ተጠቃሽ ነው። የአደአ አካባቢ ግንባታ የእርሻውን መሬት ሳይቀር እየሸፈነው ነው። ሉሜ ወረዳም እንደዚሁ፤ ሰበታ እና ሱሉልታ ላይም ግንባታው ከመስፋፋቱ ብዛት የሱሉልታ ገጠር ወረዳ በከተማ እየተዋጠ ነው። ለገጣፎ እና ለገዳዲ አካባቢ በረክ ላይ ሰፊ ግንባታ አለ። በዚህ ምክንያት ለም የሚባለው የእርሻ መሬት ራሱ በግንባታ እየተዋጠ ነው።

አዲስ ዘመን፡እንደዚህ በስፋት ወደ ግንባታው የተገባው ከመቼ ጀምሮ ነው?

አቶ ዳዊት፡በትክክል የተስፋፋበትን ጊዜ ለመግለፅ ቢያዳግትም ከአስር ዓመት ወዲህ እየከፋ መጥቷል። ለምሳሌ ሰበታ እና ቡራዩን የሚያዋስነው አጂአ ቀበሌ ተራራዎች ሳይቀሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤቶች እየተሸፈኑ ነው። ይህ ደግሞ በተፈጥሮ ሃብት ላይ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል። ደን እየተመናመነ ለእንስሳት የሚሆን ግጦሽ መሬት በግንባታ እየተያዘ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግንባታው እየተስፋፋ ነው።

አዲስ ዘመን፡ከተማው ላይስ ያለው የህገወጥ ግንባታ ምን ይመስላል?

አቶ ዳዊት፡በከተማ ውስጥም የተከለሉ ለኢንዱስትሪ የተዘጋጁ እና ካሳ የተከፈለባቸው መሬቶች ሳይቀሩ ግንባታ እየተካሄደባቸው ነው። የእርሻ፣ የደን እና የአርሶ አደሩ ቤትና መሬት ጭምር የመሬት አጠቃቀም ህጉ በማይፈቅድ መልኩ ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው። በከተማም የግጦሽ መሬት፣ የደን መሬት እና ወንዞች አካባቢ ሳይቀር ግንባታ እየተካሄደ ወንዝ እየተበከለ ነው። የአርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን የመንግሥት መሬት ሳይቀር ግንባታ እየተካሄደበት ይገኛል። የመሬት አጠቃቀሙ እየተፋለሰ የሚገኝ ሲሆን የገጠርም ሆነ የከተማ አስተዳደሮች እየተቆጣጠሩ አይደለም።

አዲስ ዘመን፡ይህን ያህል ህገወጥ ግንባታ ለምን ሰፋ?

አቶ ዳዊት የሰዎች አማራጭ መሬት ፍለጋ አንደኛው ምክንያት ነው። በማህበር ተመዘግቦ ጠብቆ መሬት ከማግኘት ይልቅ ከአርሶ አደር ላይ በፍጥነት መሬት ገዝቶ ቤት መገንባትን እና ተረጋግቶ መኖርን ይፈልጋሉ። ትልልቅ ከተሞች አካባቢ ኢንዱስትሪው ሲስፋፋ የገጠር ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪዎች በትንሽ ካሳ መሬታችንን እንለቃለን በሚል እየሸጡ ነው። ሰዎቹ በካሬ ትንሽ ብር ከሚከፈለኝ ይልቅ በ50ሺ እና በ100 ሺ ብር ሁለት መቶ ካሬ ሜትር መሬት ብሸጥ ይሻለኛል በሚል እየሸጡ ነው። ነገር ግን አሁን ካሳ አከፋፈሉ እንደድሮ አይደለም። ሰዎች ቀድመው ወደ ሽያጭ እንዳይሄዱ የሚያግዝ ነው።

አዲስ ዘመን፡ሻጩ አማራጭ የተሻለ ካሳ እንዲያገኝ አመቻቻችሁ፤ ገዢውስ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ቤት መገንቢያ መሬት እንዲያገኝ ለምን አትሰሩም?

አቶ ዳዊት፡ለእርሱ ደግሞ አሰራር አለው። አንድ በከተማ የሚኖር ሰው ቦታ ማግኘት ከፈለገ በማህበር ተደራጅቶ ቦታ ያገኛል።

አዲስ ዘመን፡በምን ያህል ፍጥነት ?

