ጣጣ የማያጣው የቤቶች ግንባታ

170

የዓለም የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መጥቷል። ይህን ተከትሎም የከተሞች መስፋፋት እና በከተማ የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር ጨምሯል። በ2007 ዓ.ም. ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ከ13,000,000 (አሥራ ሦስት ሚሊዮን) በላይ የሚሆኑ ዜጎች በከተሞች ይኖራሉ። ስለሆነም የኢፌዴሪ መንግሥት በሀገሪቱ የተለያዩ ትላልቅ ከተሞች የኗሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የተፈጠረውንና ወደፊትም ሊፈጠር የሚችለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ፤ ከተሞችን ዘመናዊ ለማድረግ እና ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ለዜጎች እንዲሰጡ ለማስቻል እንዲሁም ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንደየዓቅሙ ለመኖሪያ እና ለመሥሪያ የሚሆን ቤት ለማቅረብ የሚያስችል ፖሊሲ በ1995 ዓ.ም በመንደፍ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የተቀናጀ የቤቶች ልማት ፕሮግራም በከተሞች እያከናወነ ይገኛል።

ስለሆነም የቤቶች ልማት ፕሮግራም በከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ እና ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚመጥኑ የቤት ልማት ሥራዎችን በማከናወን የከተማ መተፋፈግንና እርጅናን ከማስወገድ ባሻገር የመጠለያ ችግርን ይቀርፋል። የቁጠባ ባህልን በማዳበር እና ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ከዚህ በተጨማሪ የአብዛኛውን ሕዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እንዲሁም የተለያዩ አማራጮችን የሚያቀርቡ የቁጠባ ቤቶችን ለማስፋፋት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት እየተከናወነ ባለው የቤቶች ልማት ፕሮግራም በ11 ዙሮች ከ182,459 (አንድ መቶ ሰማንያ ሁለት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ) በላይ ዜጎችን  የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

እንደ ዕቅዱ ቢሆን ኖሮ ከዚህም በላይ ቁጥር ያላቸው ዜጐች ተጠቃሚ በሆኑ ነበር፤ ነገር ግን ከተቋሙ በሙስና መተብተብ፣ ከጥሬ ዕቃ አቅርቦትና ከግንባታ አቅም ማነስ ጋር በተያያዘ የ40/60 ዓ.ም ሆነ ሌሎች ግንባታዎች ሲንፏቀቁ ይስተዋላሉ፤ በዓመት ያልቃሉ ተብለው የተጀመሩ የ40/60 ቤቶች በአራትና በአምስት ዓመት እንኳ አለመጠናቀቃቸው የተቋሙን የጐላ ችግር የሚያመለክት ነው፤ ሲጐተቱ ኖረው በብዙ ጣጣ ያለቁት ቤቶችም ጣጣቸው ብዙ ነው። የኮንዶሚኒየም ቤት በዕጣ ማግኘት የሚፈጥረው ደስታ ከፍተኛ የመሆኑን ያህል ቅድመ ክፍያውን እና ወርሐዊ ክፍያውን ወቅቱን ጠብቆ መክፈል ከፍተኛ ጭንቀት የሚፈጥርባቸው ብዙዎች ናቸው።

በዕጣም ይሁን በልማት ተነሽነት የኮንዶሚኒየም ቤት ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች ‹‹ከዚህ የበለጠ ነገር አያጋጥመኝም›› በሚል ስሜት ቅድመ ክፍያውን ከዘመድ አዝማድ በመዋጮም ሆነ በብድር ከፍለው የዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑ ከአንድ ዓመት የብድር የእፎይታ ቆይታ በኋላ ሌላው ጭንቀት ይጀምራል። የአንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ እንደተጠናቀቀ ተበዳሪው በየወሩ የተተመነውን ክፍያ መክፈል ይጠበቅበታል። ይህ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለሙያዎች ስልክ እየደወሉም ሆነ በቤቱ ላይ ደብዳቤ በመለጠፍ እንዲከፈል ይጠይቃሉ። የመኖሪያ ቤት ልማት ዓላማ የቤት ልማት ሥራዎችን ወጪ ቆጣቢና ከነዋሪው ኅብረተሰብ የመክፈል ዓቅም እና የመግዛት ፍላጎት ጋር የሚመጥኑ በማድረግ በተለያዩ ደረጃ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ባለቤት ማድረግ ነው።

ይሁን እንጂ ይህ መሠረታዊ ዓላማው ግቡን በታቀደለት አግባብ እንዳይመታ በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመውታል። በዋናነትም በፕሮግራሙ መሠረት የብድር አቅርቦት፣ የወለድ ምጣኔ፣ የአከፋፈል ሁኔታ በተጠቃሚዎች ላይ ቅሬታ እየፈጠረ ይገኛል። የቅሬታው ይዘት የሚከተለውን ይመስላል። የደንበኞች ቅሬታ አቶ ተሰማ ኤሊሶ ይባላሉ። በዕጣ የኮንዶሚ ኒየም ቤት የደረሳቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበዳሪ ናቸው። የእፎይታ ጊዜው በማለቁ በየወሩ መክፈል የሚገባቸውን ክፍያ መክፈል እንዳለባቸው፤ እርሳቸው ግን መክፈል እንዳልጀመሩ የባንኩ ባለሙያ በስልክ ያስጠነቅቋቸዋል።

በዚህ አጋጣሚ የሆኑትን እንዲህ ይላሉ፤ ‹‹በወቅቱ ቤቱ አልቆ ስላልተረከብኩኝ ተከራይቼ ለምኖርበት ቤት እና ለባንክ የምከፍለው ስለሌለኝ በጣም ደንግጬ ነበር። ስለዚህ በየጊዜው እየተደወለ ካልከፈልክ ሲሉኝ፤ የተዋዋልኩበት ባንክ ቤት ሄጄ ቤቱ እንዳልደረሰኝ እና ያለብኝን ችግር ለማስረዳት ስሞክር እነሱ ይህ ጉዳይ እንደማይመለከታቸው ነገሩኝ። በውሉ መሠረትም ባልከፈልኩኝ ቁጥር የወለዱ መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ፤ የክፍያ ውዝፉ ከሦስት ወር ካለፈ ችግሮች እየባሱ እንደሚሄዱ ሲነገረኝ ጭንቀቴ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ለደምግፊት በሽታ ተዳረግኩኝ። ሌሎች በሽታዎች እንዳይጨማመሩብኝ እና ህይወቴን እንዳላጣ በሚል ቤቱን በመሸጥ እዳውን ከፍዬ ከቤት ዕጣ ዕድለኛነት ወደ ቋሚ ተከራይነት ተመለስሁ።

