ህጻናት የወደፊታቸውን ሊያልሙ እንጂ በስራ ሊበዘበዙ አይገባም!

16

 የዓለም የስራ ድርጅት እኤአ 2002 ጀምሮ ጁን 12/ሰኔ 5 ቀን በየዓመቱ የህጻናት የጉልበት ብዝበዛ እንዲቆም ዓለም አቀፍ መታገያና መታሰቢያ ሆኖ እንዲከበር ወስኗል። ይህንንም ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ዕለቱ የህጻናት የጉልበት ብዝበዛ እንዲቆም ተቃውሞ የሚሰማበት ሆኖ እንዲውል አድርጓል። ዘንድሮም ይህ ዕለት “ህጻናት ስለወደፊታቸው ከማለም ውጭ በየትኛውም የስራ መስከ መሰማራት የለባቸውም” በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

በድርጅቱ መረጃ መሰረት፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ አንድ መቶ ሃምሳ ሁለት ሚሊዮን ህጻናት በከባድ ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። እነዚህ ህጻናት በሁሉም ዓይነት ስራዎች የተሰማሩ ቢሆንም ከአስሩ ሰባቱ በግብርናና ተያያዥ ስራዎች ጉልበታቸውን የሚበዘበዙ ናቸው።

በሌላ በኩል፤ የተባባሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት ግቦች አንዱ ዒላማ ይህንን የህጻናት የጉልበት ብዝበዛ እኤአ በ2025 እስከመጨረሻው ማስወገድ ነው። በዚህም እድሜአቸው ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ለጤናቸውና ለአካላዊ ዕድገታቸው አደገኛና ከባድ በሆኑ ስራዎች ላይ በፍጹም መሰማራት እንደሌለባቸው ያሳስባል። ሁሉም አባል አገራትም የግዳጅን ስራ ለማስቀረት አፋጣኝና ውጤታማ ርምጃ እንዲወስዱ ይጠይቃል።

እንደ ሌሎቹ የዓለም አገራት ባይሆንም በኢትዮጵያም እንዲህ ዓይነቶቹ ህጻናት ከእድሜአቸውና ከአካላዊ አቅማቸው በላይ ስራ ላይ የማሰማራት ተግባር ይታያል። ለጉዳዩ መፍትሔ ተደርገው የሚወሰዱት ደግሞ ርሀብ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቸ ናቸው። ከሁሉም በላይ ግን እየከፋ የመጣው የአታላይ ደላሎች የውስልትና ንግግርና በብልጭልጭ ነገሮች በማማለል ወደአልተገባ ስራ የማሰማራት እኩይ ተግባር ነው።

በሌላ በኩል፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ህጻናትን በማስገደድ፤ በማፈንና በመስረቅ ወደሌሎች አካባቢዎች ወስደው ከእረኝነት ጀምሮ በሌሎች የቤት ውስጥና የማሳ ስራ እንዲሰማሩ የሚያደርጉ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ ይታወቃል። በዚህም የተነሳ በርካታ ህጻናት ከአቅማቸው በላይ የሚሰጣቸውን ስራ መስራት ሲያቅታቸውና የቀጣሪዎቻቸውን ፍላጎት ማሟላት ሲሳናቸው በእሳት የመቃጠል፤ በስለት የመወጋት፤ እንዲሁም የሌላ አካላዊ ጥቃት ሰለባ ይሆናሉ።

አዎን በየትኛውም አካባቢ የቤተሰብ ኑሮ ሲያዘቀዝቅ፤ የማህበረሰብ የመሰብሰብ አቅም ሲያንስ፤ እና የአኗኗር ዘይቤ አቃፊ ሳይሆን ሲቀር የመጀመሪያ ረድፍ ተጎጂዎች ህጻናት ናቸው። እናም ህጻናት በቤተሰባቸው መቸገር፤ መጎሳቆልና እነርሱን መሰብሰብ አለመቻል የተነሳ ከትምህርት ገበታቸው ይስተጓጎላሉ። ከቤታቸው ይወጣሉ፤ ከቀያቸው ርቀውም ይሄዳሉ። ይሕም ለብልጣብልጥ ደላሎች ይጋለጡና ለችግር ይዳረጋሉ።

በእንደዚህ ዓይነት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ቤተሰብ የተበተነባቸውና ጨለማ የዋጣቸው ህጻናት በአዕምሮ ያልበሰሉ፤ በአካላቸው ጥቃትን መቋቋም የማይችሉ በቀላሉ በጨካኞች እጅ ስር ወድቀው ለባርነት፤ ለከባድ የጉልበት ስራ እና በተለይ ሴቶች ከሆኑ ለወሲብ ንግድ በሸቀጥነት ይቀርባሉ። በዚህ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ መረቡን የዘረጋው የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰንሰለት ሚናው ከፍተኛ ነው።