አቶ ዳዊት፡አሰራሩ ተጀምሯል። በየከተማው መሬት በህጋዊ መንገድ እየተሰጠ ነው። ፍጥነቱ ላይ ችግር መኖሩ አይካድም። ነገር ግን ሰዎች በአጭር ቀን ቤት የመስራት ፍላጎታቸው ወደ ህገወጥነት እየመራቸው ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡ምክንያቱ ይህ ብቻ ነው ለማለት ባይቻልም ወደ ህገወጥ ግንባታ የሚኬድበት ምክንያት ቤት የመስሪያ መሬት ማግኘት ስለማይችል ነው። ስለዚህ ቤት የሚሰራበት መሬት ህጋዊ በሆነ መልኩ በእርግጥ እየተገኘ ነው?

አቶ ዳዊት፡ዜጎች በማህበር ተደራጅተው ቤት ማግኘት ይችላሉ። ቤት እንዲያገኙ በስፋት እየተሰራ ነው።

አዲስ ዘመን፡ተደራጅቶ የቤት ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችል መሬት የማግኘት ዕድል አለ እያሉ ነው?

አቶ ዳዊት፡አዎ! የመንግስት ሰራተኛው በማህበር ተደራጅቶ ቤት የሚሰራበት መሬት እያገኘ ነው።

አዲስ ዘመን፡በፌዴራል የመንግስት ተቋማት የለም።

አቶ ዳዊት፡እኛ እየተነጋገርን ያለነው ስለኦሮሚያ ክልል ነው። በክልሉ ደግሞ የመንግስት ሰራተኞች እና ነዋሪዎች ተደራጅተው ቤት እንዲያገኙ እንዲገነቡ እየተረገ ነው። ባለው የሊዝ አሰራር እና የመሬት ማስተላለፊያ መንገዶች ሂደቱን እየተከተሉ በህጋዊ መንገድ መሬት የማስተላለፍ ስራ ይሰራል:: በዚህ በኩልም የመሬት ብክለትን የመሬት ወረራን ለማስቆም እየተሰራ ነው።

አዲስ ዘመን፡ህገወጥነቱ ወደ ፊት እንዳይቀጥልና አሁን ባለበት እንዲቆም በትክክል ምን እየሰራችሁ ነው?

አቶ ዳዊት፡ቀድሞ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ እና ህገወጥ ግንባታው ምን ደረጃ ላይ እንደሆነ ለማወቅ ጥናት እየተካሄደ ይገኛል። የት አካባቢ በስፋት ህገወጥ ግንባታ አለ? የሚገነባው ማን ነው? ለምን በስፋት ይገነባል? ገንቢዎቹ የሚመጡት ከየት አካባቢ ነው? ህገወጥ ግንባታ እንዲኖር አስተዋፅኦ የሚያደርገው ምንድን ነው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ጥናት እየተካሄደ ነው። ልክ ጥናቱ እንዳለቀ ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ ይሰራል።

ሌላው ህገወጥነቱን ለማስቆም የማህበረሰብ ውይይት ሊደረግ ነው። አርሶ አደሩንም ከተሜውንም ያሳተፈ ውይይት በቅርብ ቀን ይካሄዳል። በተለይ በጣም ችግሩ ጎልቶ በሚታይባቸው አካባቢዎች ውይይት በማድረግ ግንባታው እንዳይስፋፋ እና የእርሻ መሬትም ያለአግባብ እንዳይባክን ለማድረግ ከከተማ ውጪም የከተማ አረንጓዴነትን የሚጎዱ ተግባሮችን ባሉበት ለማስቆም ውይይት ይካሄዳል።

አዲስ ዘመን፡አዲስ አበባ ላይ 1988 . በፊት ወይም 1997 . በፊት የአየር ካርታን በማየት ለተካሄደ ግንባታ በቅጣትም ቢሆን ወደ ህጋዊነት የሚገባበት መመሪያ አለ። በኦሮሚያ ክልል ያለፍቃድ የተካሄደ ግንባታ በምንም መልኩ ወደ ህጋዊነት መስመር አይገባም?

አቶ ዳዊት፡በእርግጥ በኦሮሚያ ክልልም የአየር ካርታ አለ። ነገር ግን በአየር ካርታው ላይ ቢኖርም በመሬት አስተዳደር ህግ መሰረት ያልተመራ እና ያልተሰራ ከሆነ ህገወጥ ነው። ግለሰቡ የገነባበትን መሬት በሊዝ ካልያዘ እና ምንም ዓይነት ሰነድ ከሌለው ህገወጥ ነው። ስለዚህ በስጦታ በውርስም ሆነ በምሪት ባልተገኘ መሬት ላይ የሚካሄድ ግንባታ ወደ ህጋዊነት የሚገባበት አግባብ የለም።

አዲስ ዘመን፡ከአስራ ስምንት ዓመት ወዲህ ሰዎች በምሪት ለቤት ግንባታ መሬት ማግኘት የሚችሉበት ዕድል እጅግ የመነመነ በመሆኑ ወደ ህገወጥ የመሬት ግዢ እና የቤት ግንባታ ገብተዋል። ይህን ታሳቢ በማድረግ ይመስላል አዲስ አበባ ላይ በተለያዩ መመሪያዎች ወደ ህጋዊነት ለማምጣት ተሞክሯል። በኦሮሚያ በፍፁም ወደ ህጋዊነት የሚገባበት መንገድ የለም በየትኛውም ዓመተ ምህረት ቢገነባ ተቀባይነት የለውም?

