ለመኖሪያ ቤት የሚውል ከወለድ ነጻ የዳያስፖራ የፋይናንስ አገልግሎት ተመቻቸ

362

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን  የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ የሚያስችል ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ይፋ ማድረጉን ዛሬ  ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት  በላከው መግለጫ አስታወቀ።

ማንኛውም  ዳያስፖራ  ወዲዓ’ህ የቁጠባ ሂሳብን በመጠቀም ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ በእንግሊዝ ፓውንድ፣ በአሜሪካን ዶላርና በዩሮ መቆጠብ ከቻለ የፋይናንስ ጥያቄውን ለባንኩ በማቅረብ መስተናገድ እንደሚችል በመግለጫው ተጠቁሟል።

የፋይናንስ አገልግሎት መስፈርቱን  ማሟላት የሚችሉ  ማንኛውም ዳያስፖራዎች  በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ወይም በሚኖሩበት አገር በሚገኝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ቀርበው  የወዲዓ’ህ ቁጠባ ሂሳብ በመክፈት መቆጠብ የሚችሉ እንደሆነ ያመለከተው  መግለጫው   ለአገልግሎት የሚያስፈልገውን ቅድመ ክፍያ በአንድ ጊዜ ወይም በተለያየ ጊዜያት መቆጠብ ይችላሉ።  ብድሩንም  እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ቆይታ ጊዜ ከፍለው መጨረስ እንዲችሉም ሁኔታዎች  ተመቻችተዋል ተብሏል።

ባንኩ ለመኖሪያ ቤት መግዣ የሚውለው ከወለድ ነጻ የዳያስፖራ  ፋይናንስ አገልግሎት ከዚህ ቀደም ባንኩ ለዳያስፖራ ካቀረባቸው  አገልግሎቶች በተለየ መንገድ  እንደሚተገበርም  መግለጫው  አመልክቷል።