የዋጋ ግሽበት መንስኤዎች ሊቀጥሉ አይገባም!

31

በአገራችን በአሁኑ ወቅት የዋጋ ግሽበትን ጨምሮ የስራ አጥ ቁጥር መጨመር፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እጥረት፣ የወጪ ንግድ ሚዛን መዛባት፣ በአገሪቱ እየተገነቡ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በወቅቱ በጥራትና በተበጀተላቸው ሀብት መጠን ልክ አለመጠናቀቅ፣የመንግስት የብድር ዕዳ ከማክሮ ኢኮኖሚው ችግሮች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ የዋጋ ግሽበት አብዛኛውን የኢኮኖሚ ችግር ጠፍሮ የሚይዝ በመሆኑ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

የዋጋ ግሽበት የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ መጠን መጨመር ሲሆን የዚህ ተቃራኒው ደግሞ የሸቀጦች ዋጋ መቀነስ ነው፡፡ እንደ ዘርፉ ባለሙያዎች አስተያየት ከሆነ ሁለቱም ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት አገርን የመጉዳት ሚናቸው የጎላ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የጉዳት መጠናቸውም ሆነ ጉዳቱን የሚያደርሱበት ህብረተሰብ ክፍል የተለያየ መሆን ደግሞ የችግሩን አይነት የተለየ ያደርገዋል ሲሉ ምሁራን ይስማማሉ፡፡

የዋጋ ግሽበት በጨመረ ቁጥር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ክፉኛ ይመታሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ነው የዋጋ ግሽበት መጨመር ከባድ ነው የሚባለው፡፡ የዋጋ መናር በጣም ሲቀንስ /የሸቀጦች ዋጋ በጣም ሲቀንስ/ ተጎጂ የሚሆነው አምራች ክፍሉ ላይ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ ሁለቱም በድምሩ ጉዳታቸው በአገር ኢኮኖሚ እና ተያያዥ ዘርፎች ላይ የሚያደርሱት ጫና ስለሚበዛ የዋጋ ንረቱም ሆነ መቀነሱ ተመጣጣኝ ሆነው መጓዝ እንዳለባቸው ሁሉም የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡

የሆኖ ሆኖ በአገራችን ያለው የዋጋ ግሽበት በተለይ ላለፉት ተከታታይ አመታት ከ10 በመቶ በላይ በመሆኑ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ውስጥ እንዳለን በግልጽ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ግሽበቱ ቀንሶ አለመታየቱ የማክሮ ኢኮኖሚው ችግር ሆኖ ይወሰዳል፡፡ በተለይ በፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት ልንቆጣጠረው የሚገባ እንጂ ሊዝረከረክ አይገባም፡፡ በዚህ ሂደትም የአገራችን የዋጋ ግሽበት አለመረጋጋት ላይ መሆኑ የተለየ ባህሪው ነው፡፡

በተለይ በምግብ ፍጆታ ላይ ያለው ያልተረጋጋ የዋጋ ግሽበት በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ከመጉዳቱ ባለፈ መዘዙ ብዙ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች አስቀምጠዋል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ኢንቨስትመንትን ይጎዳል፣ ስራ አጥነትን ይጨምራል፣ የኢኮኖሚ እድገቱን ይገታል፤ በመጨረሻም የአገሪቱን ፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ይከተዋል ማለት ነው፡፡

ዋጋ በመሰረቱ ሊመራ የሚገባው በገበያ ነው፡፡ በአገራችን ያለው ሁኔታ ግን ባህሪው ከዚህ የተለየ በመሆኑ ጫናው የከፋ ነው፡፡ የዋጋ ግሽበት በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ ነው ሲባል በተለይ አምራቹም ሆነ ሸማቹ አቅዶ እንዳይንቀሳቀስ ስለሚያደርገው ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ እንደተባለው ዋጋው በገበያ ባለመመራቱ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ፍላጎት ቢቀንስም ዋጋ ቀንሶ አያውቅም፤ ዋጋው እንደተሰቀለ ይቀራል ማለት ነው፡፡

ይህ ብቻ አይደለም በአገር ውስጥ አንድ ኮሽታ ሲኖር እና መንገድ ሲዘጋ እንኳ የሸቀጦች ዋጋ መናር ስርዓት የሌለው ከመሆኑ ባለፈ የዋጋ ግሽበቱ አለመረጋጋት ቁልፍ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በጤነኛ የኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ ገበያው ዋጋን ሲመራ የግሽበት መንስኤዎች ውስጥ አንዱ ፍላጎት ነው፡፡ ነገር ግን በአገራችን እየሆነ ያለው ከዚህ ውጭ በመሆኑ መንግስት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ምሁራን አፅንኦት ሰጥተው ይመክራሉ፡፡

መንግስት ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ገበያው ከመርጨት መቆጠብ፤ የበጀት ጉድለትን ማስተካከል፤ የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በዋናነት ከውጪ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተመረኮዘ እንዳይሆን ማድረግ እና ከውጪ ሀገር የሚገባ የዋጋ ግሽበትን በዋናነት ሊቆጣጠራቸው እና ሊሰራበት የሚገባ ነው፡፡

ለዋጋ ግሽበት ምክንያት የሚሆኑ ለረጅም ዓመታት የቆዩ ከኢኮኖሚው መዋቅራዊ ችግሮች እስከ ሰው ሰራሽ መንስኤዎች አሁንም ሊቀጥል አይገባም በሚል ፅኑ አቋም መንግስት በየደረጃው ባሉ መዋቅሮቹ መስራት አለበት፡፡ የግብርና ምርትና ምርታማነት በሚፈለገው ልክ አለማደጉ የግብርና ምርቶች አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ክፍተት እየሰፋ መምጣቱም በተለይም የግብርና ምርቶች ዋጋ እንዲንር አንዱ መንስኤ በመሆኑ በአገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች መተካት ወሳኝ ሚናው መሆን አለበት፡፡

በአጠቃላይ መንግስት የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የገበያ ዋጋ መቆጣጠር መቻል አለበት፡፡ የሀገሪቱን የንግድ ህግን ማስተካከልና የንግድ ስርዓቱ ውስጥ ፍትሃዊነትና ውድድር እንዲኖር በዘርፉ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ ይገባዋል፡፡ ከሀገሪቱ የንግድ ዘርፍ 36 በመቶ የሚሆነው ኢ-መደበኛ ንግድ ወደ መደበኛ የሚመጣበትን ሁኔታ ማመቻቸትም ተገቢ ነው፡፡ እነዚህንና ሌሎች ስራዎችን በመስራት የዋጋ ግሽበት መንስኤዎች እንዳይቀጥሉ በማድረግ ችግሩን መቆጣጠር ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2011