አቶ ዳዊት፡የሌላው ሊለይ ይችላል። ነገር ግን ህገወጥ ህገወጥ ነው። ስለወደፊቱ መናገር ባይቻልም አሁን ግን ካለፍቃድ እየተገነቡ ያሉ ግንባታዎች ህገወጥ ናቸው። አሁን ላይ ይፀድቃሉ አይፀድቁም ማለት አይቻልም።

አዲስ ዘመን፡ህገወጥ ነው በሚል ግንባታ ሲፈርስ የሚደርሰውን የአገር እና የግለሰብ ሃብት ብክነትን ግምት ውስጥ ማስገባት አይገባም? አስር ዓመት እና ከዛ በላይ ለዓመታት የተገነቡ ቤቶችን ማፍረስ ተገቢ ነው?

አቶ ዳዊት፡ስለማፍረሱ አሁን መነጋገር አዳጋች ነው።

አዲስ ዘመን፡እሺ! ነገር ግን ለብዙ ዓመት ቤት ሰርቶ የመብራት እና የውሃ አገልግሎት እያገኘ የነበረ ሰው ለዘመናት ህገወጥ መባሉ አያጠያይቅም? መንግስትስ ቀድሞ መከላከል ሲገባ ለዚህ ሁሉ ዘመን የት ነበር?

አቶ ዳዊት፡መቼም ሆነ መቼ ከመሬት ማስተላለፊያ መንገድ ውጪ ቤት የሰራ ሰው ህገወጥ ነው። ከዚህ ዓመት ወዲህ ብሎ ማለት አይቻልም። በኛ ክልል የመሬት ወረራ ተካሂዷል። ብዙ ዓመታት የቆዩ ውሃ እና ኤሌክትሪክ ያስገቡ ቀዬ መስርተው እየኖሩ ላሉት ለወደፊት ምን ይሆናሉ? ለሚለው ክልሉ ወደ ፊት አቅጣጫ ሊያስቀምጥ ይችላል። በሂደት መልስ ያገኛል።

አዲስ ዘመን፡ጥሩ፤ የመሬት ወረራውን ማስቆም ከፈለጋችሁ ግንባታ ሲከናወን አዲስ አበባ ላይ እንደሚደረገው ከስር ከስር በደንብ አስከባሪዎች አማካኝነት ማስቆም አይቻልም?

አቶ ዳዊት፡በእርግጥ የተገነባውን ከማፍረስ ይልቅ ቀድሞ እንዳይገነባ መስራት ይገባል። ከዚህ አንፃር መጀመሪያ ህብረተሰቡን የማወያየት ስራ እየተሰራ ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው። በህጋዊ መንገድ የተገኘ መሬት ላይ እንኳ ሳይቀር ያለ ፈቃድ ግንባታ መከናወን እንደሌለበት የሚከለክል መመሪያ አለ። ነገር ግን መመሪያው ሙሉ ለሙሉ እየተተገበረ ነው ማለት አይቻልም። ህገወጥ ግንባታ ገንብቶ የተገኘ እና እንዲገነባ ያደረገ እንደሚጠየቅ የሚያሳይ እና ወረራ ማካሄድን የሚከለክል አዋጅ እና ደንብ አለ:: ህገወጥ ግንባታን መቆጣጠር የሚያስችል ህግ አለ:: ነገር ግን ህጉን ማስፈፀም ላይ ችግር አለ። ስለዚህ ሁሉም አጋጣሚውን እየጠበቀ በህገወጥ መንገድ ይገነባል።

አዲስ ዘመን፡መሬት ገዝቶ ቤት የገነባው ሲፈርስበት ለእርሻ የተሰጠውን መሬት ከሚሸጠው አርሶ አደር ጀምሮ ሲገነባ በዝምታ የተመለከተው እና ህግ ያላስከበረው ኃላፊ እና ባለሙያስ መጠየቅ የለበትም?