ህጻናት የቤተሰብ ፀጋዎች የመሆናቸውን ያህል በወጉ ተይዘውና ተኮትኩተው ሲያድጉ የወደፊት የአገር ተስፋዎች ናቸው። ለዚህ ደግሞ፤ አቅም በፈቀደ መጠን ትምህርት ተምረው፤ በስነምግባር ታንጸው እንዲያድጉ እንክብካቤ ሊደረገላቸው ይገባል። ከሁሉም በላይ ግን በዘመናዊ ባርነት ቀንበር ስር ወድቀው የሀገር ተስፋነታቸው ሊደበዝዝ አይገባም።

የዘንደሮው “ዓለም አቀፍ የፀረ-ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ቀን” ሲታሰብ መሪ ቃሉ እንደሚለው፤ ህጻናት ህልማቸውን፤ ነገአቸውንና ተስፋቸውን ሊያልሙ እንጂ፤ ከአቅምና ከእድሜአቸው በላይ በሆነ የጉልበት ስራ ላይ ተሰማርተው የአሰሪዎቻቸው መበልጸጊያ መሆን የለባቸውም። ለዚህ ደግሞ የትምህርት፤ የምግብና መጠለያ፤ የጤና ፍላጎታቸው ተሟልቶላቸው ሊያድጉ ይገባል።

በዚህ ረገድ ህጻናትን ብቻ የተመለከተ ልዩ የመብት ጥበቃ የሚያደርግ አህጉራዊ ስምምነት የሚያሳይ የአፍሪካ የህጻናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር ጸድቋል። በዚህ ቻርተር ውስጥ የእኩልነት፤ የህጻኑን ጥቅም የማስቀደም፤ በህይወት የመኖርና ማደግ፤ እንዲሁም ሀሳብን በነጻ የመግለጽ አራት መርሆዎች ይገኛሉ። ሁሉም መርሆዎች ህጻናት ያለአድልዖና ያለጉዳት በእንክብካቤ እንዲያድጉ የሚያሳስቡ ናቸው። ኢትዮጵያ አገራችንም በተባበሩት መንግሥታት የወጣውንም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ የጸደቀውን ቻርተር ተቀብላለች። ይሁን እንጂ፤ በትኩረት እጥረትም ይሁን በትምህርት ያለመስፋፋት ምክንያት በከተማም ይሁን በገጠር እነዚህ የህጻናት መብቶች ተጥሰው ክብራቸው ተነክቶና ከአቅም በላይ ለሆኑ የጉልበት ስራዎች ተዳርገው እናገኛለን። ይህ ሊቆም ይገባል።

በእርግጥ፤ በህገወጥ አዘዋዋሪዎችና በአማላይ ደላሎች የሚደርሰው የህጻናት ስርቆት፤ ማስኮብለልና በከባድ የጉልበት ስራ የማሰማራት አዝማሚያ ከሌሎች የኤስያና የላቲን አሜሪካ እንዲሁም ከአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች አንጻር ሲታይ አነስተኛ ነው ሊባል ይችላል። አዝማሚያዎቹና ምልክቶቹ አሉና በፍጹም የለም ማለት ግን አይደለም። እናም፤ “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ ሳይስፋፋ ልናስቆመው ግድ ይለናል።

በመሆኑም፤ አገሪቱ የተቀበለቻቸውን የህጻናት መብትና የደህንነት ቻርተሮች በማስተዋወቅ፤ በማስተማርና በየደረጃው ግንዛቤ በማስጨበጥ በኩል የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል። ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትም የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው። ህብረተሰቡም ህጻናት የሚወጡት ከጉያው፤ ለጉዳት የሚዳረጉትም በዚያው በመሆኑ እነርሱን ሊንከባከብ፤ አጥፊዎችን ሊያርም፤ እልፍ ሲልም ወደ ሕግ ሊያቀረባቸው የግድ ነው።

በመሆኑም የዘንድሮን “ዓለም አቀፍ የፀረ-ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ቀን” ስናከብር ህጻናት የወደፊታቸውን ሊያልሙ ይገባል እንጂ በከባደ የጉልበት ስራ ተሰማርተው ሊበዘበዙ አይገባም በሚል እውነተኛ ሃሳብና እምነት መሆን አለበት።

አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011