ወረቀትን ከእንሰት ቃጫ የማምረት የፈጠራ ሥራ

18

ወረቀት ለማምረት እንደ ዋና ግብዓት የሚታወቀውና የተለመደው እንጨት ቢሆንም አቶ ተስፋዬ መኮንን ወረቀትን ለማምረት ከተለመደው ግብዓት ወጣ በማለት ከእንሰት ቃጫ (ኮባ) ላይ ወረቀት ማውጣት ወይም ማዘጋጀት ችለዋል።

«ተስፋዬ፣ ሊያና ወይንሸት ኤኮ ፔፐር ህብረት ሽርክና ማህበር» ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ወረቀት የማምረቱን ሥራ የሚያከናውን ድርጅት ነው። የሸንኮራ አገዳ፣ እንቦጭ፣ ባምቡ፣ ፓፒረስ ወዘተ… የመሳሰሉትን ጥሬ እቃዎች በመጠቀም ወረቀት ማምረት እንደሚቻል የሚናገሩት የፈጠራ ባለቤቱ አቶ ተስፋዬ መኮንን፤ ከእንሰት ቃጫ ባሻገር የወዳደቁና የተበላሹ ወረቀቶችን በሳይንሳዊ ዘዴ ወደ ምርትነት በመቀየር ወረቀት እንደሚያመርቱ ጠቁመዋል። በተጨማሪም ጭድን /የጤፍ ገለባን/ ወረቀት ለማምረት እንደሚጠቀሙም ገልጸዋል። በአጠቃላይ የሚያመርቱት ወረቀት ‹‹አሲዲቲና አልካላይኒቲ›› የሌለው እንዲሁም በማህበረሰቡና በአካባቢው ላይ ምንም አይነት የጎንዮሽ ችግሮችን የማያስከትሉ በቀላሉ በአገር ውስጥ የሚገኙ ተፈጥሯዊ ግባቶችን በመጠቀም እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።

እንደ ፈጠራ ባለቤቱ ገለፃ፤ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ወረቀት ከምንም ኬሚካል በጸዳ መልኩ በፋብሪካ ሳይበለጽግ በእጅ የተሰራ ነበር። ስለዚህ በዚህ መልኩ የወረቀት ማምረት ሂደቱ ተጀመረ። ድርጅቱ የሚያመርታቸው ወረቀቶች ቢሮ ላይ ለአገልግሎት ከሚውሉ ወረቀቶች ለየት ያሉ ሲሆኑ፤ የሚመረቱ ወረቀቶችም ጥራታቸውንና ደረጃቸውን የጠበቁና ለህትመት ብቁ የሆኑ ናቸው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጀሞ ሚካኤል አካባቢ ወረቀት የማምረት ስራውን እያከናወኑ እንደሚገኙ የጠቆሙት የፈጠራ ባለቤቱ፤ የሚያመርቱት ምርት ወደ ገበያ ከገባ በኋላ በምርቱ ላይ ጥናት በማድረግና የተለያዩ የደንበኞችን አስተያየት በመቀበል የወረቀት ምርቱን በአይነትና በጥራት እንዲሻሻሉ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። በዚህም ቀስ በቀስ ምርቱን በማሻሻል ወረቀቶቹ ጥራት እንዲኖራቸው በማድረግ ለህትመት ብቁ የሆኑ ምርቶችን በተፈለገው መጠን ለደንበኞች ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሆነ፤ ድርጅቱ በፊት በቀን 20 ኪሎ የወረቀት ምርት ሲያመረት የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ የማምረት አቅሙን በእጥፍ በማሳደግ በቀን 40 ኪሎ ማምረት እንደቻለ፤ በአጠቃላይ በሂደት ምርቱን በአይነትና በጥራት በማሻሻል ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ እንደሆነ አስታውቀዋል።