አቶ ዳዊት፡በእርግጥ ከብዙ አቅጣጫ መመልከት ይቻላል። ግንባታውን የሚያደርገው ሰው ምናልባት ህገወጥ መሆኑን እያወቀ የገዛው መሬት ላይ የሚገነባው አማራጭ አጥቶ ሊሆን ይችላል። መሬት የሚሸጠው ሰውም መሬቱን መንግሥት በአነስተኛ ዋጋ ካሳ ከፈልኩ በሚል መሬቱን ከሚነጥቀኝ ቀድሜ በደህና ዋጋ ልሽጥ ብሎ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ይህን ችግር ለማቃለል ካሳ አከፋፈል ላይ ክለሳ እየተደረገ ነው። ይህ በአንዳንድ ቦታዎች እየታየ ነው። ሌላው ህግ ማስፈፀም ላይ መላላት ይታያል። ሰዎች ህግን አያስተገብሩም ራሳቸውም አይተገብሩም። ሆን ብሎ መመሪያ የመጣስ ራስን ማስቀደም አለ። ህጉን አዋጁን እና ደንቡን እያወቀ አይተገብርም፤ አያስተገብርም። አሁንም ሙሉ ለሙሉ ፀድቷል ማለት አይቻልም። የሚሸጠውም የሚገዛውም ህጉን የሚያስፈፅመውም ከራስ ወዳድነት ጋር የተያያዘ ነው።

አዲስ ዘመን፡ከማፍረስ ጋር ተያይዞ ሲገነባ ያልተቆጣጠረውን እና መሬቱን የሸጠውን በሚመለከት መጠየቅ አይቻልም?

አቶ ዳዊት፡ስለወደፊቱ አቅጣጫ ይቀመጣል እንጂ አሁን ምንም ማለት አይቻልም። ማንኛውም ሰው መዘንጋት የሌለበት ህገወጥ ህገወጥ ነው። መሬቱ ከሚፈቅደው አጠቃቀም ውጪ የጤፍ መሬት ላይ ቤት የገነባ ህገወጥ ነው። ተዳፋትነቱ በማይፈቅድ ተራራ ላይ ቤት ቢገነባ ህገወጥ ነው። የግጦሽ የጋራ የመንግስት መሬት ላይ መገንባት ህገወጥነት ነው።

አዲስ ዘመን፡በአጠቃላይ በክልሉ ከህገወጥ ግንባታ ጋር ተያይዞ እስከአሁን የተወሰዱ እርምጃዎች ምን ያህል ናቸው?

አቶ ዳዊት፡ሰዎች አዲስ አበባ ዙሪያ ስላለው ያስቡ እንጂ በሌሎችም አካባቢዎች በስፋት ግንባታው አለ። የማፍረስ እርምጃም እየተወሰደ ነው። በሻሸመኔ በዘጠኝ ቀበሌ በገጠር መሬት ላይ ህንፃ ሳይቀር ብዙ ግንባታ እየተከናወነ ነው። አዳማ ላይም በስፋት ግንባታው አለ። ቢሾፍቱም እንዲሁ መቱ ላይ ግንባታ የተከናወነ ሲሆን በመቱ ሰፊ የማፍረስ እርምጃ ተወስዷል። በማይገመቱ በትንንሽ ከተሞች ሳይቀር ህገወጥ ግንባታዎች በብዛት አሉ። የወረዳ ከተሞችን ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። ግንባታው አለ፤ አልፎ አልፎ እርምጃ ይወሰዳል። የተወሰዱ እርምጃዎች እና የተካሄዱ ግንባታዎችን በሚመለከት ወደ ፊት መረጃውን በማጠናቀር የሚገለፅ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡ህገወጥነት በሚል ግንባታ ሲፈርስ ኪሳራው ታሳቢ ይደረጋል?

አቶ ዳዊት፡ከምንም በላይ ትልቁ ኪሳራ ለም መሬትን ማጣቱ ነው። ለግብርና የሚሆነውን ከማጣት ባሻገር ለአረንጓዴ ልማት መዋል ያለበትን ተዳፋት አካባቢና ወንዝ ስር ቤት መገንባቱም ቦታው ለታለመለት ዓላማ አለመዋሉም ትልቅ ጉዳት ነው። በተጨማሪ ግን ከተገነባ በኋላ መፍረሱ የሰው ጉልበት፣ የግንባታ ቁሳቁሶች መክሰሩ ትልቅ ቢሆንም ከኪሳራዎች ሁሉ ትልቁ ኪሳራ ለም መሬት ማጣት፣ የመሰረተ ልማት መገንቢያ ቦታዎችን ማጣት መንገድ እና ጤና ተቋማት የሚገነቡበትን አካባቢ ማጣት እና የመሬት አጠቃቀሙ መዘበራረቅ ኪሳራው ቀላል አይደለም። እኛም ኪሳራውን ለመቀነስ ቀድሞ መከላከል ላይ እንሰራለን።

አዲስ ዘመን፡ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።

አቶ ዳዊት እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም

ምህረት ሞገስ