‹‹በአካባቢው የመፈናቀል አጀንዳ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል›› አቶ አበራ ቡኖ የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

17

በኢትዮጵያ በተከሰቱ ብሔር ተኮር ግጭቶች ሳቢያ ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።ይህን ተከትሎም ዜጎች በተፈናቀሉባቸው አካባቢዎች የግጭቶችን መነሻ ምክንያቶች በመለየት አካባቢዎቹን ወደ ቀደመ ሰላማቸው ለመመለስ የሚያስችሉ ህዝባዊ ውይይቶች ተደርገዋል።ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል አንዱ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞንና በደቡብ ክልል ጌዴዮ ዞን፤ አማሮና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ይገኙበታል።

በእነዚህ አካባቢዎች መንግስት ተፈናቃዮች የዕለት እርዳታ እንዲያገኙ እና በግጭት የወደሙ ንብረቶችን ለመተካት እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል። ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ከተመለሱ በኋላ መኖሪያ፤ ትምህርትና ህክምና እንዲያገኙ የማድረግ ስራም እየተሰራ ይገኛል።በሌላ በኩል፤ በየአካባቢዎቹ ግጭት በማስነሳት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው። በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ከአቶ አበራ ቡኖ ጋር ያደረግነው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ

የፖለቲካ አጀንዳ ባላቸው የተወሰኑ ግለሰቦች የተነሳ በ2010 ዓ.ም በጉጂና በጊዴዮ ማህበረሰቦች መካከል ግጭት ተከስቷል።አመራሩ የቀውስ ጊዜ ዕቅድ በማውጣት ሲንቀሳቀስ ነበር።አንደኛ፤ በባህላዊ መንገድ በአባገዳዎች አማካኝነት የዕርቅ ስነ ስርዓት እንዲፈጸም ተደርጓል።ሁለተኛ ደግሞ፤ በአስተዳደራዊ መንገድ ህዝብን የማወያየት፤ መልሶ የማቋቋምና የተፈናቀሉት ወገኖች እንዲረጋጉ ከማድረግ አኳያ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።ስኬታማ ስራ ሰርተናል ማለት ይቻላል፡፡

ዘንድሮ በአንዳንድ አሉባልታ ወሬና የጸጥታ ስጋት የተነሳ የተወሰኑት እንደገና የመፈናቀል ስጋት ላይ ወድቀው ነበር።በአጠቃላይ 99 ሺህ 295 ሰዎች ከጉጂም ከጌዴኦም ተፈናቅለዋል።እነዚህ ተፈናቃዮች አብዛኛዎቹ በወሰኖች አካባቢ ያሉ ሰዎች ናቸው።ከጌዴኦ ዞንና ከአስተዳዳር ወሰኖች አካባቢ ተፈናቅለው የመጡ ጉጂ ኦሮሞዎች አሉ፤ በተመሳሳይ ደግሞ ከጉጂ ወደ ጌዴኦ የተፈናቀሉ ጌዴኦዎችም አሉ፡፡

እነዚህን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ከመመለስ አኳያ የኦሮሚያ እና የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስታት በክልል ደረጃ፤ እንዲሁም የምዕራብ ጉጂ ዞንና የጌዴኦ ዞንም አንድ ላይ ሆነን ዕቅድ በማውጣት በሶስት ምዕራፍ እስከ ቀበሌ ድረስ ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል።ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ከመመለሳቸው በፊት አንደኛ ያልተፈናቀሉትንም ሆነ ተፈናቃዮችን አወያይተናል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንዲመለሱ፤ ያልተፈናቀለው ህብረተሰብ ደግሞ እንዲቀበላቸውና ዕገዛ እንዲያደርግላቸው የውይይቱ አጀንዳ ነበር።በውይይቱም የጋራ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።በርግጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ ነበር።አሁን ላይ ከ99 በመቶ በላይ ማለት ይቻላል ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

