አዲስ ካፒታል አቅም የሆናቸው ኢንተርፕረነሮች

36

ወጣት አልማዝ ይረፉ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሩፋኤል አካባቢ ከአዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ባገኘችው የካፒታል ብድር ‹‹አልማዝ ይረፉ ልብስ ሥፌት ኢንተርፕራይዝን›› ከፍታ በመስራት ላይ ትገኛለች። ኢንተርፕራይዙም ለ55 ወጣቶች የሥራ እድል እንደ ፈጠረ ትናገራለች። መነሻዋ 30 ሺህ ብር እንደሆነ የምታስታውሰው አልማዝ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገቧን ገልጻለች። በአጠቃላይ ከ40 በላይ የልብስ ስፌት ማሽነሪዎች ከአዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ በሶስት ዙር መውሰድ እንደቻለች አጫውታናለች።

ወጣቷ እንደምትለው፤ አዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ፋይዳው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ምክንያቱም አንድ ወጣት ፍላጎቱና ሀሳቡ ኖሮት ካፒታል ከሌለው ምንም ማድረግ አይችልም። ማሽነሪ ከሌለው ታስሮ የመቀመጥ ያህል ነው ብላለች። ወዴት መሄድ ይችላል ስትልም ትጠይቃለች።

‹‹ወጣቱ አቅሙን ይዞ ከመቀመጥ የዘለለ አማራጭ አይኖረውም። ሥለዚህ የማሽን ችግሩን በዚህ መንገድ የሚያቃልልለት አካል ካገኘ በእኔ እምነት ቢያንስ ከ90 በመቶ በላይ ችግሩን ይቀርፍለታል፤ ሥራ መጀመር የሚያስችል አቅም ይሆነዋል የሚል እምነት አለኝ›› ብላለች።

ሌላው ተጠቃሚ ሀብታሙ ግርማ እንደተናገረው 580 ሺህ ብር የሚያወጣ ‹‹ሮተሪ›› የተሰኘ የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ወስዶ ሥራውን አስፋፍቶ በመስራት ላይ እንዳለ ነግሮናል። ወጣቱ ሥራ የጀመረው 1 ነጥብ አንድ ሚሊዮን የመስሪያ ካፒታል ይዞ ሲሆን፣ አሁን ላይ ማሽኑን ጨምሮ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ካፒታል ባለቤት ሆኗል። ለ15 ወጣቶችም የሥራ እድል መፍጠሩን አጫውቶናል።

‹‹ተቋሙ የሚያቀርብልህ በአይነት ዕቃ በመሆኑ ዘርፍ ለመቀየርም ሆነ ሥራውን ላለመጀመር አታመነታም። ከውጪ የሚያስመጣልህም ከታክስና ቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ ነው። በተጨማሪም በዚህ ወቅት የወጣቱን ተበድሮ የመስራት ፍላጎት በመገደብ ትልቅ እንቅፋት የሆነውን የዋስትና ችግር ያስቀረ መሆኑ በወጣቱ የተሻለና ተመራጭ ያደርገዋል። ሌላው ለየት የሚያደርገው ደግሞ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተህም ሆነ በተናጠል መበደር መቻልህ ነው።›› ብሏል ሀብታሙ።

ወጣት ሀብታሙ ‹‹የአዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አገልግሎት አቅርቦት ከዘርፍ ዘርፍ ሊለያይ ይችል ይሆናል። እኔ እየሰራሁ ባለሁት ዘርፍ የሚሰጠው የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ብድር ጣሪያው አንድ ሚሊዮን ድረስ ነው። ይሄ በሰፊው መስራትና ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚቻልበትን እድል የሚገድብ እንዳይሆን አቅሙ እየተጠና ከዚያ በላይ መውሰድ ቢቻል ጥሩ ነው ብሏል።

ከእውቅናና ከተደራሽነት ጋር ተያይዞም በማ ህበረሰቡ ዘንድ የአዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስን አገልግሎትን በርካታው ሰው አያውቀውም ብሏል ወጣት ሀብታሙ።

በአዲስ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማህበር የየካ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ መርሳ በበኩላቸው፤ ‹‹የሀገሪቱ ወጣቶች አሁን ላይ በርካታ የብድር አማራጮች ቀርበውላቸዋል። መንግሥት ሥራ አጥ ወጣቶችን ሥራ ለማስያዝና ኢኮኖሚውን ለማፋጠን ካለው ቁርጠኝነት የተነሳ በሥራ ለመሰማራ ፍላጎቱ ላለው ወጣት ብድር በአይነት ጭምር እያቀረበ ነው። ለአብነትም የአዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ተጠቃሽ ነው›› ብሏል።

የአዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መሳይ እንሴኔ እንደሚሉት ‹‹አገልግሎቱ ታሳቢ ያደረገው በዋናነት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትም ሆኑ ኮሜርሻል ባንኮች የማያስተናግዷቸው አሰራሮች በመኖራቸው ነው። ሌሎች አካላት ያለዋስትና ብድር ለመስጠት አሰራራቸው አይፈቅድም። የእኛ አሰራር ግን ማሽኑን ዋስ አድርጎ የሚሰጥነው። በተጨማሪም የካፒታል ችግርን ከመቅረፍ ባሻገር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንም የሚያስተዋውቅ ነው።››

አዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አገልግሎት ማህ በረሰቡ ደስተኛ ሆኖበታል ወይ? ችግሩን የሚቀርፍለት ተመራጭ አሰራር ሆኖ አግኝቶታል ወይ የሚለውን በተገቢው መለየት የሚያስችል ዝርዝር ጥናት አላደረግንም የሚሉት አቶ መሳይ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ ቤት ለቤት ተቋሙን የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል። በሥፋት ሕብረተሰቡ ላያውቀው ይችላል። በአሰራር በኩልም ብዙ መመሪያዎች የሚስተካከሉና ተተርጉመው መልክ መያዝ ያለባቸው በሂደት ላይ መኖራቸውን ተናግረዋል።

አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2011

ሙሐመድ ሁሴን