አባ ገዳ – ለሕዝቡ ሰላም የሚለምን «የማገኖ» ተወካይ

23

የጌዴኦ ብሔረሰብ አባላት ባህላዊውን የገዳ ስርዓት ከመመሥረታቸው በፊት በእማዊ ዘመን ይተዳደር እንደነበር ይነገራል። ይህ ዘመን የሴቶች ፈላጭ ቆራጭነት የነገሠበት፣ በወንዶች ላይ የሴቶች የበላይነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ «የአኮማኖዬ» ዘመን ተብሎ ይጠራ ነበር አሉ። «አኮማኖዬ» የቤተ መንግሥት የማዕረግ ስም ሲሆን በዚህ ሥርዓት አንድ ንግሥት ስትሞት ሌላኛዋ ሥርወ መንግሥቱን እየተካች ለረጅም ዓመታት ሕዝቡን እንዳስተዳደሩ በአፈ ታሪክ ይነገርላቸዋል።

በወቅቱ በስልጣን ላይ የነበረው ይኸው የ«አኮማኖዬ» የአስተዳደር ስርዓት በነበረው አምባገነናዊ ባህርይ በወንዶች ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደሩ እና ሊከናወን የማይቻል ትዕዛዝ በመስጠቱ በአመጽ ከስልጣን እንደተወገደ አባቶች ያስረዳሉ። በ«አኮማኖዬ» እግር የተተካው ባህላዊ አስተዳደር «የጐሣሎ» አስተዳደር እንደነበር ተያይዞ ይነገራል።

ይህ የጐሣሎ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት በባህሪይው አሀዳዊና አምባገነናዊ በመሆኑ እንደ ቀድሞው የአንድ ሰው ፊላጭ ቆራጭነት የነገሠበት ነበር። በዚህ የተነሣ የአንድ ጐሣሎ አስተዳደር የሥልጣን መቆያ ጊዜው የተወሰነ ስላልነበር በዕድሜ መግፋት ወይንም በጤና መታወክ ምክንያት ለሚቀጥለው እስከሚያስተላልፍ ድረስ ሕዝቡን በፈላጭ ቆራጭነት ይመራ እንደነበር የብሔረሰቡ የሀገር ሽማግሌዎችና ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ። በጐሣሎው አምባገነናዊ አስተዳደር እጅግ የተማረሩ የብሔረሰቡ አባላት የጎሣሎን መሪ በኃይል በማስወገድ የጌዴኦ ባህላዊ የገዳ አስተዳደር ሥርዓት ለመመስረት በቅተዋል።

በወቅቱ በአዲስ መልኩ የተመሠረተው የገዳ ሥርዓት የተለያየ የስልጣን እርከን ባላቸው ክፍሎች የተደለደለ፣ ሁሉም የየራሳቸውን የሥራ ድርሻ ሊያከናውኑ በሚችሉበት መልክ የተዋቀረ በመሆኑ ሥርዓቱ በባህሪው በጣም ዴሞክራሲያዊ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይገለጻል። ይህ የጌዴኦ የገዳ ሥርዓት ዘጠኝ አባላት የሚገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ ያለው ሲሆን አመራር የሚሰጠው በጠቅላላ ጉባኤው በብሔረሰቡ ቋንቋ በ«ያኣው» ነው።

የያኣው አባላት ልዩ ልዩ የስልጣን ደረጃዎች ያሏቸው ሲሆን እነዚህ የስልጣን እርከኖች በተዋረድ «አባ ገዳ»፣ «ጃላባ»፣ «ሮጋ»፣ «ጃልቃባ»፣ እና «ሀይቻ» በመባል ይታወቃሉ። የሁሉም የበላይ የሆነው አባ ገዳ የሥርዓቱ የበላይ መሪ እና የአንድ አምላክ በምድር ተወካይ (ማገኖ) ለሕዝቡ ሰላምን፣ ብልጽግናን፣ ፍቅርን ጤናን የሚለምን በመሆኑ በሕዝቡ ዘንድ ከማንኛውም ኃጢያት እና መጥፎ ሥራ የነፃ ነው ተብሎ ይታመናል።

