ለመኖርም ለማኖርም!

20

ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ክረምት በመጣ ቁጥር በደሴ ሐረጎ ተራራ ላይ የተከልናቸው ዛፎች ዛሬ ደን ሆነው በዕድሜ ከእኛ ጎልምሰውና የተለያዩ አራዊት በውስጣቸው አስጠልለው ስመለከት እኮራለሁ፤ ልቤ በሀሴት ይሞላል። በሀረር ሀኪም ጋራ፤ በጅማ አወይቱ አካባቢ የተከልኳቸውን ዛፎች አስታውሳለሁ።

አዲስ አበባ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ስኖር በየተከራየኋቸው ቤቶች፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከአትክልተኞችና ከደብሩ አለቆች ጋር እየተጣላሁና እየተጋፋሁ የተከልኳቸው ከ60 በላይ ዛፎች ዛሬ መጥታችሁ ብታዩልኝ በእጅጉ የሚያጓጉ ናቸው።

በበኩሌ ይህንን የዘረዘርኩትን የመንግስት ቤት ኪራይ እንኳን እንዲፈቀድልኝ ወይም አድናቆትን አትርፌ ለሽልማት እንድበቃ ፈልጌ በአቤቱታ መልክ ለመጠቆም አይደለም።

እንደዛሬው በነጻ ስለማይሰጥ በዛን ጊዜ አንዱን ችግኝ ከ25 ብር በሆነ ዋጋ በላይ ነበር የምንገዛው፤ በጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከልኳቸውን ችግኞች እንዴት እንደገዛኋቸው፤ በፒካፕ መኪና ከችግኝ ጣቢያው እስከጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ድረስ እንዴት እንዳጓጓዝኳቸው የምናውቀው እኔ እና እግዚአብሔር ብቻ ነን።

ሌሎች ድርጅቶችና ተቋማት የአትክልት ባለሙያ መስያቸው እንድተክልላቸው ይጠይቁኛል። ለምሳሌ፤ የማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች… ለመትከል ሄጄ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ቦታ ባየውም የመትከያ ቦታዎች ስለሌሉት ተውኩት።

ሌሎችም ይጠይቁኛል። እረ እኔ ሰዎች እንደሚጠሩኝ ጋዜጠኛ፤ ደራሲና ተርጓሚ ሳልሆን አልቀርም ስላቸውና ስሜን ስነግራቸው ለጊዜው ደንገጥ ቢሉም ሳቅ ብለውና አድንቀው መልካሙን ሁሉ በመመኘት ነበር የሚሸኙኝ፤ ሰሞኑን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አንድ የተደሰትኩበት ጉዳይ አጋጥሞኛልና የምታውቁትን ልንገራችሁ። ሌላ አይደለም፤ በቀደም ዶ/ር አብይ አህመድ የተናገሩት ነው።

እኔ እንደምስራች ነው የማየው፤ ይህም የሚተከሉት የችግኝ ብዛቶች ብቻ ሳይሆን ችግኞቹ በአጋጣሚ ባይበቅሉ እንኳን የምንቆፍረው ጉድጓድ ውሃ የማቆሩን ነገር አርቀው በማሰብ መናገራቸው ነው። ልብ በሉልኝ በሀገራችን ሌቦች የኢትዮጰያን ህዝብ ገንዘብ ዘርፈው ለራሳቸው፤ ለቤተሰባቸው መጠቀማቸው ያልደከሙበትና ላባቸውን ያላፈሰሱበትን ገንዘብ የተጠቀሙ ስለሆነ ያልተከሉትን ዛፍ ከሚቆርጡት ሰዎች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው።

ያልተከለውንና ተንከባክቦ ያላሳደገውን ዛፍ ከአረመኔ አስቆራጭ ጋር በመመሳጠርና የቀበሌዎችን ፈቃድ ድጋፍ በማድረግ በፈለገበት ጊዜና ሰዓት መጥቶ ይጨፈጭፈዋል። ዛፎቹ ለማን አቤት ይላሉ? ለአያሌ ዓመታት ይህ ቀጥሏል። ከዚህ በኋላ ግን ሁሉም ነገር ሥርዓት ይይዛል የሚል ተስፋ አለኝ።