በምዕራብ ጉጂ በኩል ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በተደረገው ጥረት ሶስት ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሲሰሩ ቆይተዋል።አንደኛ፤ ከጌዴኦ ዞን የሚመጡትን ተፈናቃዮች የሚቀበል ሲሆን፤ ሁለተኛ፤ የጉጂ ተፈናቃዮችን ወደ ጌዴኦ የሚልክ ኮሜቴ ነው።ሶስተኛ ከህዝቡ ጋር ውይይት በማድረግ ተፈናቃዮችን ድጋፍ እንዲያደርግ የሚያስተባብር ኮሚቴ ነው።ለምሳሌ፤ የሀይማኖት አባቶችን፤ አባ ገዳዎችንና ዕድሮችን በማነጋገር ህብረተሰቡ ተፈናቅለው ለነበሩት የቤት ቁሳቁስ፤ የእርሻ መሳሪያ በማቅረብና ቤት በመስራት ዕገዛ እንዲያደርግላቸው ኮሚቴው ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በአጠቃላይ እነዚህን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ከሰራን በኋላ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ ነው የሰራነው፤ በሁሉም አቅጣጫ ማለትም ከጌዴኦ ተፈናቅለው የመጡት ጉጂዎች ከጉጂም ተፈናቅለው ወደ ጌዴኦ የሄዱትን ሙሉ በሙሉ ወደቀያቸው የመመለስ ስራ ተሰርቶ ተጠናቅቋል።ይህን መሰረት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርጫ ድረስ በመምጣት ወደ ቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮችን ጎብኝተውና አወያይተው ተመልሰዋል፡፡

በሁለቱም ወገን ማለትም፤ በጉጂና በጌዴኦ 99 ሺህ 255 ተፈናቃዮች ወደቀድሞ መኖሪያቸው ተመልሰዋል።አሁን ምን አልባት በህመም ምክንያት የቀረ ሰው ካለ ነው እንጂ ወደ ቀየው ያልተመለሰ ተፈናቃይ የለም።በህመምም ሆነ በተለያየ ምክንያት መምጣት ያልቻሉ ካሉ በሚል የእነሱን ጉዳይ የሚከታተል አንድ ቡድን አቋቁመናል።ይህ ቡድን ወደ ጌዴኦ ዞን ሄዶ የማጣራት ስራ ይሰራል።በህመም ከቀሩ እዚህ መጥተው ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል።በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው የመፈናቀል አጀንዳ ሙሉ ለሙሉ ተዘግቷል፡፡

የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ

እርግጥ ነው ከጌዴኦ ዞን ብቻ ሳይሆን ከአማሮና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ጋርም በአስተዳዳር ወሰን አካባቢዎች ችግሮች ነበሩ።ቁጥራቸው አነስተኛም ቢሆን ከዚህም ከዚያም የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ።ሰሞኑን በሁለቱ መካከል ተከስቶ በነበረው ግጭት ውይይት በማድረግ እንዲፈቱ አድርገናል።ከአማሮ ጋርም እንዲሁ ውይይት በማድረግ አካባቢውን የሰላምና የልማት ቀጣና እናደርጋለን ብለን እየሰራን ነው፡፡

ህብረተሰቡም ግጭቱ የእኛ ሳይሆን የሌላ አጀንዳ ነው።ከግጭቱ ጀርባ ያሉ ድብቅ አጀንዳዎችን አጋልጠን ለህግ ማቅረብ አለብን የሚል ውሳኔ ላይ ደርሷል። በእያንዳንዱ ቀበሌ ህብረተሰቡ በራሱ ተደራጅቶ የራሱን ደህንነት እየጠበቀ ይገኛል፡፡

የአማሮና የጉጂም ልክ እንደ ቡርጂና ጉጂ ግጭቱ ከሶስት ዓመታት በላይ የቆየ ነው።በአካባቢው ግጭት ይከሰታል፤ መልሶ ይከስማል።ዳግሞ የሚቀሰቀስበት ሁኔታ ይስተዋልም ነበር።ህብረተሰቡን በማሳተፍ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለመጀመር ዕቅድ አውጥተን ወደ ስራ ገብተናል።ህብረተሰቡ ራሱ እኛ ጥል፤ ግጭት አንፈልግም ብሏል።በተለይ በተፈጥሮ ሀብት፤ ማለትም በውሃና በግጦሽ ሳር የተነሳ ግጭት ይከሰት ነበር።ይህንን በጋራ ለመጠቀምና ሰላም ለማስፈን የአካባቢው አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ተስማምተዋል፡፡

