ወፍጮን ማንቀሳቀስ የሚችል ኃይል የሚያመነጭ ተንቀሳቃሽ ሶላር የኤሌክትሪክ ጀነሬተር

56

በኢትዮጵያ በተለይም በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል ከ10 ሰው ሰባቱ ወይም 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አለመሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ:: ለመሠረታዊ ፍጆታም ይሁን ለምጣኔ ሀብት ዕድገት ወሳኝ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመላው ኅብረተሰብ ለማዳረስ በርካታ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች እና ሌሎችም የኃይል አማራጮች በመስራት ከአገር አልፈው እንደ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ሩዋንዳ እና ሌሎችም ጎረቤት የአፍሪካ አገራት ጭምር ለማዳረስ ቢታቀድም የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትም ሆነ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንኳንስ የገጠሩን የአገሪቱ ክፍልና የጎረቤት አገራትን ተጠቃሚ ማድረግ ቀርቶ የከተማውንም ኅብረተሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በተገቢው መንገድ ማዳረስ ስለተሳናቸው ኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ ቅሬታውን እየገለጸ ይገኛል::

የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ መቋረጥ፤ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በፈረቃ በአገሪቱ መጀመር እንዲሁም በአንዳንድ ከተሞች ለዓመታት ያለ ኃይል አቅርቦት የኤሌክትሪክ መስመሮች በየመንገዱ ተዘርግተው የሚታዩበት ሁኔታ ተቋማቱን በመልካም አስተዳደር እጦት ሲያስወቅሱት መቆየታቸውን የመስኩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ከሰባት ዓመታት በፊት አቶ ኃይለልዑል ይትባረክ ኢትዮጵያ ከፈጣሪ የተሰጣትን የአስራሦስት ወር የፀሐይ ብርሃንን ጸጋ በመጠቀም በፀሐይ ብርሃን የሚሰራ ተንቀሳቃሽ የኤሌክትሪክ ጄኔሬተር (Portable solar electric generator) በመስራት የማህበረሰቡን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ፤ ለማህበረሰቡ በሚፈልገው መጠንና በየትኛውም ቦታ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማዳረስ በማሰብ የፈጠራ ሥራቸውን ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሰባተኛው አገር አቀፍ የፈጠራ ውድድር በአካሄደበት ወቅት ማስተዋወቃቸው ይታወሳል።

አሁን ላይ ይህ የፈጠራ ሥራቸው በምን ደረጃ እንደሚገኝ ከፈጠራ ባለቤቱ ከአቶ ኃይለልዑል ጋር እንደሚከተለው ቆይታ አድርገናል። የፈጠራ ባለቤቱ በኤሌክትሪክ ኤሌክትሮኒክስ በደረጃ አራት ከወሊሶ የእርሻ ተቋም ተመርቀዋል። በቴክኒክና ሙያ ትምህርታቸው ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት ተመርጠው በኢትዮቴሌኮም በመሠረታዊ ቴክኒሻንነት ለሁለት ዓመታት ሥልጠና ወስደዋል።

ይሄንን ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ በኢትዮቴሌኮም ለስምንት ዓመት ያክል በተለያዩ ጣቢያዎች ላይ የማዞሪያ ቴክኒሻን ሆነው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በመዘዋወር አገልግለዋል። በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚሰጥ የሶላር ቴክኖሎጂ ኤክስፐርት ሥልጠና በመውሰድ በሶላር ቴክኖሎጂ ላይ ዕውቀት ማግኘታቸውን የጠቆሙት የፈጠራ ባለቤቱ፤ በኢትዮቴሌኮም ተቀጥረው በሚሰሩበት ወቅት በገጠር አካባቢ የተለያዩ የስልክ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት በሚሰራበት ወቅት የገጠር ከተሞች በመሆናቸው የስልክ ማሽኖችን የሚያንቀሳቅሱት ከሶላር ኃይል በሚገኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንደነበር ይናገራሉ።

