ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ በሁሉም አቅጣጫ መተባበር ያስፈልጋል

35

ከነገ ሰኔ 3 ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ የ10ኛ እና የ 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና፣ ለስምንተኛ ክፍሎች ደግሞ ክልላዊ ፈተና በየፕሮግራማቸው መሰረት ይሰጣል። የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የሚሰጠው በሁለት ሺ 866 የፈተና ጣቢያዎች ሲሆን 82 ሺ 785 መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ለዚሁ ሥራ ተሰማርተዋል።

ለብሄራዊ ፈተናው የሚቀመጡት አንድ ሚሊዮን 277 ሺ 552 የ10ኛ እና 322 ሺ 729 ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው። ይሄ ብሄራዊ ፈተና የተማሪዎቹን መጻኢ ዕድል የሚወስን በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው። ተማሪዎች ለዚህ ደረጃ የደረሱት በርካታ መሰናክሎችን አልፈው፣ ሀብትና ጉልበትም ፈሶባቸው ነው። አብዛኛዎቹ ተማሪዎችም እንቅልፋቸውን ቀንሰው፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሰርተውና ለፍተዋል ተብሎ ይታመናል። ይህ ፈተና የልፋታቸውን ውጤት የሚያዩትበ የነገውን የህይወት መስመራቸውን አቅጣጫ የሚወስኑበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

የዛሬ ተፈታኞች ነገ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሸጋግረው በተለያዩ ዘርፎችና ሙያዎች ተሰማርተው ህብረተሰቡን የሚያገለግሉ ሀገርን የሚረከቡ ዜጎች ናቸው። እነዚህ ዜጎች በአንድም በሌላም መንገድ የእያንዳንዳችን ልጆች፤ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው። ዛሬ በሰላም እጦት በኑሮ ውድነት በአጠቃላይ በድህነትና በኋላቀርነት የምትማቅቀውን ሀገር ወደፊት አንድ እርምጃ የሚያራምዱት ለነገዋ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ፈንጣቂዎችም ናቸው።

ይሄ ብቻ አይደለም። ሳይማር ያስተማረውን፤ ቢማርም ሳይደላው ጭምር መስዋዕትነት ከፍሎ ያስተማረ ወላጅና ቤተሰብ ከእነዚህ ልጆች የሚጠብቀው ብዙ ነገር አለ። ነገ ልጆቼ አድገው ለቁም ነገር ደርሰው ኑሮዬን ይቀይሩልኛል፤ ያሻሽሉኛል፤ ለአገር ይበጃሉ የሚለው ተስፋም የሁሉም ወላጅና አሳዳጊ ምኞት ነው። እንደ ኢትዮጵያውያን ወላጅ ከባለፉት ልጆችና ወላጆች ያየውና የለመደውም ይሄንኑ በመሆኑ በዛሬዎቹ ልጆቹ ተስፋውን ጥሎ እየተጠባበቀ ይገኛል። ይሄ ተስፋ እውን የሚሆነው ደግሞ ተፈታኝ ተማሪዎች በሰላም በተረጋጋ መንፈስ ፈተናቸውን መፈተን ሲችሉም ጭምር ነው። በመሆኑም ሁሉም አካል ለፈተናው በስኬት መጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ያድርግ።

ከነገ ጀምሮ በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ ለፈተና የሚቀመጡ ተፈታኞች በሰላም በተረጋጋ መንፈስ እንዲፈተኑ ለማድረግ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት በዋነኛነት ቤተሰብ ነው። ቤተሰብ የልጆቹ ስነልቦና የተረጋጋ ሆኖ በሰላም ፈተናቸውን እንዲያጠናቅቁ በሰዎችም ሆነ በማህበራዊ ድረገጾች ከሚናፈሱ ሀሰተኛ ወሬዎች ራሳቸውን ቆጥበው ተማሪዎቹ ፈተናቸውን እንዲያጠናቅቁ መምከር ይገባል።

ሌላው ትልቁ ሃላፊነት ያለበት ደግሞ የትምህርት ማህበረሰቡ ነው። የትምህርት ማህበረሰቡ ፈታኙ መምህር፣ ተቆጣጣሪው አካል እንዲሁም ከበር ጥበቃ ጀምሮ ያለው ማህበረሰብ ፈተናው በሰላማዊ መንገድ ያለምንም የተፈታኞች መደናገር እንዲጠናቀቅ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። በፈተና ጣቢያዎቹ ረብሻም ሆነ ሌሎች ነገሮች እንዳይፈጠሩ ነቅቶ መከታተል ያስፈልጋል። መጪዎቹ የፈተና ሳምንታት የአገር ትልቁ የቤት ስራ መሆኑን በመገንዘብ ለዚያ የሚመጥን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የግድ ይላል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ትልቅ ማህበራዊ ሃላፊነት ያለበት የጸጥታ ሃ ይሉ በመላ ሀገሪቱ ሰላሙ አስተማማኝ እንዲሆን በተማሪዎችም ሆነ በሌላው ማህበረሰብ ደረጃ ምንም አይነት ኮሽታ እንዳይፈጠር የተጠናከረ ስራ መስራት ይገባዋል። የጸጥታ ኃይሉ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የየክልሉ የሥራ ሃላፊዎችጋር በመሆን ፈተናውን ከማተሚያ ቤት በሃላፊነት ተረክቦና አጅቦ እስከ ፈተና ጣቢያው ድረስ ለማድረስ የከፈለው መስዋዕትነት የሚያስመሰግነው ነው። አሁንም ፈተናው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ስራውን በተገቢው መልኩ መወጣት ይጠበቅበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን ብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጽህፍትን (ወመዘክር) በጎበኙበት ወቅት ተፈታኞች አስበውና ተረጋግተው ፈተናቸውን እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል። ይህ እንደ አገርም የመጀመሪያ የሚያስብል መቀጠልም ያለበት ክስተት ነው። ተማሪዎችም የአገሪቷ መሪ የሰጡትን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው። ኩረጃን ተጠይፈው በራሳቸው ሰርተው ራሳቸውን መሆን አለባቸው። ከሰው ተሰርቶ ከሚመጣ ትልቅ ውጤት በራስ ጥረት

 ተሰርቶ የሚገኝ ትንሽ ውጤት ይበልጥ ያኮራልና በዚህ አግባብ መስራት ይገባቸዋል።

አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2011