መትከሉን ማንም ይተክለዋል። ተንከባክቦ ከማሳደጉ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጥና አደራ ሊባል የሚገባው መቁረጡንና መጨፍጨፉን ነው። ኢትዮጵያውያን ከተባበርንና ለአንድ ዓላማ ከተነሳን በለም አፈራችንና በተስማሚ የአየር ንብረታችን እየታገዝን ልንሰራው የማንችለውና ልናለማው የሚያቅተን ነገር የለም።

ዛሬ የምንትክላቸው ዛፎች፤ እኛ በአያቶቻችን እና በቅድመ አያቶቻችን ተክሎች (ዛፎች) ተጠቅመን እንደኖርን ሁሉ እኛም ለልጆቻችን እና ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፉ በመሆናቸው በደን የተሞላ ሀገር ለማስረከብ ጥረታችንን ከዛሬው መጀመር አለብን።

እስኪ ጥቂት ጥቂት መስዋእትነትን እንክፈል! ባለሙያ ባልሆንም የዛፍ ጥቅም ዘርፈ ብዙ መሆኑን አውቃለሁ። ይህን መተንተኑ አስፈላጊ አይመስለኝም። የሚጠበቅብን ጥሪውን ሰምተን ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ነው።

የዛፍን ጥቅም ባብዛኛው የሚያውቀው በረሃ ውስጥ የኖረ እና በረሃ ላይ የሚኖር ሰው ነው። አንድ ገጠመኝ ላጫውታችሁ። ከሀገራችን የበረሀ ከተሞች አንዱ ወደነበረውና በዚያን ጊዜ ባለስልጣኖች የጠሏቸውን ሰዎች ለሁለት ዓመት ግዳጅ ወደሚልኩባቸው ቦታ የመላክ እድል አግኝቼ እንደተመደብኩኝ ከተማውን ጠልቼው ነበር። የተመደብኩበት በስፖርት ተጠሪነት ስለነበር ከተማውን እኔም ወድጄው ሌሎች ነዋሪዎችም እንዲወዱት የማድረግ ተግባር አከናውን ነበር።

ብዛት ካላቸው ስፖርቶች በተጨማሪ የከተማ ውስጥ የሞተር ብስክሌት ውድድር አካሂድ ነበር። እግር ኳስ፤ መረብ ኳስ፤ ቅርጫት ኳስ፤ ቦክስ፤ ብስክሌቱ በድምቀት ስለሚካሄድ የከተማው ነዋሪ በነቂስ እየወጣ የቻሉት ተሳታፊ፤ ያልቻሉት ደግሞ ደጋፊ እየሆኑ የረፍት ጊዜያቸውን በመልካም ጊዜ ማሳለፊያ ቦታ ያሳልፉ ነበር። ወደትግራይና ወሎ በመሄድ፤ እንዲሁም ወደ አዲስ አበባ በመምጣትም በእግር ኳስ በቦክስና በብስክሌት ሻምፒዮን ለመሆን ቻልን። አሰብ የነበራችሁ በረኸኞች ታስታውሱታላችሁ። ጅማ፤ ኢሉ አባቦራ፤ ባሌ፤ ሀረርጌ፤ የነበራችሁም…

ይህን ሁሉ ያነሳሁላችሁ የምወዳትን ሀገሬን ሰራሁላት ባልል እንኳን እንደሚታወቀው የበረኻነት መስፋፋት ምን ያህል እንደሚጎዳ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ፈልጌ ነው። እንዲህ ሆነላችሁ። ከዕለታት በአንዱ የሙቀት ቀን መብራት ከመጥፋቱ የተነሳ ችግር ተፈጠረ ቬንት ሌተሮች፤ ኤይር ኮንዲሽነሮች ምድጃዎችና ፍሪጆች ብቻ አልነበሩም የጠፉት። በአጋጣሚው አየር መንቀሳቀሱን አቆመ ብቻ ሳይሆን ሀይለኛው ወበቅ የኦክስጅን እጥረትና የመተንፈስ ችግር አስከተለ።

የአሰብ ማዘጋጃ ቤት፤ ጤና ጣቢያው፤ ሆስፒታሉ፤ ነዳጅ ማጣሪያውና የወደብና የባህር ትራንዚት መስሪያ ቤቶች በየአቅጣጫው ህዝቡ ከቤቱ ወጥቶ በመንቀሳቀስ ለየራሱ ነፋስ እንዲፈጥር በድምጽ ማጉያ መፍትሔ ነው ያሉትን ይናገሩ ጀመር። በዛን ዕለት የህጻናትን ዋይታ መስማት በእጅጉ ይዘገንን ነበር። እናቶችና ወላጆች ለጊዜውም ቢሆን ያላቸውን በረዶ ሣፋ ላይ አድርገው ውሃ በመጨመር ህጻናቱን ሣፋው ላይ በማንከባለል ህይወታቸውን ለማትረፍ የሚችሉትን አደረጉ።

