በአዲስ አበባ የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ

17
አቶ ሃብታሙ ጥላዬ

 አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በርካታ የኮንትሮባንድ ምርቶች መያዛቸውንና የህገወጥ ንግድ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የአስተዳደሩ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ገለፀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የክስ ምርመራ ቡድን መሪ አቶ ሃብታሙ ጥላዬ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ ምርቶች ተይዘዋል። ከእነዚህም መካከል 482 ኩንታል ለውጭ ገበያ ሊቀርብ የነበረ ቡና ተይዞ ለምርት ገበያ ገቢ ተደርጓል።

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በህገወጥ ምርቶች ዝውውር በህዝብ ጥቆማ በተደረገ ቁጥጥር በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ 50 ቦንዳ ልባሽ ጨርቅ ተይዞ ለጉምሩክ ገቢ ተደርጓል። በተጨማሪ አንድ ኮንቴነር ሙሉ በውስጡ ከያዘው 150 ቦንዳ ልብስ እና 23 ካርቶን መድኃኒት ጋር ተይዞ ከነተሸከርካሪው ለጉሙሩክ ገቢ ተደርጓል። ከተያዙ ንብረቶች መካከል 400 ካርቶን የህፃናት ቅባቶች፣ 15ሺ 802 ሊትር ፓልም ዘይት እና 18 ኩንታል የድጎማ ስንዴ ዱቄት ይገኙበታል።

በተለይም በአቃቂ ቃሊቲ በአንድ የእርዳታ ድርጅት ስም የተከማቸ 62 ዓይነት የተለያዩ አልባሳት፣ምግቦች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች፣ ቸኮሌቶች እና ጫማዎችን ሲሸጡ የነበሩ ሰዎች በፖሊስ ተከሰው በፍርድ ሂደት ላይ መሆናቸውንም አቶ ሃብታሙ አመልክተዋል። በሌላ በኩል ከንግድ ፈቃዳቸው ውጪ በህገ- ወጥ መንገድ የሰዎች ዝውውር ላይ ሲሰሩ የተገኙ 92 ደላሎች ከሠራተኛና ማህበራዊ ጋር በመሆን እርምጃ ተወስዷል።

በዚህም መሰረት 14 ንግድ ቤቶች የታሸጉ ሲሆን አራት የንግድ ቤቶች ንግድ ፈቃዳቸው ተሰርዟል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቤት ሰራተኛ ቅጥር እና ስራ ድለላ ፈቃድ ሳያወጡ ለዕቃ ድለላ ብቻ ባወጡት ፈቃድ ሲሰሩ የተገኙ ሰዎችም ተይዘዋል። ከገንዘብ ዝውውር ጋር ተያይዞ ደግሞ 66 ንግድ ድርጅቶች ያልተፈቀደ የውጭ ገንዘብ ምንዛሬ ላይ ሲሰሩ በመገኘታቸው እርምጃ ተወስዶባቸው ክሳቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን አቶ ሃብታሙ ገልጸዋል።

በሌላ በኩልም በስድስት ወራት በድምጽ ብክለት እና በመጤ ባህል ህብረተሰቡን የጎዱ ጭፈራ ቤቶች እና ጫት ማስቃሚያ እንዲሁም ሺሻ ቤቶች መያዛቸውን ጠቁመው፣ በተለይም የራቁት ጭፈራ ቤቶች መስፋፋት አሁንም አሳሳቢ መሆኑን አመልክተዋል። በዋናነትም ቦሌ አካባቢ የራቁት ጭፈራ ቤቶች እንዲሁም መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ጭፈራ ቤቶች መስፋፋታቸውን ጠቅሰዋል።

ህገወጥነት በከተማዋ መስፋፋቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ያሉት አቶ ሃብታሙ፤ ችግሩን የመከላከል ተግባር የመንግስት ብቻ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ ሲያደርግ የቆየውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011

 ጌትነት ተስፋማርያም