በዚህም ሁለተኛ የቤት ባለቤት መሆን እንዳላስብ ሆኛለሁ።›› ወይዘሮ መሠረት ታደሰ በልማት ተነሺነት በደረሳቸው የኮንዶሚኒየም ቤት በየወሩ 2,704 (ሁለት ሺህ ሰባት መቶ አራት ብር) ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመክፈል ተዋውለው በየወሩ እየከፈሉ በሠላም ይኖሩ ነበር። ዕቁብ ሲደርሳቸው ለሌላ ጉዳይ ከማውለው ለቤት ክፍያ ልጠቀምበት በሚል ሀሳብ የሦስት ወሩን በአንድ ጊዜ 8,112 (ስምንት ሺህ አንድ መቶ አሥራ ሁለት ብር) ለወርሐዊ ክፍያ በተከፈተላቸው ቁጥር ገቢ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ ከወር በኋላ ከባንኩ ይደወልና ‹‹የኮንዶሚኒየም ብድር ክፍያ ስላልከፈሉ ይክፈሉ›› የሚል መልዕክት ይነገራቸዋል። ይህን እንደሰሙ ‹‹ከፍያለሁ›› በማለት ይከራከራሉ።

የባንኩ ባለሙያም ከፍያለሁ ካሉ የከፈሉበትን የሚያሳይ ደረሰኝ ይዘው እንዲቀርቡ ይገልፅላቸዋል። የሦስት ወር የከፈሉበትን ደረሰኝ ይዘው ይሄዳሉ። ያነጋገራቸው ባለሙያ ደረሰኙን አይቶ ‹‹ባለፈው ወር የተከፈለ ስለሆነ፤ የዚህን ወር ስላልከፈሉ እንዲከፍሉ ነው የተጠየቁት›› አላቸው። ስለዚህ ቀደም ብለው ገቢ ያደረጉት የሦስት ወር ክፍያ ከባለዕዳነት ሊታደጋቸው አልቻ ለም። ለማስረዳት ቢሞክሩም አድማጭ አላገኙም። በመጨረሻም ከባለሙያው ገለፃ መረዳት የቻሉት ለዚህ ችግር የዳረጋቸው ባንኩ የሚጠቀምበት “ሲስተም” ነው።

ከብድር ወርሐዊ ክፍያ አንፃር ባንኩ የሚጠቀምበት “ሲስተም” ደንበኛው ውል ሲዋዋል ገቢ እንዲያደርግ ከተቀመጠለት ቀን ቀድሞ ቢከፍል፤ ገቢ የተደረገውን መጠን ከዕዳ ላይ ይቀነሳል እንጂ በወሩ እንደከፈለ አይቆጥርም። ስለዚህ የውል ቀኑን እየጠበቁ መክፈል ያስፈልጋል። ወ/ሮ መሠረትም በውል ባልተረዱት ሲስተም ምክንያት ንግድ ባንክ በፈጠረባቸው አስገዳጅ ሁኔታ ከዕቅዳቸው ውጭ ቤቱን አከራይተው ሌላ ቦታ በመከራየት 2,704 (ሁለት ሺህ ሰባት መቶ አራት ብር) ከፍለው ከባለቤትነት ወደ ተከራይነት መመለሳቸውን ይናገራሉ። አቶ ዋስይሁን ታደሰ ደግሞ የተዋዋሉበት የአንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ ሳይጠናቀቅ በስልክ ተጠርተው እንዲከፍሉ ይነገራቸዋል።

ክፍያ የሚጀምሩበት ጊዜ ያልደረሰ መሆኑን ለማስረዳት ወደ ባንክ ቤት ባቀኑበት ወቅት፤ ውሉን ሲፈርሙ በአግባቡ ያልተረዱት ብዙ ነገር ያጋጠማቸው መሆኑን ገልፀዋል። በተለይ በተሰጣቸው የአንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ ውስጥ ወለድ እንደሚታሰብባቸው የማያውቁ መሆኑን ተናግረዋል። ወይዘሪት ሶስና አብርሃ በዕጣ በደረሳት የኮንዶሚኒየም ቤት በመኖር ላይ ትገኛለች። ምንም እንኳ የተረከበችው ቤት በተገቢው ሁኔታ ሳይጠናቀቅ መረከቧ ተጨማሪ ወጪዎች እንድታወጣ ያስገደዳት ቢሆንም፤ የራሷ በሆነ ቤት መኖር በመጀመሯ መንግሥትን ታመሰግናለች።

ይሁን እንጂ የብድር አሰጣጡ እና አከፋፈሉ ሂደት ላይ አስተያየት አላት። ይህንም ስታብራራ ‹‹የክፍለ ከተማ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ለቤቱ ሽያጭ ውል ካዋዋለ በኋላ፤ የብድር አገልጋሎቱን ከሚሰጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሄደህ የብድር ውል እንድትዋዋል ይልክሃል። ባንክ ቤቱ የራሱን ውል ከደንበኛው ጋር ሲያዋውል የተዘጋጀውን የውል ሠነድ አንብበህ የምታገናዝብበት ጊዜ አይሰጥህም፤ ወከባ ስለሆነ በፍጥነት እንድትፈርም ያደርግሃል። ውሉ በደንብ ቢነበብም እንኳን በተገቢው ሁኔታ ያልተብራሩ ነገሮች አሉት። ለምሳሌ ውሉ ላይ ‹ያልተከፈለ የዕዳ ክፍያን ከሌላ የንግድ ባንኩ ሂሳብ የቁጠባ ደብተር (ሂሳብ) ካለ መውሰድ ይችላል› የሚል አለ። ይህን ብዙ ሰው አልተረዳውም፤ ባንኩ ገንዘብ ሲወስድ እንኳን ለደንበኛው አያሳውቅም፤ ደረሰኝም አይሰጥም።

ውሉም በብቸኝነት ለሚያበድረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊጠቅም በሚችል መልኩ ስለተዘጋጀ ጫናዎችን በሙሉ ተቀብሎ መዋዋል ብቸኛው አማራጭ ይሆናል። ዕድሉ ለሌሎች ባንኮችም ተሰጥቶ ቢሆን፤ የተለያዩ አማራጮች ስለሚኖሩ ተበዳሪው ወደ ተሻለውና ወደ መረጠው በመሄድ ወዶ እና ፈቅዶ የመስተናገድ ዕድል ይኖረው ነበር። አበዳሪ ተቋማቱ ቢበዙ ውድድር ስለሚኖር ለተበዳሪዎች አማራጭ የአከፋፈል ሥርዓት እና የወለድ ምጣኔ ይፈጥሩ ነበር›› በማለት ገልፃለች። ወ/ሪት ሶስና የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጄንሲ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግንባታውና በብድሩ ሂደት በተገቢው ሁኔታ ባለመናበባቸው ከተበዳሪዎች ለሚነሳው ጥያቄ የሁለቱም ምላሽ ‹‹እኛን አያገባንም›› የሚል ነው ብላለች።