ይህ ለአሁን የፈጠራ ሥራቸው አስተዋፅኦ ያበረከተ መሆኑንም ይናገራሉ። «በኢትዮቴሌኮም ተቀጥረው እየሰሩ በነበረበት ወቅት የሶላር ቴክኖሎጂው ለኅብረተሰቡ ያንያክል ጥቅም ይሰጣል የሚል ግንዛቤው አልነበረኝም» የሚሉት አቶ ኃይለልዑል፤ ሥራቸውን ለቀው ወደግሉ ዘርፍ ሲሰማሩ መንግሥት ከአካባቢ ብክለትና አየርንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ለታዳሽ ኃይል ትኩረት በመስጠቱ፤ እርሳቸውም ከነበራቸው ልምድ ተነስተው የሶላር ቴክኖሎጂው በተለያየ ነገር ተሻሽሎና ዘመናዊ ሆኖ ለኅብረተሰቡ ቢቀርብ ብዙ የማህበረሰቡን ችግር ያቃልላል በሚል እምነት ወደ ሥራው ሊገቡ እንደቻሉ ተናግረዋል።

በአገሪቱ ባለው የኃይል መቆራረጥ ችግር ቴክኖሎ ጂው በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል ብቻ ሳይሆን በከተሞችም የሚያስፈልግ መሆኑን በመገንዘብ በኤሌክትሪክ ኃይልና በፀሐይ ብርሃን ኃይል መሰብሰብ የሚችል የኃይል ማጠራቀሚያ ቋት መስራት ችለዋል። በመሆኑም የሶላር ቴክኖሎጂውን ሙሉ ግብዓቶቹን ይዞ ከቦታ ቦታ በቀላሉ ለማን ቀሳቀስ የሚቻል አድርገው፤ ኅብረተሰቡ በፈለገው የኃይል መጠን ዲዛይን አድርገው ማቅረብ በሚያስ ችል ደረጃ መስራታቸው እና በፀሐይ ብርሃንና በኤሌ ክትሪክ ኃይል መሰብሰብ የሚያስችል አድርገው በመስራታቸው ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የፈጠራ ባለቤትነት መብት እንዳገኙ ይናገራሉ።

ሶላር ቴክኖሎጂ ሙያዊ የሆነ ዲዛይን የሚፈልግ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ባለው የኤሌክትሮኒክስ ዕቃና በሚፈልገው የኃይል አቅርቦት ልክ ለማህበረሰቡ ለማድረስ የሚያስችል የፈጠራ ሥራ በመስራታቸው፤ የማህበረሰቡን ፍላጎት እንደ መነሻ ሃሳብ በመውሰድ የዲዛይን ፕሮግራም (ሶፍትዌሮችን) እና በሙያዊ የሂሳብ ቀመር በመታገዝ ተንቀሳቃሽ ሶላር ኤሌክትሪክ ጀነሬተር ሰርተው ባቋቋሙት ሥራ ሶላር ኢነርጂ ኢንተርፕራይዝ አማካኝነት ለማህበረሰቡ ተደራሽ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ሶላር ጀነሬተሩን ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ በሚገኙ ጥሬ ዕቃ መስራት እንደሚቻል የጠቆሙት አቶ ኃይለልዑል፤ በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃው ውድ በመሆኑ የፈጠራ ሥራውን ለመስራት 30 በመቶ የሚሆነውን ጥሬ ዕቃ ከውጭ እንደሚያስገቡ ተናግረዋል። 70 በመቶ የሚሆነውን የፈጠራ ሥራውን ለመስራት ግብአት የሚሆኑ ጥሬ ዕቃ በአገር ውስጥ የሚሸፈን ሲሆን፤ ከብረታ ብረት የሚሰሩ ናቸው ብለዋል።