በዚያ ሙቀት የበረዶ እድሜ አጭር ነበር። በተመሳሳይ የህጻናቱም እድሜ አጠረና ህጻናት ለሞት ተዳረጉ። በዚያን ጊዜ ከታዘብኩት ነገር አንዱ በሰው ተተክለው የነበሩት የአሰብ ዛፎች በመላ ቅጠላቸው አረንጓዴ ቢሆንም ያለምንም እንቅስቃሴ ድርቅ ብለው በመቆም ነፋስ ከሠው ለማግኘት የሚፈልጉ መምሰላቸውን ነበር።

ይህን የመሰሉ በረሀዎች በአፋር፤ በድሬዳዋ፤ በሶማሌና በሌሎች ክልሎች አሉን።

ነግ በእኔ ነው ነገሩ፤ እኔ ለወገኖቼ ማሳሰብ የምወደው መትከላችንን እየቀጠልን መቁረጣችንን ማቆም ያለብን መሆኑን ነው። ለመሆኑ በደን ውስጥና በደኖቻችን አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ትምህርት በመስጠት ብዙም ሳይርቅ ወደ ሌላ አካባቢ ወስዶ ለማስፈር ያለመሞከሩ መሬት የመንግስት መሆኑ ተዘንግቶ ነው? ወይስ ሌላ? ለሰሚ ግራ የሆነ ነገር ነው። በዚህ በሠለጠነ ዘመን የአዲስ አበባ የቤት አከራይ ጉዶችን ጉድ ደግሞ ልንገራችሁ። ቤት ለመከራየት ስትሄዱ በቅድሚያ የሚሰጣችሁ መመሪያ (ማስጠንቀቂያ) ምጣድና ምድጃ በኤሌክትሪክ መጠቀም አይቻልም የሚል ነው። ታዲያ በምንድን ነው የምንጠቀመው? ብላችሁ ብትጠይቁ በእንጨት የሚል መልስ ታገኛላችሁ።

የዱሮ ኤንትሬ መኪኖች በዚችው በመዲናችን ምን እየሰሩ የሚኖሩ ይመስላችኋል? አጠናና ግንዲላ በመሸጥ የሚኖሩትስ?

ዛፍ ተተከለም አልተተከለም፤ ደን ኖረ አልኖረም፤ የመንከባከብ፤ እንዝህላልነትና ዛፎችን የመቁረጡ ተግባር፤ እንዲሁም በደን ውስጥ የመኖር ሂደት እስከቀጠለ ድረስ ከንቱ ልፋት ነው የሚሆነው፤ በሌላ በኩል በፕሮጀክት የተተከሉትን ዛፎች በጅምላ የሚሸጡትስ? በስመ ህጋዊነትና በስመ ስልጣን እየተነሱ፤ እንዲሁም ከደን ጠባቂ ተብየዎች ጋር እየተመሳጠሩ ጨለማንና ሌሊትን ተገን በማድረግ ዛፍ እየቆረጡ የሚሸጡትንና አጣና በሸክም እያጓጓዙ የሚቸበችቡትን የኢትዮጵያ ህግና መንግሥት ምን ይሏቸዋል?

ከላይ በአሰብ ደርሶ ስለነበረው የተነተንኩላችሁ የማይደርስ እየመሰለን “ሜዳ ሲቃጠል ጋራ ይስቃል” እንዳይሆን ነው።

ለመሆኑ ለወደፊት ትውልዳችን ምን እያሰብን ነው?

ይህችን ቀላሏን ነገር ተግብረን፣ ዛፍ ተክለንና ተንከባክበን፣ አሳድገን፣ አውርሰነው ብናልፍስ? እስኪ እራሳችንን እንጠይቅ ዕደሉ እፊታችን ነው ያለው። አራት ቢሊዮን ችግኝ ቀርቦልናልና ወደ ፊት።

የሚቀረው የእኛ ፈቃደኝነት ነው።

ኧረ ይህንንስ ማን አየበት?

ቸር እንሰንብት!

አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2011

ፋንታሁን ሀይሌ