አጠቃላይ ሁኔታውን ስትገልፅም ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር ሥርዓቱ ግልፅነት የጎደለው፣ ቀላልነት የሌለው እና ፍትሐዊ ባለመሆኑ፤ ተበዳሪውን ዕዳ ውስጥ የሚከት፣ የሚያጨናንቅ እና በሞኖፖል የተያዘ ነው። ስለዚህ ፕሮጀክቱ መንግሥት ባቀደው ዓላማ ልክ እንዲተገበር፤ በኢትዮጵያ ያሉ የንግድ ባንኮች በብድር አገልግሎቱ መሳተፍ የሚችሉበት ዕድል ለመፍጠር መንግሥት አሠራሩን ሊፈትሽ ይገባል›› በማለት ተናግራለች። ሌላው ለዚህ ዝግጅት መረጃ የሰጡን ዶክተር ከበደ መገርሳ ናቸው። በዕጣ በደረሳቸው ኮንዶሚኒየም ቤት ቅድመ ክፍያ ከከፈሉ ከሁለት ዓመት በኋላ ነው የገቡበት። ነገር ግን ቤታቸውን ከመረከባቸው በፊት ለነበሩት ከሁለት ዓመት በላይ የብድር ወለድ እና የኢንሹራንስ ክፍያ ከፍለዋል።

ዶክተር ከበደ በብድር አከፋፈል ወቅት ያጋጠማቸውን ሲናገሩ ‹‹ ከታህሳስ 21 ቀን ጀምሮ በየወሩ 3,200 (ሦስት ሺህ ሁለት መቶ ብር) ለ14 ዓመት ለመክፈል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ውል ተዋውለናል። በአንድ ወቅት በተባልኩበት ቀን ሳይሆን ቀደም ብዬ ደመወዝ እንደተቀበልኩኝ የተተመነውን ብር ማስገባት ጀመርኩኝ፤ የተወሰነ ወር ከከፈልኩኝ በኋላ ስልክ ተደውሎ ሁለት ወር አልከፈልክም፤ እንድትከፍል የሚል መልዕክት ተነገረኝ።

በየወሩ የከፈልኩበትን ደረሰኝ አሳየሁ። ‹መክፈል ከሚገባህ ቀን በፊት ስላስገባህ ሲስተሙ አያነበውም። ስለዚህ የሁለት ወር መክፈል አለብህ› የሚል ቀጭን ትእዛዝ ተነገረኝ። ውላችን የሚለው በየወሩ መክፈል እንዳለብኝ እንጂ ቀደም ብሎ ከገባ ሲስተሙ አያነብም የሚል አይደለም፤ ቀደም ብዬ ሳስገባ ሲስተሙ ማንበብ እንዲችል ተደርጎ መስራት ይቻላል፤ አሠራራችሁን አስተካክሉ ብዬ ሄድኩኝ። ከትንሽ ቀን በኋላ በየወሩ መክፈል የሚገባህን ገንዘብ አቋርጠሃል ተብሎ ቤቴ ላይ ማስጠንቀቂያ ተለጠፈ። በድጋሚ በመሄድ ስለደረሰብኝ ሁኔታ ሳስረዳ ፊደል ቆጥሬያለሁ ለምለው ሰው ማስረዳት በተቸገሩበት ሁኔታ ምላሽ ሰጡኝ። በጣም የሚያሳዝነው ከሌላ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ሂሳቤ ላይ ለእኔ ሳያሳውቁ እና ደረሰኝ ሳይሰጡኝ የወርሐዊ ክፍያውን መጠን ቀንሰው ወስደዋል።

ይህንን ያወኩት በሌላ ጊዜ ሂሳብ ለማስገባት ስሄድ ሂሳቤ ላይ ቅናሽ በማየቴ ነው። ስለሁኔታው ስጠይቅ ‹የኮንዶሚኒየም ቤት ዕዳ ስላለበት ተወስዷል› ተባልኩኝ›› ብለውናል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‹‹የሚተማመኑበት ባንክ›› መባሉ ምኑ ላይ ነው? የሚሉት ዶ/ር ከበደ፤ ‹‹ከሌላ ሂሳቤ ላይ ሲቀንሱ፤ ቢያንስ ማሳወቅ እና ደረሰኝ መስጠት ይገባቸው ነበር። ሌላው የባንኩ ችግር የወለድ አሰላሉ ግልጽ አይደለም፤ ለምሳሌ ከ27 ወር በላይ 90,000 (ዘጠና ሺህ ብር) ከፍያለሁ። ከዋናው ብድር ላይ የተቀነሰልኝ ግን 11,000 (አሥራ አንድ ሺህ ብር) ብቻ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ቀሪ ክፍያ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ የግድ ወደ ተዋዋሉበት ባንክ መሄድ የግድ ይላል።

ባንኩ የተሻለ አሠራር በመዘርጋት ክፍያ በሚፈፀምበት ማንኛውም ቅርንጫፍ ምላሽ መስጠት ይገባቸዋል። ዘመኑ ቴክኖሎጂ በርካታ ሥራዎችን ያቃለለበት በመሆኑ፤ ሌሎች የባንኩን አገልግሎቶች በሞባይል ስልክ እንደሚያሳውቁት ሁሉ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ጋር ያለውንም በምዝገባ ወቅት በሞላነው የሥልክ አድራሻ ማሳወቅ ቢችሉ የተገልጋዮችን መጉላላት ከመቀነሳቸውም በላይ ግልፅነት የሰፈነበት አሠራር መጠቀም ያስችላቸዋል›› በማለት አስተያየታቸውን ገልፀዋል። የምሁራን አስተያየት አቶ ታረቀ አያሌው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ በአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል መምህር እና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ናቸው።

ከተበዳሪዎች ከተነሱ ቅሬታዎች በመነሳት ሙያዊ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ጠይቀናቸዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለኮንዶ ሚኒየም ቤት ዕድለኞች ከሚሰጠው የብድር አገልግሎት ጋር በተያያዘ ተበዳሪዎች ለሚያነሷቸው ቅሬታዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ‹‹የብድር ውል ከመቅረቡ በፊት የብድሩ መጠን፣ ብድሩ በምን ያህል ጊዜ እና የወለድ ምጣኔ እንደሚሰላ እንዲሁም ከብድሩ ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ የተለያዩ ሥርዓቶች እና ወጪዎች ምን ምን እንደሆኑ ተበዳሪው በሚገባው መልኩ በቅድሚያ በተገቢው ሁኔታ እንዲያውቀው መደረግ አለበት።