አቶ ተስፋዬ እንደሚሉት፤የፈጠራ ስራው ከራስ አልፎ ለሌሎች የገቢ ምንጭና የስራ እድል የሚፈጥር ሲሆን፤ የተለያዩ ጥራት ያላቸውን ወረቀቶች በአገር ውስጥ በማምረት አገሪቱ ለወረቀት ግዥ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር ነው። በተጨማሪም የወዳደቁና ቆሻሻ ወረቀቶችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል አካባቢና አየር ንብረት እንዳይበከል የሚያደርግ ነው። ገበሬውም እንሰትን (ኮባን) በከፍተኛ መጠን በማምረት ከምግብ ፍጆታነት አልፎ ለፋብሪካ ጥሬ እቃነት በማቅረብ የገቢ ምንጭ ለማግኘት ያስችለዋል።

ወረቀቱን የማምረቱ ሂደት የመጀመሪያው ስራቸው እንደሆነ የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፤ በሁለተኛ ደረጃ ያለቀላቸውን ምርቶች በማዘጋጀት ለተለያዩ አካላት ምርታቸውን እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል። አንድ ‹‹ኤ ፎር›› ወረቀት በአስር ብር ዋጋ የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ፖስት ካርድ፣ አልበም፣ ቡክማርክ፣ ፖስተሮች፣ መፅሀፎች፣ የመጠጥና የምግብ ዝርዝር ማውጫ ደብተርና ሌሎች ያለቀላቸውን ምርቶች በማዘጋጀት ለስጦታ እቃ መሸጫ ሱቆች፣ ለመስሪያ ቤቶች፣ ለሆቴሎች፣ ለትልልቅ ድርጅቶች፣ የተለያዩ ሁነቶች ለሚያዘጋጁ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

‹‹ወደዚህ የፈጠራ ስራ እንድገባ ያደረገኝ አንድ ሰው በአስተሳሰቡ ከተለወጠ በኢኮኖሚውም ለመለወጥ መንደርደሪያ ሃሳብ ይኖረዋል የሚል እምነት ስላለኝ ነው። እንዲሁም አንድ ሰው በአስተሳሰቡ ከተለወጠ በቅርቡ የሚያገኘውን ጥሬ እቃ ወይም ተፈጥሮ ሀብት ተጠቅሞ በቀላሉ መለወጥ ይችላል። በመሆኑም እራሴን ለመቀየር ትልቅ ፍላጎት ስለነበረኝ ወደዚህ የፈጠራ ስራ ልገባ ችያለሁ። ስለዚህ የትም አገር ስደት ሳልሄድ እዚሁ በአገሬ ሰርቼ በመለወጥ ለራሴ የስራ እድል መፍጠር እችላለሁ፤ ለወገን ተምሳሌት ከመሆን ባሻገር ለሌሎች የስራ እድል መፍጠር እችላለሁ የሚል ተነሳሽነትና የውስጥ እምነት ስላለኝ ይሄን የፈጠራ ስራ ከፍተኛ ምርምር በማድረግ ወደ ተግባር ለመቀየር ችያለሁ።

« ሰው በአስተሳሰቡ ከተለወጠ እራሱንና አካባቢውን መለወጥ ይችላል። እኔ ስለወጥ አካባቢዬን ከመለወጥ ባሻገር በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችን አመለካከታቸውንና አስተሳሰባቸውን መለወጥ እችላለሁ። በመሆኑም ለውጥ ከውጭ ወደ ውስጥ የሚመጣ ሳይሆን ከውስጥ ወደ ውጭ የሚወጣ ትልቅ ጉልበት ያለው መሳሪያ ነው። አንድ ሰው ተለወጠ የሚባለው አካላዊ ለውጥ ስላመጣ ሳይሆን ከውስጡ መለወጥ ሲችል ነው።

« እኔም በቅድሚያ ውስጤን በመቀየር በአካባቢዬ ምን አይነት ጥሬ ዕቃ፣ የሰው ኃይል፣ ተፈጥሮ ሀብት፣ እውቀት ወ.ዘ.ተ አለ የሚሉትን በማጤን እነዚህን የተፈጥሮ ሀብት በየትኛው አቅጣጫ ላይ በመለወጥ ከራሴ አልፎ ለሌሎች የስራ እድል መፍጠር እችላለሁ በሚል የውስጥ ለውጥና እምነት ተከታታይ ጥናት እያካሄድሁኝ በአካባቢ በቀላሉ የሚገኝን የተፈጥሮ ሀብትና እውቀት በመጠቀም ወረቀት በማምረት ስራ ላይ ልሰማራ ችያለሁ›› በማለት የፈጠራ ባለቤቱ አቶ ተስፋዬ መኮንን የፈጠራ ስራውን ለመስራት ምን እንዳነሳሳቸው አጫውተውናል።

