«ሚነል አይዲ»!

9

 ፍቅር፣ ጽናት፣ አንድነት፣ ሰላም፣ መተባበርና መተጋገዝ ጎልቶ የታየበት ታላቁ የረመዳን ጾም በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ አንድነትንና ሰላምን አጽንቶ እነሆ ለኢድ አልፈጥር ተደረሰ! ለመላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እንኳን ለ1440ኛው ለኢድ አልፈጥር በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን። ሚነል አይዲ!

ረመዳን በሙስሊሞች ትልቅ ክብር ከሚሰጣቸው የዕምነት ጉዳዮች ቀዳሚው ነው። በዚህ ታላቅ የጾም ወር ህዝበ ሙስሊሙ ከምግብና ከመጠጥ ታቅቦ በመጾም ከሚያከናውነው ሃይማኖታዊ ተግባር በተጓዳኝ እርስ በእርስ በመጠያየቅ፣ ጥላቻን በማራቅና የተቸገረን በማገዝ ለዘመናት መሻገር የሚገባቸውንና ፋይዳቸው እጅግ የጎላ ታላላቅ እሴቶችን በጽናት ይፈጽማል። ይህም ለአገር ሰላምና ለህዝቦች አብሮ መኖር እንደ መሰረት ድንጋይ የሚቆጠር ነውና ከኢድም በኋላ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው።

የዘንድሮው የረመዳን ወቅት በሀገራችን ታላላቅ ተግባራት የተፈጸሙበት ነው። ከእነዚህም አንዱና ዋነኛው በመጅሊሱ መካከል ተፈጥሮና አቃቅሮ የቆየው ልዩነት ተወግዶ ሰላም መስፈኑ ነው። ለዚህም ትልቅ ድል ታላላቅ የእምነቱ አባቶችና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዓብይ አህመድ የተጫወቱት የላቀ ሚና ምስጋና ሊቸረው የሚገባ ጉዳይ ነው። በመጅሊሱ መካከል ሰላም መውረዱ ህዝበ ሙስሊሙ በአንድ ልብ እንዲያመልክ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ከዚህም በላቀ ህዝበ ሙስሊሙ በአንድ ልብ ለአገር ልማትና ብልጽግና እንዲተጋ መልካም ዕድል ይሆናል።

በዚህ ታላቅ ወር ከተፈጸሙ ታላቅ ተግባሮች ሌላው ሙስሊሙ ከሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ያለውን ህብረት የሚያጠናክሩ ተምሳሌታዊ ሥራዎች መሰራታቸው ነው። ለማሳያም ያህል የክርስትና እምነት ተከታዮች ለሙስሊም ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የአፍጥር ፕሮግራም በማካሄድ የእምነት ልዩነት የፍቅር እንጂ የጥላቻና ጸብ ምንጭ አለመሆኑን ማሳየታቸው ይጠቀሳል። በሚሊኒየም አዳራሽ የተካሄደውና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገኙበት የአፍጥር ፕሮግራምም እጅግ ጠቃሚ መልዕክቶች የተላለፉበትና ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውን አገር መሆኗን በተግባር የተረጋገጠበት ነው።

መላው የሙስሊም ኅብረተሰብ በሸገር ፕሮጀክት፣ በችግኝ ተከላና በአካባቢ ጽዳት እንዲሳተፍ ጥሪ መቅረቡና ይህንንም ተከትሎ ተግባራዊ ምላሽ መሰጠቱም ከዘንድሮው ረመዳን የተቋደስነው ሌላ በረከት ነው። የጽዳቱን ጉዳይ ለየት የሚያደርገው ደግሞ በአዲስ አበባ፣ ደሴ፣ ጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎችም ክርስቲያን ወገኖች ሙስሊም ወገኖቻቸው በዓላቸውን የሚያከብሩበትን ቦታ በማጽዳት አንድነትንና ፍቅርን የሚያጸና አኩሪ ተግባር መፈጸማቸው ነው። ለዚህም ነው የዘንድሮው ረመዳን ላቅ ያሉና ፋይዳቸው የጎላ ታላላቅ ተግባራት የተከወኑበት ታሪካዊ ወር ነው ያልነው።