ምክንያቱም አንደኛ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል፤ ሁለተኛ የብድር ሥርዓቱን በማየት ለመበደርም ሆነ ላለመበደር ሊወስን ይችላል። ተበዳሪው ስለሚዋዋለው ውል ቀደም ብሎ እንዲረዳው እና እንዲያውቀው ማድረግ የባንኩ ግዴታ ሲሆን፤ ተበዳሪው ደግሞ መብቱ ነው። የብድሩን ውል በተገቢው ሁኔታ ሳይረዳው እና ሳያውቅ ውል እንዲዋዋል ማድረጉ ተገልጋዩ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ስለማይችል ገባ በተባለው ውል መሠረት መክፈል ይቸገራል። በመሆኑም ተበዳሪው የተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ይገባል። ይህም በመሆኑ በኢኮኖሚ ይጎዳል፣ በአካልም ሆነ በሥነ-ልቦና ረገድ በራሱም ሆነ በቤተሰቡ ላይ የሚደርስ ጫናም ይፈጠራል። ስለዚህ የተለያዩ አማራጮችን እንዲያይ ይገደዳል።

በአማራጭነት ሊታዩ የሚችሉትም በብድር ወደተጨማሪ ዕዳ መጋባት አሊያም ቤቱን ሸጦ ወደ ዘላቂ ተከራይነት መግባት ነው። ይህ ደግሞ መንግሥት ያስቀመጠው ዓላማ እንዳይሳካ ያደርጋል›› በማለት ይጀምራሉ። የብድር አቅርቦቱ በአንድ የባንክ ተቋም ብቻ መሆኑ በተበዳሪው ኅብረተሰብ ላይ የሚፈጥረውን ጫና አስመልክተው ሲናገሩ ‹‹የብድር አቅርቦቱ በአንድ ባንክ ብቻ መሆኑ፤ ተበዳሪው አማራጮች ስላልቀረቡለት በጣም ይጎዳል። ከወለድ ምጣኔ እንዲሁም ከጊዜ አንፃር የሚያዋጣውን እና የሚቀንስለትን እንዳያይ አድርጎታል። አማራጮች ቢኖሩ ውድድር ስለሆነ የተሻሉ ሁኔታዎችን ሊያማትር ይችል ነበር። እየቀረበ ያለው የብድር አሰጣጥ ሲታይ ግን አሁን የተያዘው አካሄድ አስገድዶ ማበደር ነው።

ምክንያቱም ተበዳሪው ቤት ስለሚፈልግ እና አማራጭ ስላልተሰጠው ከሚቀርበት (ዕድሉን ከሚያጣ) ሳያምንበትም ቢሆን ለመዋዋል ይገደዳል። ስለዚህ በነፃ የኢኮኖሚ ሥርዓት መርህ በምትመራ ሀገር በአንድ ባንክ ብቻ የብድር አገልግሎቱ መሰጠቱ ተገቢነት የለውም›› በማለት ይገልፃሉ። ከብድር አቅርቦት አንፃር መንግሥት ማድረግ የነበረበት ብለው የሚያምኑትን ሲያስረዱም፤ ‹‹ሁሉም የንግድ ባንኮች ለኮንዶሚኒየም ቤት ተበዳሪዎች የተሻለ የብድር እና የወለድ አማራጭ ይዘው እንዲቀርቡ እኩል ዕድል ሊፈጠር ይገባው ነበር። ይህን ባለማድረጉም ተበዳሪው ላይ ጫና ተፈጥሯል።

ከዚህ በተጨማሪም በአበዳሪው ንግድ ባንክ ላይም በማስተዳደሩ ረገድ ጫና ተፈጥሯል። ምክንያቱም ባንኩ ይህን አገልግሎት ለመስጠት ብቻ ተጨማሪ ቢሮዎችን ለመክፈት ተገድዷል። ሌሎች ባንኮች ተከፋፍለውት ቢሆን ተጨማሪ ቢሮ እና ሠራተኛ ሳያስፈልግ ባላቸው ዓቅም ሊሰሩት ይችሉ ነበር። ይህ ደግሞ ለተበዳሪዎቹም ሆነ ለባንኮቹ በጣም ጠቃሚ ይሆን ነበር›› ብለዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ ላይ አውየዋለሁ ከሚለው “ሲስተም” አንፃር ተበዳሪዎች የሚያቀርቡትን ቅሬታ በተመለከተም አቶ ታረቀ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፤ ‹‹አብዛኞቹ ተበዳሪዎች ገቢያቸው አነስተኛ ስለሆነ በየወሩ ክፍያ እንዲፈጽሙ መደረጉ ለተበዳሪውም ለባንኩም ጥቅም አለው። ከሚከፈልበት ቀን ቀድሞ መክፈል ይበረታታል፤ ባንኩም ቀደም ብሎ ገንዘቡን ማግኘቱ ይጠቅመዋል።

ተበዳሪዎች ቀድመው በመክፈላቸው እንዳልከፈሉ ተደርጎ እየተጠሩ አላስፈላጊ መጉላላት እና እንግልት የሚደርስባቸው ከሆነ ባንኩ ላይ አሉታዊ አመለካከት እንዲፈጠር ያደርጋል። “ሲስተሙ” ነው የሚለው ምላሽ ተገቢ አይደለም። “ሲስተሙ”ን የሚያዘጋጀው ሰው ነው። ቀድሞም ይሁን ዘግይቶ ክፍያ ቢፈፀም የተከፈለው ተቀንሶ ሂሳብ የሚሰላበት ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል እንጂ ተበዳሪውን ያላማከለ ሥርዓት መዘርጋት አይገባም። በተለያዩ ምክንያቶች ከተዘረጋም ተበዳሪዎች የሚያነሱትን ጥያቄ እና ፍላጎት ባማከለ መልኩ ማስተካከል ይገባል። ይሄ የሚያሳየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቂ ጥናት እና ዝግጅት ሳያደርግ በግዴታ ሥራ ተብሎ የተጣለበት መሆኑን ነው።

ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ በኤ.ቲ.ኤም፣ በኢንተርኔት ባንኪንግ እና በሞባይል ባንኪንግ የተቀላጠፈ አገልግሎት ይሰጣል። በሌላው ሳይታማ በዚህ ለምን ቅሬታ ይቀርብበታል? ከዚህ መረዳት የሚቻለው አንድም በግዴታ ወይም በቂ ጥናት እና ዝግጅት ሳያደርግ መግባቱን ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ለንግድ ባንኩ ጥሩ አይደለም። ተበዳሪው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ቅሬታዎቹ በተገቢው ሁኔታ ካልተፈቱ አንዴ ብድሩን ልክፈል እንጂ ዞር ብዬ ወደ ባንኩ አላይም የሚል ስሜት ሊያሳድር ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ተበዳሪዎች ሥራ ፈተው መጉላላታቸው ለአገርም የሚበጅ አይደለም›› በማለት ገልፀዋል።

የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ምሁሩ ከባንክ አሠራር ጋር በተያያዘ ደንበኛው ሳያውቅ በሌላ ቅርንጫፍ ካለው የቁጠባ ሂሳብ ላይ ደረሰኝ ሳይሰጥ መውሰዱን በተመለከተ ለሚነሳው ቅሬታ አስተያየታቸውን ሲሰጡም ተበዳሪው ዕዳውን መክፈል በሚገባው ጊዜ በወቅቱ ካልከፈለ፤ በባንኩ ከሚገኝ የደንበኛው ሌላ ሂሳብ ላይ ተገቢውን የገንዘብ መጠን መውሰዱ አግባብ መሆኑን አመልክተው፤ ነገር ግን በቅድሚያ ያልተከፈለውን የገንዘብ መጠን ጠቅሶ ሊቀንስ (ሊወስድ) መሆኑን ማሳወቅ እና ለመቀነሱም ማስረጃ መስጠት እንዳለበት ግን አሳስበዋል። በእርሳቸው አባባል መሠረት አንድ ተበዳሪ ‹‹ከፍያለሁ›› እያለ እና ለመክፈሉም የሚያስረዳ ደረሰኝ እያሳየ እንዳልተከፈለ ተቆጥሮ ከሌላ ሂሳቡ የሚቀነስበት አሠራር ተገቢ አይደለም ማለት ነው።

እኝሁ ምሁር እና ባለሙያ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዚህ አገልግሎት እየተጠቀመበት ያለውን “ሲስተም” መፈተሽ እና ማስተካክል ይጠበቅበታል›› በማለት ጉዳዩ እንዲጤን ምክር ለግሰዋል። የባንኩ ተገልጋዮች ቅሬታ የሚያቀርቡበት ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ በግንባታ ላይ እያለ እና ርክክብ ባልተደረገበት ሁኔታ ወለድና የኢንሹራስ ክፍያ እንዲከፍሉ መጠየቃቸው ተገቢ አለመሆኑን ነው። በዚህም ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የጋ በዝናቸው አቶ ታረቀ ‹‹የቤት ግንባታውና የብ ድር አሰጣጡ በቅድሚያ በተገቢው ባለሙያ አለመጠናቱ ግንባታው በጥራት አለመከናወኑ፣ በጊዜ አለመድረሱ እና ይህን ተከትሎ አላስፈላጊ ዋጋ በመጨመር በኩል የሚታዩ ችግሮች አሉ።

መንግሥት በኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ ድጎማ አድርጌያለሁ ይላል። ነገር ግን የተደረገው ድጎማ ዋጋው ላይ አይታይም። ሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ የባንክ ወለድ እና የኢንሹራንስ ክፍያ እንዲከፍሉ መደረጉ ተገቢ አይደለም።›› ይላሉ። የኮንዶሚኒየም ቤት ብድርን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በራሱ አመንጭቶ የሚፈጽመው እንደማይመስላቸው የሚናገሩት ምሁሩ የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫ ስለሆነ ብቻ የሚያስፈጽመው እንደሆነ ያስባሉ። ከእንደዚህ ዓይነት ችግር ለመውጣትም እንደ ሞርጌጅ ያለው ባንክ (ቤቶች ግንባታ ላይ ለረጅም ጊዜ ብድር የሚሰጥ) አካል ቢሠራው አጀማመሩ በጥናት ላይ ስለሚመሠረት እና በቂ ዝግጅት አድርጎ የብድር ሥርዓቱን ስለሚዘረጋው ለተበዳሪዎች የገንዘብ መጠኑም ሆነ ወለዱ ላይበዛባቸው እንደሚችል ያላቸውን እምነት አስረድተውናል።

አክለውም ‹‹የሞርጌጅ ዓይነት አሠራር ሲፈጠር ደግሞ ተበዳሪዎች የተለያዩ ጫናዎች ውስጥ በመግባት በቤቱ መኖር እየፈለጉ ለመሸጥ አይገደ ዱም። ምክንያቱም እንደሞርጌጅ ያሉ ባንኮች ብድር ከመስጠታቸው በፊት ለተበዳሪዎቻቸው የተለያዩ አማራጮችን እና የምክር አገልግሎቶችን ይሰጣሉ።›› ብለዋል። የባለሙያው መደምደሚያም በዓቅም ማነስ ምክንያት በቤቱ መኖር ያልቻሉ መኖራቸው፣ ብድር ለመክፈል ሲሉ በተዳከሙ ቤቶች እየኖሩ ቤቶቻቸውን ማከራየታቸው፤ የተወሰኑት ደግሞ ሸጠው የቤት ባለቤት መሆናቸውን ማጣታቸውን በማሰብ ፕሮግራሙ የአዲስ አበባን የቤት ቁጥር ቢጨምርም የሚገባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የቤት ችግር ስላልፈታ የአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን በተመለከተ መንግሥት ያቀደለትን ዓላማ አልተሳካለትም የሚል ነው።

በመጨረሻም የብድር ሥርዓቱ በቀጣይ ምን መምሰል እንዳለበት ሲያብራሩ ‹‹የከተማ አስተዳደሩ የኮንዶሚኒየም ቤት ለሚገባቸው ግለሰቦች የመሬት አቅርቦቱን ቢያመቻች፣ ለግንባታ ሂደቱ ደግሞ የብድር አገልግሎት የሚሰጡ ሞርጌጅ ባንኮች ተቋቁመው የገንዘብ ብድር ሥርዓቱን እና የግንባታውን ሁኔታ እንዲያስተዳድሩ ቢደረግ ፕሮጀክቱ ለታለመለት ዓላማ መዋል ይችላል። ይህ ሲሆን የኮንዶሚኒየም ቤት ሲሠራ በምን ያህል ጊዜ ምን ያህል ቤት ይገነባል?፣ ሥራውን ለማጠናቀቅ ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል? እንዲሁም ለእያንዳንዱ የቤት ዓይነት ተገቢ የሆነው ዋጋው ምን ያህል ሊሆን ይችላል? የሚለው ሙያዊ በሆነ ጥናት ሊታወቅ እና ሊተገበር ይችላል።