የፈጠራ ስራውን በ3ሺ ብር ካፒታል እንደጀመሩት የተናገሩት ስራ አስኪያጁ፤ አሁን ላይ 1ነጥብ5 ሚሊዮን ብር የፋይናንስ አቅም መፍጠር ችለዋል። የፈጠራ ባለቤቱ ከራሳቸው አልፈው በተለያየ የትምህርት ዘርፍ ለተመረቁ ሰባት ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ አራቱ ቋሚ ሶስቱ ደግሞ ጊዜያዊ ሰራተኛ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

አቶ ተስፋዬ ምንም እንኳን ትምህርታቸውን በነገረ መለኮት የሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በኮሚዩኒቲ ዲቨሎፕመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ ቢያገኙም፤ የትምህርት ዝግጅታቸው ከተፈጥሮ ሳይንስ ውጭ መሆኑ የፈጠራ ስራቸውን ለመስራት ምንም እንቅፋት እንዳልሆነባቸው ነው የሚናገሩት። በአንጻሩ የፈጠራ ስራውን ለመስራት የመነሻ ካፒታል እጥረት፣ የመስሪያ ቦታ አለማግኘት፣ የተለያዩ የመስሪያ ማሽን አለማግኝትና ዋጋቸው መወደድ እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች አሁንም ድረስ ምርቱን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ተግዳሮት ሆነውባቸዋል።

የፈጠራ ባለቤቱ ለረጅም ዓመታት የተለያዩ ጥናቶችንና መጽሐፍቶችን በማገላበጥ ጥናትና ምርምር በማድረግ የፈጠራ ስራውን በመስራታቸው በእውቀትና በክህሎት ምንም አይነት የገጠማችው ችግር እንዳልነበረ አውስተዋል።

የቀድሞው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአሁኑ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለፈጠራ ስራቸው እውቅና የዋንጫ ሽልማት፣ የምስክር ወረቀት እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ አበርክቶላቸዋል። በተጨማሪም በመንግሥት በኩል ምርታችውን ለአንዳንድ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ማቅረብ እንዲችሉ የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል። የፈጠራ ስራውን በብዛት አምርቶ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችላቸው የመስሪያ ቦታ ተመቻችቶላቸዋል። በሌላ በኩል ማህበረሰቡ በአገሩ ምርት እምነት በማሳደር ለተለያዩ ዝግጅቶች የሚውሉ የህትመቶችንና የተለያዩ የስጦታ እቃዎችን በመግዛት እየተጠቀመ ይገኛል ብለዋል የፈጠራ ባለሙያው።

የፈጠራ ባለሙያው ‹‹መንግሥት የሁሉንም ዜጋ ፍላጎት ማሟላት ስለማይችል፤ በትንሽም ቦታ ይሁን ባለችን ትንሽ የፋይናንስ አቅም ምን ልሰራ እችላለሁ የሚል ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ካደረግን ማንም ሰው ካሰበው ለመድረስ አዳጋች አይሆንበትም። ስለዚህ ወጣቱ የመስራት አቅሙና ችሎታው ስላለው ከውስጡ እራሱን መለወጥ ከቻለ የትኛውንም ከባድ ነገር በማለፍ የስኬት ማማ ላይ መቆናጠጥ ይችላል። ስለዚህ ወጣቱ ለመለወጥ እራሱን ዝግጁ አድርጎ ምን ልስራ የሚለውን ጥያቄ በመመለስ ራሱን ወደ ስኬት ጎዳና ማንደርደር ይችላል›› በማለት ተነሳሽነት ለፈጠራ ስራ ያለውን ዋጋ ይገልጻሉ::

አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም

 ሶሎሞን በየነ