ሁለተኛው የስልጣን እርከን «ጃላባ» የሚባለው የአባ ገዳው ምክትል ሲሆን ዋና ተግባሩ ከአባ ገዳው መልዕክት እየተቀበለ ለ«ሮጋ» ዎች የሚያቀብልና ከሌሎችም አካላት መልዕክት በመቀበል ለአባ ገዳው የማድረስ ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው ነው። ሌሎች እርከኖች እንደዚሁ የየራሣቸው ኃላፊነትና የሥራ ድርሻ ያላቸው ሲሆን በዚህ መልኩ የተዋቀረው የጌዴኦ የገዳ ሥርዓት በየስምንት ዓመቱ የስልጣን ርክክብ እንዲደረግ ያዛል። ወቅቱ ሲደርስ ይህን የስልጣን ርክክብ የሚያከናውኑ «ራባ» ዎች ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ስልጣን ተረካቢው «ሉባ»፣ ስልጣን አስረካቢው ደግሞ «ዮባ» በመባል ይታወቃሉ።

የጌዴኦ ብሔረሰብ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ «ማገኖ» ብሎ በሚጠራው አንድ አምላክ እንደሚያምን፤ ይኸው የሰማይ አምላክ ሩህሩህ፣ ከሁሉ የበላይ በተለይም የሁሉ ነገር ፈጣሪ በመሆኑ ሕዝቡ ተገቢ የሆነ ክብርና መስዋዕትን ያቀርባል። በጌዴኦ ባህላዊ እምነት «ወዮ» የሚባሉና ስርዓተ መስዋዕቱን የሚፈፅሙ ከሰባቱም የጌዴኦ ጎሣዎች የተውጣጡ የሃይማኖት መሪዎች አሉ። እያንዳንዳቸው የተለያዩ መንፈሣዊ ተግባራትን የመፈፀም፣ በእምነቱ መሠረት የመመረቅ እና የመርገም የሥራ ድርሻ ሲኖራቸው ከማገኖ ዘንድ ለዝናብ ለመብረቅ ለውሃ ሙላት … ወዘተ የተሰጣቸው የተለያየ «ቃሮ» ወይንም መንፈሣዊ ኃይል እንዳላቸው ይታመናል።

የቀድሞዎቹ የጌዴኦ ብሔረሰብ አባላት ታሪካዊ አመጣጥ በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኘው እና ልዩ ስሙ «ሐርሱ» ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ተነስተው የሐዋጣን ወንዝ ተሻግ ረው «ሐሮ ወላቦ» በዛሬው «ቡሌ ወረዳ» አካባቢ እንደሰፈሩ የብሔረሰቡ የዕድሜ ባለ ፀጋ አዛውንቶች ከአያት ቅደመ አያቶታቸው የተላለፈላቸውን ትውፊት መሠረት አድርገው ይናገራሉ። አያይዘውም እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የጌዴኦ አባቶች እና እናቶች በ«ሐሮ ወላቦ» አካባቢ ከሰፈሩና ከተባዙ በኋላ «አዳ ያኣ» በሚባለው የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታ የሚመሩበትንና የሚተዳደሩበትን ባህላዊና መንፈሣዊ ሥርዓትና ደንብ ማደራጀታቸው ታሪኩን የሚያውቁ የሀገር ሽማግሌዎች አክለው ያወሳሉ።

በእነዚህ ሰዎች አገላለጽ «ደረሶ» የብሔረሰቡ መጠሪያነው ፤ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የነበሩት የገዢ መደቦች የብሔረሰቡን ማንነት ዝቅ ለማድረግ ሲሉ «ደረሶ» የሚለውን በማዛባት «ደራሣ» በማለት ይጠሩት እንደነበር ይነገራል። ስያሜው በብሔረሰቡ አባላት እያሣደረ የመጣውን መጥፎ ጠባሣ ለመፋቅ ሲባል በፊውዳሉ ሥርዓት ወቅት የተሰጠውን ስያሜ «ጌዴኦ» በሚል ስያሜ እንዲተካ በብሔረሰቡ አባላት ጥያቄ ቀርቦ ውሣኔ አግኝቷል።

