ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በአፍሪካ ዋንጫ በኮሚቴነት መሳተፋቸው ልምድ ለመቅሰም እንደሚያግዝ ተጠቆመ

9

በግብጽ አስተናጋጅነት በሰኔ ወር በሚካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በተለያዩ ኮሚቴዎች የሚሳተፉ ሙያተኞች ዝርዝር ውስጥ ኢንስትራክተር አብርሀም መብ ራቱ መካተታቸው እውቀቱና ልምድ ለመቅሰም እንደሚያግዝ ተጠቆመ፡፡

ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ድረገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ውድ ድሩን በዳኝነት ከሚመሩት የጨዋታው ዳኞች ኢንተርናሽናል ባምላክ ተሰማ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሣሙኤል በተጨማሪ፤ ኢትዮጵያ በኢንስትራክተር አብ ርሀም መብራቱ መወከሏ በዘርፉ እው ቀትና ልምድ ለመቅሰም እንደሚያግዝ ተጠ ቁሟል፡፡

የ2019ኙን የአፍሪካ ዋንጫ በተለያዩ ዘርፎች የሚያገለግሉ ሰላሳ ኮሚቴዎችና 224 የኮሚቴ አባላት ይፋ ሲደረጉ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ የውድድሩ ቴክኒክ ኮሚቴ የጥናት ቡድንን ተቀላቅሏል ሲል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

ይህ ቴክኒካል የጥናት ቡድን 15 አባላት ያሉት ሲሆን፤ በዋነኛነት የውድድሩን ኮከብ ተጫዋች ይመርጣል፤ የአፍሪካን የእግር ኳስ ደረጃን እና ቴክኒካል ነገሮችን ይገመግማል፡፡ ከውድድሩ የተገኙ አዳዲስ ነገሮችንም በሪፖርቱ ያቀርባል።

ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ ካፍ ስለሰጣቸው ሀላፊነት ሲናገሩ፤ “ከብዙ አገሮች ጋር ያገናኛል፤ እውቀቱንም ልምዱንም ለመቅሰም ይረዳናል፤ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማመቻቸት ይጠቅመናል፤ ይህንን እድል በማግኘቴ እኔ እዚህ ለመድረሴ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ያደረጉትን ሙያተኞች፤ የስፖርት ቤተሰቡን፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን እና ካፍን ከልብ አመሰግናለሁ” ብለዋል።

በዚህ ቡድን ውስጥ ኤሊት ኢንስትራክተሮች፤ በከፍተኛ ደረጃ የመጫወት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ጋር በማካተት የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ የታሰበ ነው።

አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011

 ዘላለም ግዛው