ትምህርት ቤቱና ግብረሰናይ ድርጅቱ ባለመስማማታቸው የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር ተቋረጠ

20

 አዲስ አበባ፡- የስብስቴ ነጋሲ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አፍሪካ የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት በአሠራር ባለመስማማታቸው ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር መቋረጡ ተገለፀ።

በኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ወይዘሪት ሰብለ ነብየልዑል ፤ ድርጅቱ በላፍቶ ክፍለ ከተማ አጋዚያን እና ስብስቴ ነጋሲ ትምህርት ቤት የምገባ መርሐ ግብር ላይ እንደሚሳተፍ ገልፀው፤ በሁለቱ ትምህርት ቤት ላይ 2ነጥብ8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የዳቦ መጋገሪያ የዳቦ ማሽን መገዛቱን አመልክተዋል።

ለስብስቴ ነጋሲ ትምህር ቤት ዳቦ ቤት ሰርተን አስረክበን እንወጣለን ብለን ተስማምተን ነበር ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ይሁንና የፌዴራል በጎ አድራጎትና ማህበራት ኤጀንሲ ይህን ያክል ንብረት ለትምህርት ቤት አስረክባችሁ መውጣት አትችሉም ስላለን በማሽኑ አጠቃቀምና በቀጣይ መሆን ስላለበት እንድንከታተል ብለን ብንጠይቅም በትምህርት ቤቱ ተከለክለናል ብለዋል። እንጉዳይም ማምረት ቢጀምሩም ‹‹ለጤና ጎጂ ነው›› በሚል ከጥቅም ውጭ ተደርጓል ብለዋል።

የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ህግ ተከትለን ብንሠራም፤ ትምህርት ቤቱ በአሠራሩ ጣልቃ ለመግባት በመፈለጉ ሥራውን ለማቆም ተገደናል ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ለ100 ተማሪዎች ስንሰጥ የነበረውን ምገባ መርሐ ግብር አቋርጠናል ብለዋል። ጉዳዩ ከክፍለ ከተማ ከዚያም ከተማ መስተዳድር ድረስ ቢደርስም መፍትሄ ማጣታቸውን ገልፀዋል።

የስብስቴ ነጋሲ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ወይዘሮ አበበች ሞትባይኖር ፤ ግብረሰናይ ድርጅቱ ለምገባ መርሐ ግብሩ መጀመሪያ የመጣው በ2008 ዓ.ም የነበረ ሲሆን ውል ገብቶ የነበረውም ለሦስት ዓመታት ለመቆየት ነበር። በወቅቱም በ80 ተማሪዎች ምገባ ጀምረው በሂደት ወደ 100 ተማሪዎች ማሳደጋቸውን አስታውሰዋል።ይሁንና

 የገቡት ውል በመጠናቀቁ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር ስምምነቱ በአዲስ መልክ መታደስ የነበረበት ሲሆን፤ ያንን ባለማድረጋቸው መርሐ ግብሩ እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ዳቦ ለመጋገር ማሽን የገዛ ቢሆንም ማሽኑ እንዲተከል የተፈለገበት ሥፍራ ሆነ አሰራሩ ህግን የተከተለ ባለመሆኑ ከልክለናል ብለዋል። የዳቦ ማሽኑ ልዩ ፍላጎት የሚሹ ተማሪዎች መማሪያ መምህራን ማረፊያ ክፍል አጠገብ ብሎም ዙሪያውን በመማሪያ ክፍሎች የተከበበ በመሆኑ ዳቦ ሲጋገር፣ ዱቄትና ሌሎች ግብዓቶች የጫኑ ተሽከርካሪዎች ሲወጡና ሲገቡ ብሎም የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውኑ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ጫና መፍጠሩን አመልክተዋል።

ወይዘሮ አበበች ፣ ማሽኑ በትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ፎቶ ተለምኖ የመጣ ስለሆነ ለድርጅቱ የመመለስ ፍላጎት የለም ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ማሽኑ ያለሥራ የተቀመጠ ሲሆን፤ መንግሥት ለሥራ አጥ ወጣቶች አደራጅቶ ሥራ ቢፈጠርበት መልካም እንደሆነም ተናግረዋል። ይሁንና አሁንም ቢሆን ጉባኤ እግዝአብሄር የሚባል ሌላ ድርጅት 200 ተማሪዎችን እየመገበ መሆኑን ገልጸዋል።

የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ደረጀ እንዳወቀ በበኩላቸው፤ ከዳቦ ማሽን ጋር የሚነሳው ወቀሳ አግባብ አይደለም። ስምምነቱም የዳቦ ቤት እንገነባላችኋለን የሚል እንጂ ማሽን እንተክላለን የሚል አልነበረም። በተጨማሪም ማሽኑ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ተተክሎ እንዲሠራ ነገር ግን ንግድ ፈቃድ ደግሞ በግብረ ሰናይ ድርጅቱ እንዲሆን ጠይቀዋል። ይህ አሠራር ከተማሪዎች ምገባ ይልቅ ወደ ንግድ ያደላ ነው፤ በመሆኑም ምገባው መቋረጡን አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር አስተባባሪ ወይዘሪት ሜቲ ታምራት በበኩላቸው፤ የምገባ መርሐ ግብር መንግሥት የሚፈልገውና በትብብር የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። ይሁንና ግብረሰናይ ድርጅቱ መጀመሪያ ስምምነት ያደረገው ከክፍለ ከተማውና ከትምህርት ቤቱ ጋር ነው። በእነዚህ አካላት መካከል የተቀመጠው ችግር እንዲፈቱ ተወያዩ ተብሎ ነበር። ይሁንና ክፍለ ከተማ ብዙ ሞክሮ አልተሳካም ብሎ አሳውቆ ነበር። የከተማው አስተዳደር ስምምነቱ መሰረት በማድረግ ለማስታረቅ ሞክሮ ነበር። አሁንም ቢሆን ከክፍለ ከተማውና ትምህርት ቤቱ ጋር ተስማምተው ችግሩን እንዲፈቱ የከተማው ትምህርት ቢሮ አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።

1942 ዓ.ም የተመሰረተው የስብስቴ ነጋሲ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 የሚገኝና 39ሺ113 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ 94 ሠራተኞች፣ 677 ተማሪዎች አሉት።

አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011

 ክፍለዮሐንስ አንበርብር