ቅሬታ የፈጠረው የሴቶችና የወንዶች እግር ኳስ ተጫዋቾች የክፍያ ወጣ ገባነት

11

ዛሬ ዓለም ላይ የሴቶች እግር ኳስ ተመልካችና ተደማጭነት እያገኘ መጥቷል፡፡ የሴቶችን የዓለም ዋንጫ ውድድር አንድ ቢሊዮን ተመልካቾች እንዳሉት ይጠበቃል፡፡ ከወንዶች እግር ኳስ ውድድር ጋር ሲነጻፀር የሴቶች እግር ኳስ ተጫዋቾች ክፍያና ሽልማት ግን እየጨመረ ሊመጣ አልቻለም፡፡

የአሜሪካ የሴቶች እግር ኳስ ድል ባለቤት ሆፕ ሶሎ እንደገለጸችው፤ በወንዶችና በሴቶች እግር ኳስ ቡድኖች የሚሰጠው የሽልማት ልዩነት አሁንም የወንዶች የበላይነትን አጉልቶ የሚያሳይ ነው ስትል የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽን የበላይ አመራሮች ትወቅሳለች፡፡

ለአብነትም ፊፋ እኤአ በ2015 በሴቶች የዓለም እግር ኳስ ውድድር ለተሳተፉ ቡድኖች ለሽልማትና ለተሳትፎ በአጠቃላይ 30 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሲያደርግ፤ በአንጻሩ ለወንዶች የዓለም ዋንጫ ውድድር ተሳታፊዎች ሽልማትና ማበረታቻ 400 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል፡፡ ይህም ከሴቶች ጋር ሲነጻፀር ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑን ታነሳለች፡፡

የሽልማት ገንዘቡም ለቡድኑ አባላት ሲከፋፈል ለእያንዳንዳቸው የሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች 800 ሺህ ዶላር ሲደርሳቸው፤ ለወንዶች ግን አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ ስትል ልዩነቱ ምን ያህል ሰፊ መሆኑን ገልጻለች፡ ፡ ይህም የሴቶችና የወንዶች እግር ኳስ ቡድኖች የሚያገኙትና የሚያመነጩት ገንዘብ ልዩነት ያለው መሆኑን ነው፡፡

ፊፋም የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ከሌሎች ውድድሮች ገቢው ተለይቶ የሚታይ አለመሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ፊፋ የሚከፍለው የሽልማት ገንዘብ ለተጫዋቹ የሚሰጥ ሳይሆን ለብሄራዊ ቡድኖቹ መሆኑን ገልጿል፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ክፍፍሉ የፊፋ ሳይሆን የብሄራዊ ቡድኖቹ ጉዳይ ነው የሚል ሀሳብ ሰንዝሯል፡፡ እናም የእግር ኳስ ተጫዋቾቹ ተወያይተው መፍትሄ የሚሰጡት እንጂ ለህዝብ ይፋ የሚሆን አጀንዳ አይደለም ብሏል የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤

የአስትራሊያ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ከሚያደርገው ውድድር የሚገኘውን ገንዘብ 30 በመቶ ለተጫዋቾቹ እንደየተሳትፎኣቸው የሚሰጥ መሆኑን ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ሌሎች ብሄራዊ የሴቶች እግር ኳስ ቡድኖች በዚህ ነጠላ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

“እንዲያም ተባለ እንዲህ ብሄራዊ የሴቶች እግር ኳስ ተጫዋቾች ለሽልማት ሆነ ለማበረታቻ የሚከፈላቸው ገንዘብ ከወንዶች እግር ኳስ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ የሴቶች እግር ኳስ ስፖርት ቡድኖች በስፖንሰርና በደመወዛቸው ላይ የተንጠለጠለ ነው›› ስትል የአሜሪካ እግር ኳስ ቡድን ታሪክ ጸሀፊ ካትሊን ሙሪይ ገልጻለች፡፡

የዓለም እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር መረጃ እንደሚያመላክተው በአሁኑ ጊዜ በምስራቅ አውሮፓ የእግር ኳስ ቡድኖች የሚጫወቱ ሴት ተጫዋቾች ወርሀዊ ክፍያ በአማካይ ከአንድ ሺህ እስከ ሁለት ሺህ ያገኛሉ፡፡ከብሄራዊ ቡድናቸው ደግሞ የቀን ዓበል ከ50 እስከ 100ዶላር ይከፈላቸዋል፡፡ምርጥ ተጫዋቾች ከፍተኛውን ክፍያ ተከፍይ ናቸው፡፡በታዳጊ አገራት የሚገኙ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ግን በጣም አነስተኛ ክፍያ እንደሚከፈላቸው ገልጧል፡፡

በእግር ኳስ ውድድሮች ለሴቶችና ለወንዶች ተጫዋቾች ለሽልማትና ለማበረታቻ የሚከፈለው ገንዘብ ከፍተኛ ቢሆንም፤ ለሴቶች ቡድኖች የሚከፈለው ገንዘብም በዚህ ዓመት በእጥፍ መጨመሩን ካትሊን ሙሪይ ሳትጠቅስ አላለፈችም፡፡ ይህ ለሴት የእግር ኳስ ተጫዋቾች ወሳኝ የተስፋ ምዕራፍ ነውም ብላለች፡፡

የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ፤ የሴት እግር ኳስ ቡድኖችን ለማበረታታት ተጨባጭ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጸው፤ የሽልማት ገንዘቡ አንዱ ነጠላ ጉዳይ ነው፤ ግን ፊፋ የሴቶች እግር ኳስ ቡድኖች እንዲጠናከሩና እንዲስፋፉ ሁለተናዊ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፤ ያሉት ደግሞ በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና የሴቶች ቢሮ ሀላፊ ሳራ ባርሜን ናቸው፡፡ በቀጣይ ሶስት ዓመታትም ፊፋ ለሴቶች እግር ኳስ ውድድሮች 400 እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለማድረግ ማቀዱን ይፋ አድርገዋል፡፡ ተቋሙ ባላፈው ዓመት ግን 28 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ወጪ ማድረጉን አውስተዋል፡፡

የአሜሪካ ብሄራዊ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን እኩል ክፍያ ጥያቄን በአገሪቱ ህግ መሰረት እንደሚጠይቅ አስታውቋል፡፡ የአዉስትራሊያ እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር በበኩሉ ደግሞ የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለወንዶችና ለሴቶች እግር ኳስ ተጫዋቾች እኩል ክፍያ ጥያቄ እንዳቀረበ አስታውቋል፡፡ የናይጀሪያ ሴት የእግር ኳስ ቡድን አባላት እኤአ በ2016 የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫን መውሰዳቸውን ተከትሎ በሆቴላቸው ባደረጉት አመጽ ክፍያቸው በተወሰነ መልኩ ተሻሽሏል። ኒውዚላንድ እኤአ በ2018 ለሴቶችና ለወንዶች ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድኖች እኩል ከፍያና ሽልማት ገንዘብ በመክፈል በዓለም የመጀመሪያዋ አገር ለመሆን በቅታለች፡፡

እኤአ በ2020 የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሴቶችና ለወንዶች ብሄራዊ እግር ኳስ ተጫዋቾች እኩል የሽልማት ክፍያ ለመፈጸም ስምምነት መደረሱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011

ጌትነት ምህረቴ