ከታላቅ የእምነት ጽናት በኋላ በሚከበረው በዚህ ኢድ አልፈጥር ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ለአገር ዕድገትና ሰላም ብሎም ብልጽግና ከዚህ ቀደም ሲያበረክተው የቆየውን ቅዱስ ተግባር አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል የሚገባበት ሊሆን ይገባል። ከዚህም በላቀ ሀገራዊ ጥሪ በቀረበባቸው እንደ ሸገር ፕሮጀክት፣ የአካባቢ ጽዳትና አራት ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ፕሮግራሞች ላይ በንቃት በመሳተፍ ለአገሩ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ያስፈልጋል።

በብዙ ኢትዮጵያውን የህይወትና የአካል መስዋዕትነት በአገራችን የመጣው ለውጥ ፍሬ እንዲያፈራና ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ከሙስሊሙ ህብረተሰብ የሚጠበቀው ብዙ ነው። ለማንም ግልጽ እንደሆነው በእስልምና እምነት ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ልዩነት ለመፍታት ለውጡና የለውጡ አመራር ያበረከተው አስተዋጽኦ ትልቅ ነው። ስለሆነም ለዚህ ድልና ሰላም ያበቃውን ለውጥ እንደ ዓይን ብሌን መንከባከብ ከመላ ሙስሊሞች የሚጠበቅ ታላቅ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።

የለውጡን ሂደት በማደናቀፍ የተጀማመሩ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ለማደናቀፍ የሚሰሩ ሃይሎች ለጥፋት ዓላማቸው ከሚጠቀሙበት መንገድ አንዱ በክርስትናና እስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ግጭት መፍጠር ነው። ስለሆነም ይህንን የጥፋት ዕቅድ ተገንዝቦ ለማክሸፍ መላው የሙስሊም ኅብረተሰብ በአንድነት ሊቆም ይገባዋል። ከሰሞኑ የታዩ የክርስቲያንና ሙስሊም ህዝቦችን ተምሳሌታዊ ክንውን የሰርክ ተግባር ማድረጉ ደግሞ የጥፋት ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ ፍቱን መድሃኒት መሆኑ አያጠራጥርም።

ከእስልምና አስተምህሮዎች አንዱ በሆነውና ትልቅ ቦታ በሚሰጠው የእርስ በእርስ መረዳዳትም ያለው ለተቸገረ ወገኑ በማገዝ በዓሉን ማክበሩ ትልቅ የአዕምሮ እርካታን የሚያጎናጽፍ ነው። ይህ ተግባር ምዕመኑ በረመዳን ጾምና ሁልጊዜም ሲያደርገው የቆየ እንደመሆኑ በበዓሉም አጠናክሮ እንደሚተገብረው ይታመናል።

የዘንድሮው ዒድ የሚከበረው አገራችን በለውጥ ጅማሮ ባለችበትና በሙስሊሞች መካከል ከመቼውም ጊዜ የላቀ አንድነት በተፈጠረበት ነው። ስለሆነም በዓሉን በደስታና በፍቅር ከማክበሩ ጎን ለጎን ለለውጡ ዘብ መሆንና በእምነቱ ውስጥ የተፈጠረውን አንድነት ማጠናከር ከምዕመናኑ የሚጠበቅ ታላቅ ሃላፊነት መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ሊሆን ይገባል። መላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታይም ይህንን የተቀደሰ ተግባር በመፈጸም በፍቅርና በሰላም የጀመረውን ጾም በደስታና በፍቅር እንደሚደመድመው እምነታችን ጽኑ ነው። መልካም ኢድ አልፈጥር ! ሚነል አይዲ!

አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2011