አማሮና ጉጂም ችግሮቻቻውን ተወያይተው ይፈቱታል።የተፈናቀሉም ካሉ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ይደረጋል።ይህን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ቀጣናውን የሰላም አየር እንዲነፍስበትና ልማት እንዲስፋፋበት የሚደረግ ይሆናል።ህብረተሰቡም ፊቱን ወደ ልማት አዙሮ እየተንቀሳቀስን ነው።አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በተቻለ መጠን አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ወደ ልማት እንዲገቡ ጥረት ይደረጋል፡፡

በግጭቶች የተሳተፉ አመራሮችና የተወሰደ እርምጃ

“በግጭቶች የአመራሮች እጅ አለበት ወይ?” የሚል ግምገማ አድርገናል።በግምገማውም በግጭቶች ተሳትፈው የተገኙ አመራሮች ካሉ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ውሳኔ ላይ ደርሰናል።በዚህ መሰረትም ከ100 በላይ በሆኑት የቀበሌ፤ የወረዳና የዞን አመራሮች አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

ሌላው የህግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ በዞን ደረጃ ከፖሊስ ሁለት መርማሪ ቡድኖች አዋቅረናል።እነሱም ተንቀሳቅሰው እየሰሩ ነው።በአጠቃላይ በዚህ እንቅስቃሴ ወደ 267 ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል።89 ተፈርዶባቸዋል።ቀጠሮ ላይ ያሉ አሉ።25ቱ ጉዳያቸው በፌዴራል አቃቤ ህግ እየታየ ነው።በጥቅሉ አሁን በዞኑ አንጻራዊ ሰላም አለ ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

የልማት ስራዎች

በአንድ በኩል የጸጥታ ችግሮችን ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ሰርተናል።በሌላ በኩል ደግሞ፤ የልማት ስራዎችን እየሰራን ነው።በዞኑ በአርብቶና በአርሶ አደሮች አካባቢ የሚሰሩ ጅምር ፕሮጀክቶች አሉ።እነዚህን ፕሮጀክቶች የማጠናቀቅ ስራ ላይ እየተረባረብን ነው።ለምሳሌ፤ በፌዴራል መንግስት ሲሰራ የነበረው የጊዳቦ መስኖ ፕሮጀክት ግድብ ተጠናቅቋል።ወጣቶች በመስኖ ስራ ተሰማርተው የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው እያደራጀን ነው።በአምስት ሺህ ሄክታር 100 ማህበራትን በማደራጀት ለእያንዳንዳቸው ማህበራት 50 ሄክታር መሬት በመስጠት ዘመናዊና ገበያ ተኮር የግብርና ስራ እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡

ዞኑ ከ57 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለዓለም ገበያ ያቀርባል።ከዚህ አኳያ የቡና ምርትና ምርታማነቱን እንዲጨምር የሚያደርጉ ስራዎች እየሰራን ነው፡፡

የዞኑ ችግሮችና መፍትሄዎች

የዞኑ ዋና ችግር የሰላም እጦት ነበር እሱን እየፈታነው ነው። ከጌዴኦ፤ ከአማሮና ከቡርጂም ጋር ግጭት ነበር።የእነዚህ ዋና ዋና ችግሮች ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሰላም የማስፈን ስራ ሰርተናል።ሌላው የስራ አጥነት ችግር ነው።በአካባቢያችን ኢንዱስትሪ አለመኖሩ ደግሞ ስራ አጥነቱን አበራክቶታል።ዞኑ ገበያ ተኮር ምርቶች በብዛት የሚመረቱበት አካባቢ ነው።ቡና፤ ፍራፍሬ በብዛት ይገኛሉ።

በተለይ የግብርና ምርት ማቀነባባሪያ ፋብሪካዎች ቢኖር ለስራ አጥ ወጣቶች ስራ መፍጠር ይቻላል። በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች አሉ።ሌላው የመንገድ ችግር ነው።የቡሌ ሆራ- ሻኪሶ መንገድ፤ ከገርብ ቀርጫ-ሀንበላ ድረስ ያሉት መንገዶች የተበላሹ ናቸው።በህዝቡ እንደ መልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆነውም የሚቀርቡ ናቸው።የወረዳ ጥያቄም በቀላሉ የሚታዩ አይደለም። እነዚህ ጥያቄዎች ሁሉ ለመንግስት ቀርበው በሂደት ምላሽ ያገኛሉ፡፡

አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011

በጌትነት ምህረቴ