የጌኤኦዎች አባት የነበረው ደረሶ ከሁለት ሚስቶች የወለዳቸው ሰባት ልጆች እንደነበሩትና እነዚህም ዳራሻ፣ ጐርጐርሻ፣ ደቦኣ፣ ሀኑማ፣ ጤምባኣ፣ ሎጐዳ እና በካሮ በመባል እንደሚጠሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። እነዚህ ከ «ደረሶ» ሁለት ሚስቶች የተወለዱት ልጆች በሙሉ ከጥንት ጀምሮ ሁሉም ጌዴኦዎች እንደሚባሉና የብሔረሰቡ የጐሣ መሠረቶች እንደሆኑ ታሪኩን የሚያውቁ አዛውንቶች ይገልጻሉ። እነዚህ ሰባቱ የጐሣ መሰረቶች በውስጣቸው ሌሎች ንዑሣን ጐሣዎች አካተው ይዘዋል።

በጌዴኦ ብሔረሰቡ ዘንድ ተግባራዊ የሚደረጉ የተለያዩ የጋብቻ ዓይነቶች መካከል «ካጃ» እና «ሀዋዴ» የተሰኙት የጋብቻ ዓይነቶች በብሔረሰቡ ውስጥ በስፋት ተቀባይነት ያላቸው ሲሆን «ቡታ» እና «ዋራዬ ኦልታ» የተሰኙት በአፈፃፀማቸው በህገ ወጥነት ይፈረጃሉ።

ብሔረሰቡ በሕጋዊነት የተቀበላቸው የጋብቻ ዓይነቶች ከመፈፀማቸው በፊት ከጥንት ጀምሮ በዓይነት የሚተገበር የጥሎሽ ሥርዓት ይኖራል። በጥንታዊ የጋብቻ ሥርዓት ጥሎሽ ይሰጥ የነበረው ለአባትና እናት ሲሆን ከሚቀርቡ ስጦታዎች መካከል ለአባት ጠገራ፣ ድርብ ቡልኮ፣ ሂቶ (መቀነት) በዋናነት የሚሰጡ ሲሆን ለእናት ደግሞ ነጠላ ቡልኮ (ዱዳ) ይሰጣል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባህላዊ የጥሎሽ ስጦታ ወደ ገንዘብ ተለውጦ ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

የጥሎሽ ገንዘብ ከፍ ማለት በብሔረሰቡ ዘንድ ሕጋዊ ጋብቻን እያመነመነ በመምጣቱ በገዳ ሥርዓት ጠቅላላ ጉባኤው /ያኣ/ ለአባት ቡልኮ መግዣ ስድሣ ብር፣ ለእናት ደግሞ ሃያ ብር በድምሩ ብር ሰማኒያ እንዲሰጥ ቢወሰንም አንዳንድ የብሔረሰቡ አባላት በገዳ ስርዓቱ የተወሰነውን የጥሎሽ መጠን በመተላለፍ ከብር አንድ ሺ እስከ አንድ ሺ አምስት መቶ የሚደርስ የጥሎሽ ገንዘብ ሲሰጡ ይስተዋላሉ።

በጥቅሉ ኢትዮጵያ በብሔር ብሔረሰቦች የደረጀ ባህላዊ እውቀቶች ባለቤት ናት። እነዚህ እውቀቶችና እሴቶች በብዙ ልናተርፍባቸው የምንችልና ባህርማዶ ሳንሻገር ስልጣኔን ልንቀስምባቸው የሚገቡ ናቸው። ያም ብቻ አይደለም። እነዚህን ባህላዊ እውቀቶች በመጠቀም ለሀገር ሰላም ለህዝብ ብልጽግና በማዋል አገሪቱን የሰላምን፣ የብልጽግናና ፍቅር ማማ ላይ ማስቀመጥ አለብን። ሰላም!

አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2011

 አብርሃም ተወልደ