ሙያዊ ጥናት ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ ሲሆን፤ ቤት ፈላጊው ኅብረተሰብ ከአሥራ ሁለት ዓመታት በላይ አይጠብቅም። ሞርጌጅ ባንኮች ከመንግሥት ጋር በመነጋገር እና በማጥናት ተበዳሪው በአጠቃላይና በየወሩ ይህን ያህል ሊከፍል ይገባዋል ተብሎ በግልጽ እንዲቀርብለት ይደረጋል። በቀረበለት መረጃ ተመሥርቶም ተበዳሪው ዓቅሙ የሚፈቅድለትን የቤት ዓይነት መምረጥ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ከአበዳሪው ተቋም ጋር ሲዋዋልም ሙሉ መረጃው ውል ከሚደረግበት ቀን በፊት በተገቢው እና በተብራራ ሁኔታ እንዲያውቀው ማድረግ ያስፈልጋል›› በማለት ሙያዊ አስተያየታቸውን አካፍለዋል።

የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ከላይ በቀረበው መረጃ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጄንሲ ገንብቶ ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ እያስተላለፋቸው ባሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር በተያያዘ ከባንክ የብድርና የወለድ አከፋፈል ላይ ከተበዳሪዎች የሚነሱ ቅሬታዎችን እና ከባለሙያ የተሰጡ አስተያየቶችን ይዘን የሚመለከታቸውን የባንክ የሥራ ኃላፊዎችን ለማነጋጋር ጥረት አድርገናል። በዚያም መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮንስዩመርና የቤቶች ብድር ዳይሬክተር አቶ መዝገበ ይፍሩ ለዘመን መጽሔት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕድለኞች ጋር የብድር ውል የሚዋዋለው መጀመሪያ ዕድለኞቹ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት የሽያጭ ውል ካደረጉ በኋላ ነው።

በብድር ውሉ ላይም የመኖሪያ ቤት ተበዳሪዎች ሊያውቋቸው የሚገቡ መሠረታዊ ነጥቦች በግልጽ ተቀምጠዋል። የውል ሠነዱን አንድ ቅጅ ተበዳሪ ይወስዳል። በውሉ ላይም፤ ለስቲዲዮ እና ለባለ አንድ መኝታ ቤት የብድሩን ገንዘብ በሃያ ዓመት፤ ለባለ ሁለት እና ለባለሦስት መኝታ ቤቶች በአሥራ አምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚከፈል፤ ለሁሉም ዓይነት ቤቶች ተበዳሪዎች የአንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ እንደሚሰጥ፤ ከአንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ ቆይታ በኋላ በየወሩ የተዋዋለውን የክፍያ መጠን መክፈል እንደሚጀመር፤ በአንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ ውስጥ ውሉ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በተበደረው የገንዘብ መጠን ወለድ የሚታሰብ መሆኑን፤ የኢንሹራንስ ክፍያ መኖሩ፣ ተበዳሪው የእፎይታ ጊዜው ተጠናቅቆ ወርሐዊ ክፍያ መክፈል ካልጀመረ ወይም መክፈል ከጀመረ በኋላ ቢያቋርጥ ዘጠና ቀን ከቆየ ከዘጠና አንደኛው ቀን ጀምሮ በውል ጊዜ ከነበረው የወለድ ምጣኔ 3% ተጨማሪ የብድር ምጣኔ እንደሚኖር (ከ9.5% ወደ12.5%) እና የወለድ ምጣኔው በተለያየ ጊዜ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው ስሌት መሠረት ሊጨምር ወይም ሊቀንስ እንደሚችል በውሉ ላይ የተካተቱ መሆናቸውን አቶ መዝገበ ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ የኮንዲሚኒየም የመኖሪያ ቤት ባለቤቶች ከንግድ ባንክ ጋር የብድር ውል ከፈፀሙ በኋላ በውሉ መሠረት በየወሩ ክፍያ መክፈል አይጀምሩም፤ ወይም ከጀመሩ በኋላ ያቋርጣሉ። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት አበዳሪው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያከናውናቸውን ቅደም ተከተላዊ እርምጃዎችን በተመለከተ አቶ መዝገበ ሲያስረዱ፤ ‹‹በየወሩ መከፈል የሚገባው የገንዘብ መጠን ካልተከፈለ በስልክም ሆነ ቤቱ በሚገኝበት ስፍራ በመገኘት በደብዳቤ የገንዘብ መጠኑን በመጥቀስ እንዲከፈል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ዘጠና ቀን ካለፈው እና ካልተከፈለ በውላችን መሠረት ለአዲስ አበባ መስተዳድር ተበዳሪያችን ዕዳውን ስላልከፈለን ተተኪ ላኩልን እንላለን። ተተኪ ሊልኩም ላይልኩም ይችላሉ፤ ካልተላከልን በአዋጅ ቁጥር 70/90 በተሰጠን ሥልጣን መሠረት ጨረታ በማውጣት ቤቱ ሊሸጥ ይችላል።

ባንኩ ገዥ ካላገኘ የቤቱን መረጃ ለመስተዳድሩ በመመለስ ተገቢውን ገንዘብ ይቀበላል። ይህ ቅደም ተከተላዊ እርምጃ ቢሆንም ተበዳሪዎች በዝቅተኛ እና በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ስለሆኑ፤ የማይከፍሉበት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ስለሆነም ከዘጠና ቀን በኋላ የማገገሚያ ሥርዓት አዘጋጅተን ተበዳሪዎችን በማነጋገር ዕዳቸውን እንዲከፍሉ የማስታመም እና የመታገስ ሥራ ይሠራል። ይህ አሠራር ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣበት አንዱ አካሄድ ነው። አዲስ አበባ ላይ ብድርን ባለመክፈል ጎልቶ የወጣ ሂደት ብዙም አይታይም›› ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተበዳሪው ብድሩን ከተዋዋለበት ቀን ጀምሮ ከፍሎ እስከሚጨርስበት ቀን ድረስ የሚከታተል ባለሙያ ይመደባል። ይህ ባለሙያ ለደንበኛው ብድሩን በተመለከተ ዋና ዋና ሀሳብ የማስጨበጥ ኃላፊነት አለበት።

