እጅ የሚበዛባቸው የእግረኛ መንገዶቻችን

14

የአዲስ አበባ የእግረኛ መንገዶች ከእግር ይልቅ እጅ ይበዛባቸዋል። የመንግስት መስሪያ ቤቶች በፈረቃ እየቆፈሯቸው እንዳልነበር ያደርጓቸዋል። የህንጻ ተቋራጮች የግንባታ ቁሳቁስ ማከማቻ (ስቶር) ሆነውም ያገለግላሉ። አንዳንዴም ሲሚንቶ ተቦክቶባቸው አባጣ ጎርባጣ ይሆናሉ። ዘወትር የሸቀጥ አይነት ተዘርግቶባቸው ህገወጥ ንግድ ይደራረብባቸዋል። መንገድ ዳር ያሉ መጠጥ ቤቶች ወንበር ደርድረውባቸው አሸወይና ይሉባቸዋል።

በዓል በመጣ ቁጥር በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች በሚገኙ እግረኛ መንገዶች ላይ በመንግሥት እውቅና የተሰጣቸው የንግድ ኤግዚቢሽኖች ይካሄዳሉ። ከዚህም አልፎ ከባድ መኪና ወጥቶባቸው ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ለመከላለከል ከሚሰራው ስራ ውጭ መንገዶቹ ለታለመላቸው ዓላማ እንዳይውሉ ያደረጉትን የሚጠይቅ አካል ያለ አይመስልም። እነዚህ ጥቂቱ ችግሮቻችን ናቸው።

ከአዲስ አበባ ነዋሪ 26 በመቶ በብዙኃን መጓጓዣ ተጠቃሚ፤ አራት በመቶው የግል አውቶሞቢል አሽከርካሪ፤ ቀሪው 70 በመቶ ደግሞ በእግር ተጓዥ እንደሆነ ይናገራል። መንገዶች ሲገነቡ ግን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የከተማዋ እግረኛ ነዋሪ ይዘነጋል።

ለመኪና አደጋ መከሰት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ የእግረኛ መንገድ አጠቃቀም ችግር እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል። እኔ የምለው መጠቀሚያው ሳይኖር የአጠቃቀም ችግር አለ ይባላል እንዴ? የእግረኛ መንገዶች ታስቦባቸው አይሰሩም። እንዲያውም በአንዳንድ ቦታዎች ለስም ብቻ ቀጭን መስመር የሚመስል ንጣፍ ይደረጋል። ቀደም ባለው ጊዜማ የእግረኛ መንገዶች የከተማዋ እንብርት ላይ ብቻ የሚሰሩ ጌጦች ተደርገው ይታሰቡ ነበር። ልክ እንደ ትራፊክ መብራት ቀስ በቀስ ነው መስፋፋት የጀመሩት።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለእግረኛ መንገዶች ትኩረት ቢሰጥም አሁንም ከእግረኛው ቁጥር ጋር ተጣጥመውና ስፋት ኖሯቸው እየተሰሩ አደለም። ስለዚህ እግረኞች ምርጫ በማጣት ከመኪና ጋር እየተጋፉ በአስፓልት ላይ መጓዝን ልምድ አድርገውታል። በየአደባባዩ እግረኛ ወደ መኪና መንገድ እንዳይገባ በብረት አጥር መከለል ግድ የሆነው ለዚህ ነው። ባለፉት ሳምንታት ከመኪና መንገድ የተወሰነውን በመቁረስ የጠበቡትን የእግረኛ መንገዶች ለማስፋት ጥረት ሲደረግ እያየን ነው። እርምጃው ጥሩ ነው ነገር ግን የአገር ሀብት ከመባከኑ በፊት መጀመሪያ ቢታሰብበት መልካም ነበር።

የእግረኛ መንገዶች ላይ ቆመው እግረኞችን የሚያስተናብሩ የትራፊክ ፖሊሶችን መመደብ ሳያዋጣ አይቀርም። ምክንያቱም የእግረኛ ትራፊክ ፖሊሶች ካሉ የመኪና መንገድ ሲዘጋ የሚደረገው አይነት ርብርብ የእግረኛ መንገድ ሲዘጋና ሲቆፋፈርም ክትትል ይኖረዋል። የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎችም የእግረኛ መንገድ ተቆጣጠሪ ትራፊክ ፖሊሶችን መስመር ላይ ቀጥታ እያስገቡ በየጉድጓዱ እየገቡ የሚሰባበሩና የሚሞቱ እግረኞችን ቁጥር ይፋ ያደርጋሉ። በየዕለቱ በግንባታ ምክንያት አሸዋና ጠጠር ፈስሶባቸው የተዘጉ የእግረኛ መንገዶችን ነግረውን አማራጭ የእግረኛ መንገድ ይጠቁሙናል። ለቴሌኮም፣ ለውሃና ለኤሌክትሪክ አገልግሎት መስመር ዝርጋታ በየጊዜው የሚያካሄዱት ቁፋሮዎች መቼ ተጀምረው መቼ እንደሚጠናቀቁና ስንተኛ ዙር እንደሆነ መረጃ ይሰጡናል።

በነገራችን ላይ ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ ለሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት መቶ ሚሊየን ብር መለገሱና ሰራተኞቹም የትርፍ ሰዓት ክፍያቸውን በመተው ሰማኒያ ሚሊየን ብር መስጠታቸው አስደስቶኛል። ነገር ግን ኢትዮ ቴሌኮም ሸገር እንድትዋብ ከፈለገ ሌላም ነገር ይጠበቅበታል። በየጊዜው የእግረኛ መንገዶችን እየቆፈረ ከተማዋን የገበጣ መጫወቻ ጉድጓድ ከማስመሰል መቆጠብ አለበት።

ደንብ አስከባሪዎች ከጎዳና ላይ ንግድ አጧጧፊዎች ጋር በእግረኛ መንገዶች ላይ ሲተናነቁ ማየት መቼ እንደሚያቆም መገመት አይቻልም። ይህ ጉዳይ መገናኛንና ሜክሲኮን በመሰሉ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በየዕለቱ የሚታይ ድራማ ነው። አንዳንድ ጊዜ ከደንብ አስከባሪዎች ለማምለጥ የሚሯሯጡ ወጣቶች መሀል መንገድ ገብተው ለመኪና አደጋ ሲዳረጉ ይታያል፡ ነገር ግን ቁጥጥሩ ያመጣው ፋይዳ አለ ለማለት ይቸግራል። የከተማዋ አስተዳደር የጎዳና ላይ ንግድን ለማስቀረት እርምጃ እየወሰደ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር እዚህ ግባ የሚባል ጥረት ያለ አይመስልም።

የእግረኛ መንገድ ላይ የሚሰነዘሩ እጆች ሁሉ ተሰብስበው እግሮችን ለመፍታት እንዲውሉ የሚመለከተው አካል ኃላፊነቱን መወጣት ቢጀምር መልካም ነው።

አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2011

 የትናየት ፈሩ