“ብሄር ተኮር ፖለቲካን በህግ ማገድ በኢትዮጵያ አንፃራዊ ሁኔታ ተመራጭ መንገድ አይደለም” አቶ ልደቱ አያሌዉ

225


ብሄር ተኮር ፖለቲካን በህግ ማገድ በኢትዮጵያ አንፃራዊ ሁኔታ ተመራጭ መንገድ አይደለም ሲሉ አቶ ልደቱ አያሌዉ ተናገሩ።

አቶ ልደቱ ይሄን ያሉት ዛሬ “ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም ወይስ መልክኣምድርን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም ?” በሚል የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ምሁራንንና ፖለቲከኞችን ባሳተፈ የምክክር መድረክ ላይ ነዉ።

አቶ ልደቱ ብሄር ተኮር ፖለቲካ በህግ ይታገድ የሚሉ አካላት መኖራቸዉን አዉስተዉ ይሄ ግን በኢትዮጵያ አንፃራዊ ሁኔታ ተመራጭ መንገድ እንዳልሆነም ገልፀዋል። ከዛ ይልቅ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ያከበረ የሀገሪቷንም አንድነት ያስጠበቀ የፌደራሊዝም ስርአት መዋቀር አለበት ሲሉ አሳስበዋል:: አክለዉም በአሃዳዊ ስርአት የሚገኙ ጥቅሞችን ያገናዘበ የፌደራሊዝም ስርአት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የፌደራሊዝም አስፈላጊነት ጥያቄ ዉስጥ ሊገባ አይገባም ያሉት አቶ ልደቱ ከዛ ይልቅ ግን ምን አይነት ፌደራሊዝም የሚለዉ ላይ ነዉ መሰመር ያለበትም ብለዋል።

አሃዳዊ ስርአትና ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም በሀገሪቷ በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ታይተዉ ብዙ ጉድለቶች እንደነበሩባቸዉ ያወሱት አቶ ልደቱ ሁለቱንም ለየብቻ ከማየት ይልቅ በማስታረቅ ያላቸዉን ቅራኔ መፍታት የተሻለ የመፍትሄ ሀሳብ መሆኑንም አፅንዖት ሰጥተዉበታል።

በዳግማዊት ግርማ