ይሁን እንጂ በአንድ ጊዜ በሚወጣ ዕጣ ከአሥር ሺህ እስከ ሰላሳ ሺህ ሰዎች ዕድለኛ በሚሆኑበት ጊዜ ለውል አገልግሎት ባንኩ ባዘጋጃቸው አምስት ማዕከላት ከአንድ ወር እስከ አንድ ወር ከአሥራ አምስት ቀናት (እንደ ተዋዋዩ ቁጥር ከፍ ወይም ዝቅ ሊል ይችላል) ውል የማዋዋል ተግባራትን ያከናውናል። ይህም ሆኖ ከደንበኞች ብዛት የተነሳ መጨናነቅ ይኖራል። ይሁን እንጂ በዚህም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ውሉን አንብቦ መረዳት ይቻላል። ከዚያም አልፎ ውል ከተዋዋሉ በኋላም ቢሆን ተበዳሪዎች እንዲብራሩላቸው የሚፈልጓቸው ጉዳዮች ካሉ በማንኛውም ጊዜ ወደ ተመደበላቸው ባለሙያ ቀርበው ሊጠይቁ እንደሚችሉ አቶ መዝገበ ያስረዳሉ።

ከብድር አሰጣጥ እና ወለድ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ሌላው መሠረታዊ ነጥብ ቤቱ ሳይጠናቀቅ ወለድ መታሰቡ ነው። ከዚህ አንፃር ከተበዳሪዎች ለሚነሳው ቅሬታ የባንኩን አሠራር መሠረት በማድረግ አቶ መዝገበ ምላሻቸውን ሲሰጡ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ጋር የተዋዋለው ውል የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ 80% ከተጠናቀቀ ለማስተላለፍ ብቁ ይሆናል በሚል ነው። የእፎይታ ጊዜ ከተሰጡበት ምክንያቶች አንዱ ግንባታው ያልተጠናቀቀ መሆኑን በማየት ነው። ስለዚህ እንደባንክ የቤቱን (የግንባታውን) ወቅታዊ ሁኔታ የማጣራት ዓቅሙ የለም፤ በውሉ ውስጥም የለም። ተበዳሪዎች 20% ከፍለው ከመስተዳድሩ ጋር የሽያጭ ውል ከተዋዋሉ በኋላ በስማቸው ካርታ ሲዘጋጅ፤ ይህ እንደተከናወነ ባንኩ 80% ገንዘቡን ከተበዳሪው ጋር በመዋዋል የወለድ ሥርዓቱን ይጀምራል እንጂ ቤት መገንባት የባንኩ ተቋማዊ ኃላፊነት አይደለም። ይሁን እንጂ ተበዳሪዎች ከግንባታው አለመጠናቀቅ፣ መንገድ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች አለመሟላት በተያያዘ የሚያቀርቧቸውን ቅሬታዎች በተመለከተ ባንኩ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ጋር በሚኖረው ግንኙነት እና የጋራ ስብሰባ እየተነሱ ያሉ ችግሮችን በማሳወቅ መፍትሔ እንዲያገኙ ጥረት ይደረጋል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ብድሩ ግን በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መከፈል አለበት›› ብለዋል። የክፍያ ሂደቱ የሚመራበት “ሲስተም” ለደንበኞች ግልፅ ባልሆነ መንገድ ተገቢ ያልሆነ ክፍያ ለመክፈል የሚገደዱት ለምንድን ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ችግሩ መኖሩን ያመኑት አቶ መዝገበ ለባንኩ ባለሙያዎች እና ለተበዳሪዎች ትምህርት በመስጠት ችግሩን ለመቀነስ ጥረት መደረጉን እና ወደፊትም ተከታታይነት ያላቸው ጥረቶች እንደሚደረጉ አብራርተዋል። አያይዘውም ‹‹ባንኩ እ.ኤ.አ ከ2012 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘመኑ ቴክኖሎጂ የሆነ የኮር ባንኪንግ “ሲስተም” እየተጠቀመ ይገኛል።

ሲስተሙ ሙሉ ለሙሉ አውቶሜትድ በሆነ ሁኔታ የሚሠራ ነው። ለምሳሌ አንድ ተበዳሪ ወር በገባ በአሥረኛው ቀን ክፍያ እንዲፈጽም የተዋዋለ ከሆነ፤ ሲስተሙ የተስተካከለው ሁል ጊዜ ወር በገባ በአሥረኛው ቀን ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ተቀማጭ ሂሳቡ ላይ ገንዘብ ካለ በመውሰድ እንዲከፍል ተደርጎ ነው። ይህ አሠራር ከተበዳሪዎች ጋር ሳያጋጭ ሂሳቡን ለመክፈል ያስችላል። ነገር ግን ችግር የሚከሰተው በአሥር መክፈል የሚገባው በስምንት መጥቶ ሲከፍል ከብድሩ ላይ ይቀነሳል እንጂ ወርሐዊ ክፍያ እንደተከፈለ አይመዘግብም። ስለዚህ በአሥረኛው ቀን ወርሐዊ ክፍያውን ይጠብቃል።

በመሆኑም በአሥር አልተከፈለም ብሎ ለባለሙያው ያመላክተዋል። በዚህ ወቅት ባለሙያው ተበዳሪው በስምንት መክፈሉን ለኮንዶሚኒየም ቤት ቁጠባ ተብሎ የተዘጋጀውን የተቀማጭ ሂሳብ በማየት ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅበታል። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የተጠቀሱት ችግሮች ይስተዋሉ ነበር። ምክንያቱም ባለሙያዎች ለሥራው አዲስ በመሆናቸው ሲስተሙን በሚገባው ልክ ባለመገንዘባቸው ነው። ስለዚህ ባንኩ ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሥልጠናዎች አገልግሎቱን እየሰጡ ለሚገኙ ባለሙያዎች በመስጠት መፍትሔ እየሰጠ ነው። ለወደፊትም ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮች እንዳይከሰቱ ጥረት ይደረጋል። ከባለሙያው የማስረዳት ወይም ከተበዳሪው የመረዳት ችግር ካልሆነ በስተቀር፤ ሲስተሙ የሰው ንክኪ ስለሌለው የባንኩንም ሆነ የተበዳሪውን ሥራ የሚያቀል ነው።

ባንኩ እስከ አሁን የንግድ ቤቶችን ጨምሮ ወደ 170 ሺህ ቤቶችን በብድር አስተላልፏል። አሁንም ወደ 86 ሺህ የሚጠጉ ተበዳሪዎች አሉት። ብዛቱም አንዱ ችግር ነው›› በማለት ገልፀዋል። ከአቶ መዝገበ ገለፃ መረዳት እንደተቻለውም ከሲስተም ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች ካሉ ተበዳሪዎች ከባለሙያ እስከ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም በተዋረድ ቅርንጫፎችን ለሚያስተባብር ኃላፊ ከዚያም አልፎ ለባንኩ ፕሬዚዳንት በማቅረብ ስለሁኔታው መረዳት ወይም ችግራቸውን ማስፈታት እንደሚችሉ ነው።

