በአዳማ ከተማ በመሬት ወረራ ላይ ህጋዊ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገለጸ

36

አዳማ፤ ዘንድሮ በመሬት ወረራ ተይዞ የነበረ 28 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ወደ መንግሥት እንዲመለስ ማድረጉን እና ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ርምጃ መውሰዱን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የአዳማ ከተማ ገለጸ፡፡

የአዳማ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት፤ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ ለከተማው ችግር ሆኗል። ዘንድሮ በአዳማ ከተማ በዘጠኝ ወራት በተወሰደው እርምጃም አንድ ሺህ 19 ቤቶች፤ 262 አጥሮች ፈርሰዋል፡፡ በህገ ወጥ ግንባታ የተወረረ 28 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ወደ መንግሥት እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ በህገ ወጥ መንገድ መሬት ለመውረር ተገልብጦ የነበረ 739 ሜትር ኪዮብ ድንጋይ ተወርሷል፡፡

የላንድ ካዳስተር ሲስተሙ በጣም የተዳከመ ነበር ያሉት አቶ መስፍን፤ አንዳንዴ ሲሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲቀዘቅዝ የነበረበት አጋጣሚ መስተዋሉንም ተናግረዋል፡፡ ሂደቱ የመሬት ስርቆት እንዲቆም የማይፈልግ አካል ያለ እንደሚያስመስለውም ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ መስፍን ገለጻ፤ ከህገ ወጥ ግንባታ ጋር ተያይዞ ለመሬት ወረራ የሚያመቻቹ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ ሀሰተኛ የመሬት ካርታ ሰርተው የመንግሥትን መሬት ካርታና ፕላን ሰርተው ሲሸጡ የነበሩ ግለሰቦችንም በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል፡፡

ግንቦት 09 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለ ችሎት አንዱን 19 ዓመት፤ ሌላውን ደግሞ 16 ዓመት ቅጣት አስፈርደናል። መሬቶቹም እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ከህገ ወጥ የመሬት ወረራው ጋር ንክኪ የነበራቸው 19 የጸጥታ ሃይሎች ላይም ህጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃ ተወስዷል፡፡ 23 ሰዎች ላይም በተመሳሳይ መልኩ ህጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃ ተወስዷል ብለዋል። ተጠያቂነቱ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

አሁን 75 የሚደርሱ ባለሙያዎች ተቀጥረው ወደ ሥራ ገብተው መሬት እየተቆጠረ እንደ ሚገኝም ተናግረዋል፡፡ የነባር ይዞታዎችንም የማጽደቅ ሥራ መሰራቱንም ነው የገለጹት። በዚህ ስራ ላይ ህብረተሰቡም ሊተባበር ይገባል ብለዋል፡፡ የላንድ ካዳስተር ሥርዓትን እስካልተተገበረ ድረስ ችግሩን ማስቆም አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ህገ ወጥ ንግድን በከተማው ለመከላከል ቁጥጥር እና ክትትል ተደርጓል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በተሰራው ሥራም አምስት ሺ 167 በሚሆኑት ላይ እንደጥፋታቸው ደረጃ ህጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

ከነዚህ ውስጥ አንድ ሺ 944 ፍቃድ ሳያወጡ እና ግብር ሳይከፍሉ ሲነግዱ የነበሩትን ፍቃድ እንዲያወጡና ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓቱ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል። በቁጥጥር ሥራው በዳቦ ንግድ በተሰማሩና የዱቄት ፋብሪካዎች 32 በሚደርሱት ላይ ርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት የተጣለባቸውን አደራ ባለመወጣታቸው ነው ህጋዊ ርምጃ የተወሰደባቸውም ብለዋል፡፡

አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011

ዘላለም ግዛው