 በአጠቃላይ የኤሌክትሪክ ገመድ፣ ማቆሚያ ብረት፣ ጎማ፣ ሪሌ (change over switch) በአገር ውስጥ የሚሰራ ሲሆን፤ ሶላር ፓናልና ባትሪውን ከውጭ በማስገባት የፈጠራ ሥራውን እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በ2007 ዓ.ም መጨረሻ የፈጠራ ሥራውን ሃሳብ እንዳመነጩት የሚናገሩት አቶ ኃይለልዑል፤ በሙከራ ደረጃ በቅድሚያ ለጸጉር ቤቶችና የመኖሪያ ቤት አምፖሎችን መሸከም የሚችል ከ500 እስከ 1ሺ 200 ዋት ማመንጨት የሚችል ሶላር ጀነሬተር ሰርተው ነበር። ይሄም አራት ቶንዶስ፣ አራት አምፖል፣ 21 ኢንች ቴሌቪዥን ከነዲኮደሩ እና ቀለል ያሉ የቤት ውስጥ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ለስምንት ሰዓት ማስጠቀም የሚችል ነበር ብለዋል።

 የፈጠራ ሥራውን በመካከለኛ ደረጃ የኃይል አቅርቦት ከፍ ማድረግ የቻሉ ሲሆን፤ ከ1ሺ500 እስከ 3ሺ ዋት የሚደርስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል በማድረግ የፈጠራ ሥራውን አሻሽለው በመስራት በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ የማህበረሰብ ክፍል እንዲውል ዲዛይን አድርገው መስራታቸውን የፈጠራ ባለቤቱ ተናግረዋል። ይሄም ከፍ ያለ ኢንች ያለው ቴሌቪዥን ከነዲኮደሩ፣ ማቀዝቀዣ ማሽን፣ ከስምንት እስከ 10 የሚሆኑ አምፖሎችን፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ የውሃ ማጣሪያ ማሽን፣ ኃይል ቆጣቢ ስቶቭ (የኤሌክትሪክ ምድጃ) እና ምጣድ ማስጠቀም የሚያስችል እንደሆነ አቶ ኃይለልዑል አጫውተውናል። አሁን ላይ የፈጠራ ሥራውን ከ3ሺ 500 እስከ 5ሺ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል አድርገው መስራታቸውን የገለጹት የፈጠራ ባለቤቱ፤ ለጤና ጣቢያ፣ ለትምህርት ቤቶች፣ ለትንንሽ መንደሮች እና አነስተኛ ወፍጮዎችን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ደረጃ ላይ መድረሱን ተናገረዋል።

አሁን ላይ ቴክኖሎጂው የደረሰበትን ደረጃ ለማህበረሰቡ በሚፈለገው መጠን ተደራሽ ለማድረግ አቅሙ ባይኖራቸውም በተቻላቸው መጠን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤን ዲፒ) ጋር በመተባበር ቴክኖሎጂው አሁን ላይ የደረሰበትን የኃይል አቅርቦት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን በገንዘብም በሥልጠናም ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል። እንደ አካባቢው እርቀት፣ እንደሚጠቀሙት ሰዓትና እንደሚጠቀሙት ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ዓይነት በአማካኝ ከ500 እስከ 1ሺ 200 ዋት ኃይል ያላቸውን ሶላር ጄኔሬተሮች ከ16ሺ እስከ 20ሺ ብር እንደሚሸጡ ገልጸው፤ በመካከለኛ ደረጃ ያሉትን ሶላር ጄኔሬተሮችን ከ38ሺ እስከ 46ሺ ብር እንደሚሸጡ ተናግረዋል።

እንዲሁም ከ3ሺ 500 እስከ 5ሺ ዋት ማመንጨት የሚችሉትንና ሀመር የሚል ወፍጮዎችን የማንቀሳቀስ ጉልበት ያላቸውን ሶላር ጀነሬተሮችን ከ160ሺ እስከ 180ሺ በአማካኝ ለማህበረሰቡ የማዳረስ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል። እንደ አቶ ኃይለልዑል ማብራሪያ ሶላር ጀነሬተሮቹ ቢበላሹ ከሙሉ መለዋወጫ ጋር ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ድረስ ዋስትና ይሰጣቸዋል። እንዲሁም የተለያዩ የቴክኒክ ችግሮች ቢገጥሙ በራሳቸው ማስተካከል እንዲችሉ ስለቴክኖሎጂው መሠረታዊ ስልጠና ይሰጣሉ።

