ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የዋና ኦዲተርን ሪፖርት አልቀበለውም አለ

26

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት መጤ ዝርያዎች አካባቢን እንዳይበክሉ በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት አልተወጣም ሲል ዋና ኦዲተር ያቀረበው ሪፖርት ኢንስቲትዩት እንደማይቀበለው ገለጸ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2010 በጀት ዓመት የፌዴራል መስሪያ ቤቶችን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት መጤ ዝርያዎች አካባቢን እንዳይበክሉ በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት አልተወጣም ሲሉ ሪፖርት አቅርበዋል። ይህ ሪፖርት የአመለካከትና የግንዛቤ እጥረት እንዳለበትና አካሄዱም ትክክል አለመሆኑን ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።

እንደ ዋና ኦዲተሩ ማብራሪያ ኢንስቲትዩቱ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ በ2003 ዓ.ም በጣና ገባር በሆነው መገጭ ወንዝ ላይ ይታይ የነበረውን የእንቦጭ አረም በወቅቱ መቆጣጠር ባለመቻሉ በ2004 ዓ.ም አምስት ቀበሌዎችን በማዳረስ አራት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ተስፋፍቷል፡፡ በ2005 ዓ.ም ደግሞ 15 ቀበሌዎችን በማዳረስ በ20 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተስፋፋ ሲሆን፤ በእነዚሁ ቀበሌዎች አጠቃላይ 50 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሊስፋፋ መቻሉን ዋና ኦዲተሩ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በእንቦጭ አረም የተሸፈነው የውሃ አካል መጠን በፌዴራል ደረጃ ጥናት ያልተከናወነ ቢሆንም የመከላከል ስራው በአስቸኳይ ካልተከናወነ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሌሎችም ሀይቆችና ወንዞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርዮ፤ የፌዴራል ዋና ኦዲት ሪፖርት ላይ የአመለካከትና የግንዛቤ እጥረት እንዳለ ይታያል፡፡ የሪፖርቱ አካሄድም ትክክል አይደለም። የዋና ኦዲተሩ ባለሙያዎች ወደ ኢንስቲትዩቱ የመጡት ስለ እምቦጭ አመጣጥና ሳይንሳዊ ሁኔታዎችን ለመረዳት መረጃ ፈልገው ሆኖ ሳለ በኦዲቱ ሪፖርቱ የተገለጸው ኢንስቲትዩቱ ኃላፊነቱን አለመወጣቱን ለመመርመር አይደለም ብለዋል። ‹‹በውይይቱም ላይ ችግሩ በአንድ ተቋም ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን ያስረዳን ቢሆንም ግብረ መልስ አልሰጡንም››ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ኢንስቲትዩት ከውጭ የሚገቡ መጤ ዝርያዎችን መቆጣጠርና ጥናትና ምርምር ማድረግ ኃላፊነት ቢሰጠውም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያሉትን 35 የታወቁ ወራሪ መጤ ዝርያዎችን ለማጥፋት የሚያስችል አቅምም ሆነ መዋቅር የለውም።ኢንስቲትዩቱ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል መዋቅርና ሀብት እንዲመደብለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢጠይቅም ሊጸድቅለት አልቻለም።

በአገሪቱ የምስራቁ ክፍል በተለምዶ ‹‹የወያኔ አረም›› የሚባለው መጤ አረም እንኳ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር ተወሯል። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች በርካታ መጤ ዝርያዎችና የአገር ውስጥ አረሞች አገሪቱን መወረራቸውን ገልፀዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለኢንስቲትዩት አስፈላጊው መዋቅር፣ በጀትና የሰው ኃይል ሊፈቀ ድላቸው እንደሚገባም ገልፀዋል። ከዚህም በላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተለያዩ ተቋማት እንዳሉና በዋናነትም የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ባለስልጣን እንዲሁም መንግስት ያቋቋማቸው በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ጉዳዩ እንደሚመለከታቸው ዶክተር መለሰ አብራርተዋል።

አዲስ ዘመን  ሰኔ 5/2011

አጎናፍር ገዛኸኝ