በውሉ መሠረት ባንኩ ከደንበኛው የሌላ ቅርንጫፍ ሂሳብ በወር መከፈል የሚገባውን ያህል ገንዘብ ብቻ ቀንሶ ይወስዳል። ተበዳሪውም በማንኛውም ጊዜ ስለብድሩ አጠቃላይ እይታ የሚያሳይ እስቴትመንት (የሂሳብ ማስረጃ) መውሰድ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ተገልጋዩ ሌላ ቦታ ሳይሄድ ወርሐዊ ክፍያውን ገቢ ባደረገበት ባንክ ቤት ቀሪ ሂሳቡን ማየት የሚችልበት አሠራር ተግባራዊ ሆኗል። ስለዚህ ደንበኛው ተበዳሪ መሆኑን የሚገልጽ ማስረጃ በማቅረብ ከብድር እና ወለድ ጋር ተያይዞ ማወቅ የሚፈልገውን ሁሉ የማወቅ መብት አለው። የባንኩ ባለሙያዎችም የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸው ለመረዳት ተችሏል።

ብድሩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብቸኝነት እንዲያቀርብ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን የሚያነሱ ምሁራን እና ቅሬታ አቅራቢ ደንበኞች መኖራቸውን ለዳይሬክተሩ ስንጠቁማቸው ‹‹መንግሥት አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የቤት ባለቤት ለማድረግ ግንባታውን ሲገነባ፤ ባንኩ የመንግሥት እንደመሆኑ ሲጠየቅ የመንግሥትን ፍላጎት በፋይናንስ ማገዝ ስላለበት ያግዛል። ከመደበኛ የብድር አገልግሎቱ አንፃር ሲታይ ግን አትራፊ ሆኖ አይደለም። ምክንያቱም ባንኩ በመደበኛ የብድር አገልግሎቱ ለተበዳሪዎች የሚሰጠው በ11.5% ሲሆን፤ ለኮንዶሚኒየም ቤት ተበዳሪዎች በ9.5% ወለድ ለ15 እና 20 ዓመት ቆይታ ነው የሚያበድረው።

ይህ የተራዘመ ብድር ደግሞ ተበዳሪን እንጂ አበዳሪን አይጠቅምም። እስከማውቀው ድረስ የትኛውም የፋይናሻል ተቋም ይህ ብድር ለእኔ ይሰጠኝ ብሎ የጠየቀ የለም። ጠይቆም የተከለከለ ያለ አይመስለኝም። ብድሩን መስጠት እፈልጋለሁ የሚል ካለ ባንኩ ምንም ዓይነት ተቃውሞ የለውም፤ በጣም ደስተኛ ሆኖ ይቀበላል። የኅብረተሰቡን የቤት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ እና ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ለተራዘመ ጊዜ በአነስተኛ የወለድ ምጣኔ ማበደሩ ባንኩ ላይ ጫና አለው›› በማለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብቸኝነት አበዳሪ መሆኑ ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ አለመሆኑን ገልፀዋል።

ባንኩ የተለያዩ ጫናዎችን በማድረግ ተበዳሪዎች የቤት ባለቤትነታቸውን እንዲያጡ ምክንያት እየሆነ ነው ተብሎ የተነሳውን አስተያየትን በተመለከተም፤ በተጨባጭ እውነታ ላይ ያልተመሠረተ ተገቢ ያልሆነ መሆኑን ሲገልፁ፤ ባንኩ ለኮንዶሚኒየም ቤቶች ልማት ፕሮግራም ቅድሚያ በመስጠት በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ብር ብድር በመስጠት ፈሰስ አድርጓል። ተበዳሪዎችም የቤቱን ዕዳ በተባለው መጠን እና ጊዜ ያለማቋረጥ በመክፈል ተመላሽ ሲያደርጉ ገንዘቡን ሌሎች ተበዳሪዎች ለተመሳሳይ ዓላማ እንደሚበደሩበት ማወቅ ይገባቸዋል። ስለዚህ ባንኩ ጫና እየፈጠረ ሳይሆን፤ ዜጎች የቤት ባለቤት ለመሆን የሚያደርጉትን ጥረት እያገዘ መሆኑን በመግለፅ አስተያየታቸውን አጠናቀዋል።

ማጠቃለያ በመጨረሻ የኮንዶሚኒየም የመኖሪያ ቤት ግንባታ ዓላማ፣ ከተጠቃሚዎች የሚነሱ ቅሬታዎች፣ የምሁራን አስተያየት እና የባንክ ኃላፊ ምላሽን ለአንባቢያን ግንዛቤ ሊያስጨብጥ በሚችል መልኩ ለማቅረብ ተሞክሯል። በአጠቃላይ ከተበዳሪዎች ሀሳብ፣ ከምሁራን አስተያየት እና ከባንክ ኃላፊው ምላሽ መረዳት የሚቻለው በብድር አሰጣጡ፣ በወለድ ምጣኔው እና በውል መዋዋል ሂደቶች የሚታዩ ክፍተቶች አሉ።

ይህም የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጄንሲም ሆነ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠራራቸውን በተመለከተ ለተጠቃሚዎች በቅድሚያ ግንዛቤ ባለማስጨበጣቸው የተፈጠረ ነው። ስለዚህ አሠራራቸውን መፈተሽ አለባቸው። መንግሥትም የዜጎችን መሠረታዊ የቤት ፍላጎት ለማሟላት የሚያደርገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን፤ ለተበዳሪዎች የሚቀርበው የብድር አገልግሎት በአንድ ባንክ (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) ብቻ እንዲሆን ከማድረግ፤ ሌሎች ፍላጎት እና ዓቅም ያላቸው የንግድ ባንኮች ሊሳተፉ የሚችሉበት ዕድል ማመቻቸት አለ በት።

ይህ መሆኑ ለተበዳሪው አማራጭ ዕድል ይፈጥራል፤ የኮንዶሚኒየም ቤት ዕድለኞችም የተፈጠረላቸውን ዕድል በመጠቀም የቤቶቻቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህ ካልሆነ ግን በዓቅም ማነስ ወይም ግልፅነት በጎደለው አሠራር በመማረር በማከራየት አሊያም በሽያጭ ከተጠቃሚነት ውጭ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ትርጉም አልባ ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ ይደረግበት እንላላን።

ዘመን መፅሄት መጋቢት 2011

ስሜነህ ደስታ