በተለይ ከፍተኛ ዋት ለሚያመነጩ ሶላር ጀነሬተሮችን ለሚገዙ ድርጅቶች ለራሳቸውም ሆነ ለባለሙያዎቻቸው ሙያዊ ሥልጠና ይሰጣሉ። ከሥልጠናው ባሻገር ከተጠቃሚው አቅም በላይ የሆነ ችግር ከገጠማቸው በስልክ ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጠቁመው፤ የዋስትና ሰዓቱ ከአለፈ በኋላም በተመጣጣኝ ዋጋ የጥገና አገልግሎት እንደሚሰጡና የመለዋወጫ ዕቃዎችን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። በአጠቃላይ ቴክኖሎ ጂው የተወሳሰበ ያልሆነና ለመጠቀም ቀላል በመሆኑ መሠረታዊ ጥንቃቄ ማድረግ ከተቻለ ለረዥም ጊዜ ያለምንም ብልሽትና ወጪ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሲሆን፤ የቅድመ ብልሽት ጥገና ሥልጠና ለተጠቃሚው አካል በሚገባ ስለሚሰጥ ያንያክል ችግር አይገጥምም ብለዋል።

 እንደ ፈጠራ ባለቤቱ ገለጻ፤ አንድ ሜትር በአንድ ሜትር በሆነች ቦታ ላይ በፀሐይ ብርሃን እስከ 1ሺ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል ተፈጥሯዊ ሀብት ያለ መሆኑን በመጠቆም፤ ቴክኖሎጂው አሁን ላይ በአገራችን ያለውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመፍታት ያላሰለሰ ሚና ይጫወታል ብለዋል። ከታዳሽ ኃይል ጋር የተገናኙ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፣ 20 ሚሊዮን የሚደርሱት የኅብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኙ ናቸው። ስለዚህ እነዚህን የማህበረሰብ ክፍል የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ የኤሌክ ትሪክ ኃይል ፍጆታ ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅና አሰፋፈራቸው የተበታተነ በመሆኑ ስለሚያስቸግር ይሄንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በቀላሉ የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

እንዲሁም ማንኛውንም የኤሌክትሮኒክስ የቤት ውስጥ ዕቃ እና በየትኛውም ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ላለ ሰው ከትንሽ ጸጉር ቤት ጀምሮ መለስተኛ ቤቶችን፣ መንደሮችን እስከ ወፍጮ ቤት ድረስ የኃይል ፍጆታ የሚውል የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰጥ በመሆኑ ለማህበረሰቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚሰጥ ነው ብለዋል። አክለው፤ በከተማም አካባቢ የኃይል መቆራረጥ በሚኖርበት ወቅት ተክቶ በመግባት ሥራ እንዳይስተጓጎል የሚያደርግ ነው ብለዋል። በተለይ ጥራጥሬ አብቃይ በሆኑና ቆላማ አካባቢዎች ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ሀመር ሚል ወፍጮዎችን በመጠቀም በቀላሉ ማህበረሰቡ እህል ለመፍጨት ያስችለዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ይከሰታል ተብሎ ሳይጨናነቁና ምንም የነዳጅ ፍጆታ ሳያስፈልግ የፀሐይ ብርሃንን በመጠቀም ትርፋማ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ነው። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ በቃሊቲ ቴርሞ ሳይት ኢንዱስትሪ መንደር መንግሥት በሰጣቸው 120 ካሬ ሜትር የመስሪያ ቦታ የፈጠራ ሥራውን እየሰሩ እንደሆነ የጠቆሙት የፈጠራ ባለቤቱ፤ የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር ለስምንት ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።

አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2011

ሶሎሞን በየነ